“የአበው ሥርዓት ለቤተ ክርስቲያን አንድነት” በሚል ርዕስ ሲሰጥ የነበረው የሥልጠና እና የምክክር የሁለት ቀናት ጉባኤ የኣቋም መግለጫ

ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የምስካየ ሕዙናን መድኃኔዓለም ገዳም የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ፣
ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የቤተ መጻሕፍት ወመዘክር የማኅበራት ምዝገባና ቁጥጥር መምሪያ ሊቀ ጳጳስ፣
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት
ክቡራን ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጆች
ክቡራን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የየመምሪያው ኃላፊዎች
ክቡር የገዳማት መምርያ ኃላፊ መጋቤ ካህናት ቆሞስ አባ ሃብተ ጊዮርጊስ አሥራት፣
ክቡራን የኢትዮጵያ አንድነት ገዳማት አበምኔቶችና እመምኔቶች እንዲሁም
ጥሪ የተደረገላችሁ የክብር እንግዶች
ክቡራን የዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ታዳሚዎች
ከዚህ በመቀጠል ለሁለት ቀናት
የቆየንባቸውን የምክክርና የሥልጠና መርሀ ግብር ቃለ ጉባኤና የአቋም መግለጫ ከዚህ እንደሚከተለው እናቀርባለን
ጉባኤው በብፁዕ ጠቅላይ ሥራስኪያጅ
በብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ
በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በጸሎት የተጀመረ ሲሆን
በዲያቆናቱ በቅዱስ ዳዊት መዝሙር
ኪያከ ተወከሉ አበዊነ
ተወከሉከኒ ወአድኀንኮሙ
ኀቤከ ጸርሁ ወድኅኑ
የሚለውን ምስባክ ተሰብኳል።
የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 5 ከቁጥር አንድ እስከ አሥራ ሰባት ድረስ ያለው የተነበበ ሲሆን በማያያዝ ጸሎተ ኪዳን ደርሷል።
በመቀጠል የገዳማት መምርያ ኃላፊ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን በመልዕክታቸውም
ገዳማት የነበራቸውን ጥንታዊ ሥርዓተ አበው እና መናኝነታቸውን ሳይለቁ፣ በልማት ራሳቸውን መቻል የሚችሉበትን ዕውቀትና የልምድ ልውውጥ እንዲፈጠር ፤የገዳማቱን ክብር ለመጠበቅና አዲስ መናንያንን ለመቀበል የሚያስችል ወጥ የሆነ “የአንድነት ገዳማት መተዳደሪያ ደንብ” በምሁራን ተዘጋጅቶ በቅዱስ ሲኖዶስ እንዲጸድቅና ገዳማት ወደ ደብርነት የመቀየር አዝማሚያ እንዲቆምና
ገዳማት ከልመና ሕይወት ወጥተው ምርቶቻቸውን በቀጥታ ለተጠቃሚ የሚያቀርቡባቸው ማዕከላት በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች እንዲቋቋሙ በማድረግ፣ በገዳማት መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ልዩነት ማጥበብ ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል ካሉ በኋላ
