“ኦርቶዶክሳዊ እውነትን በአፍ በመጽሐፍ የምትገልጹ የምናፍራችሁና የምናከብራችሁ ሊቃውንት እንዳለችሁ ስለምናምን በዚህ ጉባኤ ብዙ እንጠብቃለን “። ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ

“ኦርቶዶክሳዊ እውነትን በአፍ በመጽሐፍ የምትገልጹ #የምናፍራችሁና #የምናከብራችሁ ሊቃውንት እንዳለችሁ ስለምናምን በዚህ ጉባኤ ብዙ እንጠብቃለን በማለት ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ ተናገሩ።
ብፁዕነታቸው ይህንን ያሉት በዛሬ ዕለት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሊቃውንት ጉባኤ በኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር አዳራሽ ባዘጋጀው የሊቃውንት የምክክር ጉባኤ ላይ ነው።
በጉባኤው ላይ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባና ሀዲያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ክቡር ንቡረ ዕድ ኤልያስ አብርሃ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የመንፈሳዊ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ መልአከ ምሕረት አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ የመንበረ ፓትርያርክና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ ሐላፊዎች፣
ሊቀ ኅሩያን ይልማ ጌታሁን የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ዋና ጸሐፊ ፣ የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲና የቅዱስ ጳውሎስ ኮሌጅ መምህራን ፣ ከገዳማትና አድባራት የተወጣጡ የጉባኤ መምህራን ተገኝተዋል።
የምክክር ገባኤው በብፁዕነታቸው ጸሎና ቡራኬ የተጀመረ ሲሆን የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት በመልአከ ፀሐይ አባ ኃይለ መለኮት የሀገረ ስብከቱ የሊቃውነት ጉባኤ ሰብሳቢ አማካኝነት ቀርቧል።
በመልእክታቸውን “ደገኛዋ ሥርዓት እንዳትጠፋ ጠብቁ” የሚለውን ቃል መነሻ ያደረጉ ሲሆን የጉባኤው ዓላማ የአበውን ሃይማኖት እንደትናቱ ጠብቁ ለነገ ትውልድ በተጠናከረ መልኩ ማስተላላፍ እንዲቻል ምክክር ማድረግ የሚል መሆኑን ገልጸዋል።
ሥርዐት ሃይማኖትን ያጸናል ሃየማኖት በሥርዓት ይገለጣል ነውና በተለይም በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ላይ የሚስተዋሉ ከሥርዓት የወጡ አንዳንድ ድርጊቶች ወደ ቀደመው ሥርዓታቸውን እንዲመለሱ በእጅጉ መሥራት አለብን ለዚህም ይህ ጉባኤ ድርሻው ሰፊ ነው ብለዋል።
በሥርዐተ ማኅሌት የሚስተዋሉ ከሥርዐት የውጡ ድርጊቶችን “አባቶች እያዘኑ ወጣቶች እየተዝናኑ ማድር የሚመስሉ ከሥርዐት ውጭ እየተፈጸሙ ያሉ ችግሮችን በጥብዐትና በትምህርት ወደ ልኩ መመለስ አለብን ብለዋል።
ጉባኤው የአንድ ቀን ሲሆን ሁለት ትምህርታዊ ጥናታዊ ጽሑፎች እንደሚቀርቡ አስታውሰው ውይይት እንደሚደረግባቸው ገልጸዋል።
ይህ ጉባኤ እንዲከናወን መምሪያ ከመስጠትና ከመፍቀድ ጀምሮ ድርሻቸውን ለተወጡ ብፁዕነታቸውንና ክቡር ዋና ሥራ አስኪያጁ እናመሰግናለን ብለዋል።
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ ባስተላላፉት አባታዊ መልእክት ጠቃሽና ነቃሽ በበዛበት በዚህ ዘመን በዝምታና በአባትነት ሞገስ የምታስተምሩ ሊቃውንት እንዳለችሁና ከዚህም በላይ ኦርቶዶክሳዊ እውነትን በአፍ በመጽሐፍ የምትገልጹ የምናፍራችሁና የምናከብራችሁ ሊቃውንት እንዳለችሁ ስለምናምን ብዙ የሚጠበቅበት ጉባኤ ነው ብለዋል።
የዘመኑን አስቸጋሪነት ተግዳሮተ ብዙ መሆኑን የገለጹት ብፁዕነታቸው “ለመልካም ነገር እንኳ ዝም አሉኩ” የሚለው ቃል አሁናዊ እውነት ጋር ሲነጻጸር ተገቢነት አይኖረውም።
ስለሆነም በበረታ አንደበት በተገለጠ ሕይወትና ሕያው ዓላማን በጠበቀ መልኩ ዘመኑን በመዋጀት በትጋት ማስተማር ይገባል ብለዋል።
በዚህም የሀገረ ስብከቱ ሊቀውንት ጉባኤ ሰብሳቢ መልአከ ፀሐይ አባ ኃይለ መለኮት ይኄይስ ከክፍሉ ሠራተኞችን ጋር በመሆን ጥሩ እንቅስቃሴ እየጨመረ ዳረጉ መሆኑን አስታውሰው ምስጋና አቅርበዋል።
አክውም የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ጉባኤ እንዲዘጋጅ ለበኩሉን ድርሻ ስለተወጣና በተለያዩ ጉዳዮችንም አብሮነቱን ስለሚያሳያን እናመሰግናለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ የሊቃውንት ጉባኤ በሁሉም አህጉረ ስብከት መዋቅሩን ጠብቆ እንዲደራጅ ውሳኔ ባለፈው ዓመት ማሳለፉ የሚታወስ ነው።
ይህን መነሻ በማድረግ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ከተመደቡ በኋላ በአዲስ መልክ ተግባራዊ ያደረጉት የሀገረ ስብከቱ ሊቃውንት ጉባኤ መዋቅራዊ አደረጃጀት ተጠቃሽ ነው።