የተከናወኑ እና ሊበረታቱ የሚገባቸው ብለው ያነሷቸው
የሶላር መብራት ድጋፍ፦ መብራት ለሌላቸው 33 ገዳማት በ5 ሚሊዮን ብር ወጪ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ተገዝቶ ለርክክብ መዘጋጀቱ
የገንዘብ ድጋፍ፦ በአደጋ ለተጎዱ ከ100 በላይ ገዳማት በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ድጋፍ መደረጉ።
የጠቆሙ ሲሆን
ገዳማት ሥርዓታቸውን ጠብቀው እንዲቆዩ ማድረግ የወቅቱ ወሳኝ ተግባር መሆኑን በመግለጽ፣ ጉባኤው ለዚህ መፍትሔ እንዲያመጣ ጥሪ አቅርበው
በማያያዝም ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የምስካየ ሕዙናን መድኃኔዓለም ገዳም የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ፣
ለጉባኤ መመርያና መልዕክት እንዲያስተላልፉ ጋብዘዋል።
ብፁዕነታቸውም
“ውእቱሰ ይወጽእ ገዳመ ወይጼሊ በህየ –
“እርሱ ግን ወደ ገዳም ወጥቶ በዚያ ይጸሊ ነበር”
(ሉቃ 5÷16) የሚለውን
የሚለውን ኃይለ ቃል መነሻ በማድረግ፣ አባታዊ መልእክትና መመርያ አስተላልዋል።
ብፁዕነታቸው በመልዕክታቸው
ገዳማዊ ሕይወት መሠረቱ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አርአያነት መሆኑን ገልጸዋል። ገዳም ለተመረጡና ለተጠሩ ቅዱሳን አባቶችና እናቶች የመንፈሳዊ ተጋድሎ ማዕከል መሆኑን ጠቅሰው፣ በኢትዮጵያም ጥንታዊና ታሪካዊ ትውፊት እንዳለው አብራርተዋል።
የገዳማትን ሚና በሦስት ዋና ዋና ጭብጦች ከፍለው እንደሚከተለው አሳስበዋል፦
የትምህርትና የሥነ ጥበብ ማዕከልነት፦ ገዳማት የአብነት ትምህርት ቤቶች መገኛ፣ የሊቃውንት መፍለቂያና የታሪክ ቅርሶች ማከማቻ መሆናቸውን ገልጸዋል። ዛሬ ላይ የጠፋውን የትውልድ ሥነ ምግባር ለመመለስ ገዳማት የአብነት ትምህርቱን አጠናክረው ሊቃውንትን ማፍራት እንደሚጠበቅባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።
የልማትና ራስን የመቻል አስፈላጊነት፦ ብዙዎቹ ገዳማት አሁን ላይ በኢኮኖሚ ቢዳከሙም፣ ያላቸውን ሰፊ የመሬትና የሰው ኃይል ተጠቅመው ወደ አምራችነት መሸጋገር እንዳለባቸው አሳስበዋል። ይህ ሲሆን ገዳማውያን በችግር ምክንያት ወደ ከተማ የሚያደርጉትን ፍልሰት ማስቆም እንደሚቻል ገልጸው፣ ምሁራንና ባለሀብቶችም በፕሮጀክትና ለገዳማት የሚያስፈልጉ የልማት መሣሪያ በማቅረብ ከገዳማት ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።
መንፈሳዊነትና ተቋማዊ አንድነት፦ የአገልግሎታችን መሠረት መንፈሳዊነት ሊሆን እንደሚገባና የሥጋ ምኞትን በማሸነፍ ለሀገርና ለዓለም ሰላም መጸለይ እንደሚገባ መክረዋል። ገዳማት ድክመቶቻቸውን በጋራ ውይይት ለመቅረፍና አላማቸውን ለማሳካት በገዳማት አስተዳደር መምሪያ ሥር ተቋማዊ አንድነታቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ በማሳሰብና መመርያ በመስጠት መልእክታቸውን አጠቃልለዋል።
በመቀጠል
የዕለቱ የክብር እንግዳ ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን
በመልዕክታቸው ያተኮሩባቸው ዋና ዋና ነጥቦች ሦስት ሲሆኑ
በሁሉም ገዳማት
አንደኛ ጸሎት፣
ሁለተኛ ትምህርት፣
ሦስተኛ ሥራ ፣
መሠረታዊ የገዳም ጠባይ ናቸው
ያሉ ሲሆን በገዳማቶቻችን አራት ዕንቊ ሀብቶች እናገኛለንንም ብለዋል
እነዚህም
የመንፈሳዊነት ማዕከል፣
የታሪካዊ ሀብቶች፣
የዕውቀት ምንጭ እና
የተፈጥሮ ሀብት ናቸው ብለዋል
ለዚህም ያነሱት ምሳሌ
መርከቧ በውሃ ውስጥ ብትሄድ ችግር የለውም።
ውሃ ወደ መርከቧ መግባት ሲጀምር ነው ችግር የሚመጣው ገዳማት በዓለም ውስጥ ነው ያሉት ይህ ችግር የለውም ዓለማዊነት ወደ ገዳም ከገባ ግን ከባዱ ነገር እሱ ነው
በገዳማቶቻችን አሁን እየቸገረን ያለው ችግርና የዓለማዊነት ወደ ገዳም ሠርገው መግባታቸው ነው።
ፈተናው ይመጣል ለምን መጣ አይባልም እንዴት እንወጣዋለን የሚለው ነው መታሰብ ያለበት ገዳማዊ ሕይወት ባለንበት ዘመን እንዴት እንወጣዋለን።
እኛ ነን ወደ እነርሱ መምጣት ያለብን
እነርሱ ናቸው ወደ እኛ መምጣት ያለባቸው
ዓለማዊነት አሸንፎ እንዳያስጨንቀን መጠንቀቅ አለብን።
ገዳማቶቻችን
በሰላም ጉዳይ
በትብብር ጉዳይ
በአንድነት ጉዳይ ጠንክረው መስራት አለባቸው በማለት
አውሮፕላን የሚነሳበት አለው መዳረሻም አለው በሀገራችን ከመቶ በላይ አውሮፕላኖች አሉ የሚነሳበትና የሚያርፍበት አለው።
ለአንድ መነኩሴም መነሻው እና መድረሻው ገዳም መሆን አለበት ሥምሪቱ ከገዳማት ሲሆን ትርፋማ መሆን እንችላለን ብለው መልዕክታቸውን አጠቃለዋል።
በመጀመርያ ውሎ
አምስት ጥናታዊ ጽሁፎች የቀረቡ ሲሆን
በመጀመርያ በፕሮፌሰር ቆሞስ አባ ሃይለ ገብርኤል
ቅዱስ ሥርዓት ገዳማዊነትንና መንፈሳዊነት ከዘመኑ አስተዳደር ጋር የሚል ሲሆን፤
በትምህርታቸው እነዚህን አበይት ነጥቦች አንስተዋል፦
ሥርዓተ አስተዳደር፦ እውነተኛ የምንኩስና ሥርዓት ቀልጣፋ የአስተዳደር መመሪያን፣ ግልጽ የሥራ ሰሌዳንና ውጤታማ የመግባቢያ ዘዴዎችን መከተል እንደሚገባው፤
ውስጣዊ ቅድስና፦ ያለ ውስጣዊ ሕይወት የሚደረግ ውጫዊ ግትርነት መንፈሳዊ ድርቀትን እንደሚያስከትልና
የገዳም እውነተኛ መመዘኛው የሥራ ቅልጥፍና ሳይሆን “ቅድስና” እንደሆነ፤
አስተዳደር እንደ ተጋድሎ፦ ገዳማዊ አስተዳደር ተራ ተግባር ሳይሆን መንፈሳዊ ተጋድሎ መሆኑን፤ ይህም ንብረትን በኃላፊነት መያዝንና “እኔ ከሌለሁ ገዳሙ ይፈርሳል” ከሚል የትዕቢት ስሜት መራቅን እንደሚጠይቅ፤
የጸሎት ቀዳሚነት፦ ማንኛውም አስተዳደራዊ ተግባር ከጸሎት መመንጨት እንዳለበትና የእግዚአብሔር መንግሥት ቀዳሚ፣ አስተዳደራዊ ሥራዎች ደግሞ ሁለተኛ ሆነው ሊመሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
“ሥራ በሥርዓት፣ ሕይወት በቅድስና፣ ንብረት በኃላፊነት፣ አስተዳደር በጸሎት!” መዋጀት እንዳለበት አሳስበዋል።
በመቀጠልም ረዳት ፕሮፌሰር ግርማ ባቱ
ረዳት ፕሮፌሰር ግርማ ባቱ በጥናታቸው እነዚህን አበይት ነጥቦች አንስተዋል፦
የገዳማት ልዩ ትርጉም፦ ገዳማት ለቤተ ክርስቲያን የታሪክ ማኅደር ብቻ ሳይሆኑ የነገረ መለኮት ምንጭ፣ ረድኤተ እግዚአብሔር የሚገለጥባቸውና የኦርቶዶክሳዊ መንፈሳዊ ሕይወት አርአያ የሚገኝባቸው ማዕከላት መሆናቸውን፤
የታሪክ ምንነትና ፋይዳ፦ ታሪክ ያለፈው ዘመን የሚጠናበት ዘርፍ ብቻ ሳይሆን፣ የነገሮችን ፍቺና የእድገት አዝማሚያ በመረዳት “ለመጻኢ አቅጣጫ መቀየሻ” የሚያገለግል የትናንትና የዛሬ ተዋስኦ መሆኑን፤
ታሪክ እንደ መድኃኒት፦ የታሪክ ጥናት ለተዛባና ለታመመ አዕምሮ ፍቱን መድኃኒት እንደሆነ፤ ቤተ ክርስቲያንም ለዛሬው ሕልውናዋ ያለፈችበትን የታሪክ ሂደትና የእምነት አቋም ማወቅ ለነገው ጉዞ ወሳኝ መሆኑን፤
የገዳማት ሚና፦ ገዳማት ታሪክን በመሥራት፣ በመጻፍና ጠብቆ በማቆየት ረገድ ያላቸውን የማይተካ ሚና በመረዳት፣ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ማጉላትና ነባራዊ ዕውቀትን ከነገረ መለኮታዊ መረዳት ጋር አጣምሮ መጓዝ እንደሚገባ አብራርተዋል።
ሦስተኛ ያቀረቡት ረዳት ፕሮፌሰር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል ሲሆኑ
የገዳማት የቅርስ አያያዝ
የቅርሶች ፋይዳ፦ ገዳማት የቅርሶች አምራችና ጠባቂ መሆናቸውን፤ ቅርሶች ደግሞ የቤተ ክርስቲያን የጥንታዊነት ምስክርና የበረከት ምንጭ መሆናቸውን ።
ቅርሶቹ በሁለት (ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀሱ) ተከፍለው የሚመደቡ ሲሆን ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል ብለዋል ።
ቅርሶችን ለመመዝገብ፣ ለመንከባከብና ለማጥናት የሚያስችል ወጥ መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ እና
ቅርሶችን በዘመናዊ መንገድ መመዝገብ፣ የጠፉትን ማስመለስና ሙዚየሞችን በማደራጀት ለጥናትና ለቱሪዝም ማዋል እንደሚገባ በአጽንኦት አሳስበዋል።
በጥቅሉ
“ቅርሶች የታሪካችንና የማንነታችን መገለጫ በመሆናቸው፣ አያያዛቸው በመመሪያና በዕውቀት ሊመራ ብለዋል”
እኛ የገዳማት አበምኔቶችና እመምኔቶች፣ ከብፁዕነታቸው የተሰጠንን አባታዊ መመሪያና ወቅታዊ ቃለ በረከት መሠረት በማድረግ፣ ገዳማቶቻችንን ከመንፈሳዊና ከዓለማዊ ተግዳሮት ለመጠበቅና የቀደመ ክብራቸውን ለመመለስ የሚከተሉትን ነጥቦች ለመፈጸም በልዑል እግዚአብሔር ስም ቃል እንገባለን፦
በመቀጠል
ከዐባይ ባንክ በመጡ በአቶ ማርቆስ ደመቀ የዐባይ ባንክ የሀብት ማሰባሰብ ዳይሬክተር
ስለ ሒሳብ አያያዝ ሥልጠና የተሰጠ ሲሆን
“ገዳማዊ አስተዳደር በንብረት አያያዝ ረገድ ጥንቁቅ ሊሆን ይገባል፤ ይህም ከጥሬ ገንዘብ ጀምሮ እስከ ቋሚ ንብረቶች ድረስ ያለውን ሀብት በትክክል በመመዝገብና ለታለመለት መንፈሳዊና ልማታዊ ዓላማ ብቻ በማዋል ገልጸው
በተለይም የገዳሙን ንብረትና ገንዘብ በሥርዓት ለመመዝገብና ከብክነት ለመከላከል ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት፤
ለወደፊት ዕቅድና ልማት ትክክለኛ የፋይናንስ መረጃ ለማግኘት ያስችላል ብለዋል”።
ሌላው ከልማት ኮሚሽን በመጡ መምህር ተዋነይ ሰይፈ ሥላሴ ስለ ገዳማትና ደን ጥበቃ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡ ሲሆን በጥናታቸውም
ደን የገዳማት መታወቂያ፣ የጸሎት ማዕከልና የተፈጥሮ ጸጋ ነው ያሉ ሲሆን
የገዳሙን የደን ድንበር በአጥር ማስከበርና ከንክኪ መጠበቅ።
አገር በቀል ችግኞችን በየዓመቱ በመትከል ተተኪ አጸዶችን ማብቀል እንደሚገባና “የገዳም ደን የእግዚአብሔር ድንቅ ፍጥረት መገለጫና የመናንያን መጠለያ በመሆኑ፣ ይህንን አረንጓዴ ቅርስ ጠብቆ ማቆየት ከመንፈሳዊ ተጋድሎ የማይነጥል ተግባር ነው።”ብለዋል።
በሁለተኛው ቀን ምንኩስና ትናንትናና ዛሬ በሚል ርዕስ በርዕሰ ሊቃውንት በየኔታ አባ ገብረ ኪዳን ግርማ የተሰጠ ሲሆን፡-
ያነሷቸውም ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው
የዛሬው መሰብሰባችን እንደ ተራ ክስተት የሚታይ አይደለም። እግዚአብሔር አምላክ ቤተክርስቲያንን ሊያሻግራት፣ ከጥበብ ድልድይ ሊያደርሳት እንዳሰበ የሚጠቁም መንፈሳዊ ኃይል አለው። “አስተናደፍኩ መሠረተ ከመ ጠቢብ ሊቀ ጸርብት” (እንደ ብልህ ግንበኛ መሠረትን መሠረትሁ) እንዲል ቅዱስ ጳውሎስ፣ እኛም የቤተክርስቲያንን ሕንጻ ለመጠበቅ መሠረቱን – ምንኩስናን ልንመረምር ተሰብስበናል ካሉ በኋላ
ለቤተክርስቲያን የሚሠራውም ሆነ ለቤተሰቡ የሚያስበው ራሱ እግዚአብሔር ነው። እኛ ግን “ቤተክርስቲያንን እኔ አሻግራለሁ” ብለን የራሳችንን “እኔነት” ስናስቀድም፣ ወደፊት እያሰብን ወደ ኋላ መጓዝ እንጀምራለን። የዛሬው ውይይታችን ዓላማ ይህንን “እኔነት” ሰብሮ የክርስቶስን ልብ መልበስ ነው ብለዋል በማያያዝም
ምንኩስና እንደ መሞት (መንኲሰ ሞተ) ማለት ሲሆን
ከእኔነት መለየት፦ መነኩሴ ማለት ከራሱ ፈቃድ፣ ከትዕቢትና ከዓለማዊ ማንነቱ የተለየ (የሞተ) ማለት ነው። “እኔ” የሚለው ስሜት ሲጠፋ የክርስቶስ ልብ ይተካል።
ከዓለም መለየት፦ ቁሳዊ ሀብትን፣ የባንክ አካውንትንና ምድራዊ ዝምድናን እርግፍ አድርጎ መተው ነው። መነኩሴ ለምስጋናም ለስድቡም እንደ ሙት የማይሰማ መሆን አለበት ያሉ ሲሆን አያይዘውም ምንኩስና እንደ መላእክት ሕይወት፡-
ሰማያዊነት፦ መነኩሴ በምድር የሚኖር መልአክ ነው። ተግባሩም ያለማቋረጥ መጸለይ፣ መታዘዝ፣ በትሕትና መኖርና ማኅበራዊ አንድነትን መጠበቅ ነው።
ትሕትናና ታዛዥነት፦ ጸጋን ትሕትና ይቀድመዋል። ያለ ታዛዥነትና ያለ ንጽሕና የሚደረግ ምንኩስና ፍሬ የለውም ብለዋል።
የዘመኑ ፈተናና መፍትሔ ናቸው ብለው ያነሷቸው ነጥቦች፡-
ፈተናዎች፦ ፍጹም ዓለማዊነት የቴክኖሎጂ (የስልክ) አጠቃቀም ሥርዓት ማጣት፣ የገዳማት አስተዳደራዊ ክፍተቶችና የኢኮኖሚ ጫናዎች የምንኩስናን ሕይወት አድክመውታል ያሉ ሲሆን፤
መፍትሔውን ሲያስቀምጡ ፦ መነኩሴ ፖለቲካ ውስጥ ሳይገባ ዘመኑን በመንፈሳዊ ጥበብ መዋጀት አለበት። ወደ ምንኩስና ከመገባቱ በፊት ትክክለኛ የቤተክርስቲያን ትምህርትና የሥነ-ምግባር ዝግጅት ሊኖር ይገባል።
ምንኩስና የቤተክርስቲያን የድል አክሊልና የሃይማኖት ጠበቃ ነው። ይህ ሕይወት ሲጠበቅ ቤተክርስቲያን ትጠበቃለች ብለዋል።
ከመምህራን በተሰጡ ጥናታዊ ጽሁፎች በመነሳት ከጉባኤው የቀረቡ ዋና ዋና ነጥቦችም
ሀ/ ሥርዓተ ገዳምን የሚያጸና ደንብ በሁሉም ገዳማት በጥናት መዘርጋት እንዲቻል ገዳማቱ የነበራቸውን ክብራቸውንና ልዕልናቸውን ጠብቀው እንዲቀጥሉ፤ አዲስ መናንያን የሚገቡበትን ሥርዓት ተጠንቶ እንዲቀርብና በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ እና ወደ ሁሉም ገዳማት እንዲተላለፍ
ለ/ የገዳማትን ክብርና ልዕልናን በሚነካና ታሪክን በሚያፋልስ መልኩ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አካላት እየታዩ መምጣታቸው በጉባኤው የተነሣ ስለሆነ፤ እነዚህ ሰዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ቅዱስ ሲኖዶስ ለየሀገረ ስብከቱ ጥብቅ መመርያ እንዲሰጥ
ሐ/ ራስን የመቻልና የልማት ማዕከላት፦ ገዳማት “ከእጅ ወደ አፍ” ከሆነ የልመና ሕይወት ወጥተው፣ በየከተማው በሚቋቋሙ ማዕከላት አማካኝነት ገዳማቱ የድካማቸውን ፍሬ (ምርቶቻቸውን) ለምእመናን የሚያቀርቡበት የልማት ሥርዓት እንዲዘረጋ።
መ/ የአብነት ትምህርትንና ሊቃውንትን መታደግ በተመለከተ፦
ገዳማት የሊቃውንት መፍለቂያነታቸው እንዳይገታ፣ በገዳማት ውስጥ የሚገኙ የአብነት ትምህርት ቤቶች ልዩ በጀትና ትኩረት ተሰጥቷቸው የአብነት ትምህርት በሌላቸው ገዳማት ደግሞ የአብነት ትምህርት ተከፍቶ
ተተኪ መምህራንና ሊቃውንት የሚፈሩበት መንገድ እንዲመቻች።
ሰ/ የቅርሶችና የታሪክ ማኅደሮች ጥበቃን በተመለከተ ፦ አባቶቻችን በደምና በአጥንታቸው ያቆዩልን የብራና መጻሕፍትና ንዋያተ ቅድሳት እንዳይመዘበሩ፣ በዘመናዊ መንገድ ተመዝግበውና ተጠግነው በገዳማት ሙዚየሞች እንዲጠበቁ የጥበቃ መመሪያ ተግባራዊ እንዲሆንና አቅም ለሌላቸው ገዳማት ድጋፍ አድራጊዎችን በማስተባበር ቅርሶቹን የሚጠብቁበት ሙዜም እንዲዘጋጅላቸው።
ረ/ የአረንጓዴ ቅርስ (የደኖች) ሐልዎት፦ መናንያን ለጸሎትና ለተጋድሎ የሚገለገሉባቸው የገዳማት አጸዶችና ደኖች፣ የቤተ ክርስቲያን የቃል ኪዳን ምልክቶች እና ሀገር በቀል ዘመናትን ያስቆጠሩ አጸዶች የሚገኙባቸው በመሆናቸው፤ የደን ድንበራቸው ተከብሮ ከማንኛውም ንክኪና ወረራ በሕግ እንዲጠበቁ እንዲደረግ።
ሠ/ የገዳማውያንን ፍልሰት መግታት በተመለከተ ፦ መናንያን በኑሮ መቸገር በትምህርት ፍለጋ እና በሕክምና እጦት ምክንያት ገዳማቸውን ትተው ወደ ከተማ እንዳይሰደዱ፣ በገዳማት ውስጥ በቂ የጤና አገልግሎት የመንፈሳዊ ትምህርት ቤት እና የመንፈሳዊ ተጋድሎ ምቾት የሚገኝበት ሥርዓት ተዘርግቶ “የገዳማዊ ሕይወትን ለትውልድ ማስቀጠል እንዲቻል የሚሉ ሐሳቦችን ጉባኤው ተወያይቶ ሐሳብ ከሰጠ በኋላ፤ ከዚህ የሚከተለውን ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቷል
እኛ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የገዳማት አበምኔቶችና እመምኔቶች፤ የገዳማውያን ፋና በሆነው በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፈቃድ፤
በብፁዕ ወቅዱስ አባታችን አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኩስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በ2017 ዓመተ ምህረት ለ2018 የበጀት ዓመት በሥራ ላይ እንድናውለው በሰጡን አባታዊ መመርያ መሠረት፤
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ
ይህንን ጉባኤ ሲከፍቱ በሰጡት አባታዊ መመሪያና ወቅታዊ ጥሪ መሠረት፤ በገዳማቶቻችን የሚታዩ ድክመቶችን አስወግደን የቀደመውን ክብርና ልዕልና ለመመለስ፤ የሚከተሉትን ባለ ስምንት አንኳር ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተናል።
፩. መንፈሳዊ ተጋድሎን ስለማጽናት፦
ጌታችን ወደ ገዳም ፈቀቅ ብሎ እንደጸለየ እኛም አርአያነቱን በመከተል፣ ገዳማቶቻችን የጾምና የጸሎት ማዕከልነታቸው ጸንቶ እንዲኖር፣ ስለ ዓለም ሰላምና ስለ ቤተ ክርስቲያን አንድነት ያለማቋረጥ ለመጋደል ቃል እንገባለን።
፪. የአብነት ትምህርትንና ሊቃውንትን ስለማፍራት፦
ገዳማት የጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን የዕውቀት መፍለቂያ እንደመሆናቸው መጠን፣ የአብነት ትምህርት ቤቶችን በማጠናከርና መምህራንን በመደገፍ፣ ለነገዋ ቤተ ክርስቲያን ተተኪ ሊቃውንትንና መምህራንን ለማፍራት ቃል እንገባለን።
፫. ትውልድን በሥነ ምግባር ስለመቅረጽ፦
በዘመኑ የዓለማዊነት ተግዳሮት ውስጥ ለወደቀው ትውልድ ገዳማቶቻችን የመንፈሳዊነትና የሥነ ምግባር ተምሳሌት እንዲሆኑ በማድረግ፣ በፍቅረ ቤተ ክርስቲያን የታነጸ ዜጋን ለመቅረጽ ቃል እንገባለን።
፬. በልማት ሥራ ራስን ስለመቻል፦
በገዳማቶቻችን ያለውን ሰፊ መሬትና የተፈጥሮ ጸጋ በመጠቀም፣ በግብርናና በልዩ ልዩ የልማት ዘርፎች ተሰማርተን፣ ገዳማችንን ከኢኮኖሚ ጥገኝነት አላቀን ለሌሎችም ተርፈን ለመገኘት ቃል እንገባለን።
፭. የገዳማውያንን ፍልሰት ስለመግታት፦
አስፈላጊውን የኑሮና የሥራ ሁኔታ በገዳማት ውስጥ በማመቻቸት፣ ገዳማውያን በአካላዊና በመንፈሳዊ ምክንያት ወደ ከተማ የሚያደርጉትን ፍልሰት በማቆም በገዳማቸው እንዲጸኑ ለማድረግ ቃል እንገባለን።
፮. የሥነ ጥበብና የታሪክ ቅርሶችን ስለመጠበቅ፦
አባቶቻችን በደምና በአጥንታቸው ጠብቀው ያቆዩልንን የብራና መጻሕፍት፣ የጥበብ ሥራዎችና የኪነ ሕንጻ ቅርሶች እንዳይጠፉና እንዳይዘረፉ በንቃት ለመጠበቅና ለትውልድ ለማስተላለፍ ቃል እንገባለን።
፯. ተቋማዊ አንድነትንና ታዛዥነትን ስለማጽናት፦
ከጠቅላይ ቤተ ክህነት የገዳማት አስተዳደር መምሪያ ጋር በመተባበርና በጋራ በመመካከር፣ የገዳማትን አንድነትና ተቋማዊ አሠራር ለማጠናከርና ለበላይ አካል መመሪያዎች ተገዢ ለመሆን ቃል እንገባለን።
፰. የምጽዋትና የርኅራኄ ማዕከል ስለመሆን፦
ጌታችን የተራቡትን እንዳበላ ሁሉ፣ እኛም በልማታችን በረከት የታመሙትን ለመጠየቅ፣ የተራቡትን ለመመገብና ለተቸገሩት ሁሉ የርኅራኄ መጠጊያ ሆነን ለመገኘት ቃል እንገባለን።
ሚያዝያ 23 ቀን 2018 ዓ.ም
መንበረ ፓትርያርክ አዲስ አበባ ኢትዮጵያ