ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የሚሰጡ የአብነት ትምህርት ጉባኤ ቤቶች የአጥቢያው ምእመናን ልጆች ላይ ትልቅ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው አሳሰቡ።
ኢኦተቤ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ
ሰኔ ፮/፳፻፲፰ ዓ/ም
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የሚሰጡ የአብነት ትምህርቶት ጉባኤ ቤቶች የአጥቢያው ምእመናን ልጆች ላይ ትልቅ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው አሳሰቡ።
ብፁዕነታቸው ይህንን ያሉት በትናንትናው ዕለት በአስኮ ደብረ ገነት ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ነው።
በመርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባና ሀዲያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ መልአከ ስብሐት ዐቢይ ዘለቀ የብፁዕነታቸው ልዩ ጸሐፊና ፕሮቶኮል፣ መልአከ ገነት ልሳነወርቅ ተስፋ የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ፣ መልአከ ምሕረት አበበ የሺንጉሥ የካቴድራሉ አስተዳዳሪ፣ የካቴድራሉ የአስተዳዳር ሠራተኞችና ሊቃውንት ተገኝተዋል።
ብፁዕነታቸው ካቴድራሉ የቤተ ክርስቲያን ተልእኮን መሠረት በማድረግ እየሠራቸው የሚገኙትን አዲስ ቤተ ልሔም (B+1) ግንባታ እንዲሁም B+1+G+3 የቢሮና የተለያዩ መንፈሳዊ አገልግሎት የሚሰጡ ክፍሎችን የያዘ ሕንጻን ጎብኝተዋል።
የካቴድራሉ አስተዳዳሪ መልአከ ምሕረት አበበ ቤተ ልሔሙ በ2015 ዓ/ም መሠረት ድንጋይ የተቀመጠ ቢሆንም ሳይሳራ በመቆየቱ በ9 ወራት ውስጥ እዚህ ለማድረስ ተችሏል ብለዋል።
አክለውም ሙሉ ወጪው በአንድ ኦርቶዶክሳዊ የሚሸፈን መሆኑን ያስታወሱት አስተዳዳሪው ግንባታው የቤተ ክርስቲያን ሥርዓትና ዘመኑን የሚጠይቀውን የአገልግሎት ምቹነትን መሠረት በማድረግ የተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም አስተዳዳሪው ከጸሐፊው መጋቤ ምሥጢር ፍቃዱ አረጋ ጋር ወደዚህ ካቴድራል ከተመደቡ 11 ወራትን ያስቆጠሩ መሆናቸውን ገልጸው ከዓመታት በፊት ተጀምሮ የነበረውና መሠረት ተጥሎ ያገኙትን G+3 ሕንፃ በአጭር ጊዜ ውስጥ አሁን የሚታይበት ደረጃ ለማድረስ ተችሏል ብለዋል።
ሕንጻው የአስተዳዳር ቢሮዎች ፣ አዳራሽ ፣ የጸበል መጠመቂያ በርካታ ክፍሎች ያለውና ሌሎችን መሰል አገልግሎት የሚሰጡበት እንደሆነ ገልጸዋል።
ብፁዕዕነታቸው ባዩት መልካም ሥራ ተደንቀው በቀጣይም ካቴድሬሉን የሚመጥን በርካታ ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
በመቀጠልም ብፁዕነታቸው በካቴድራሉ የሚሰጡ የዜማ የቅኔ የቅዳሴ እንዲሁም የንባብ የአብነት ትምህርት ጉባኤ ቤቶችን ተመልክተዋል።
በተለይም ከ100ዐ በላይ ደቀ መዛሙር የሚገኙበትን የወላዴ አእላፍ ነቅዐ ጥበብ ያለው የንባብ፣ የዜማና የቅዳሴ ጉባኤ ቤት በእጅጉ በመደነቅ መምህሩን አመስግነዋል።
ጉባኤ ቤቱ በዋናነት ትኩረት የሚያደርገው የአካባቢውን ምእመናን ልጆች ወይም ወደ ሌላ ሀገር ሄደው መመር ያልቻሉትንና ያልተመቻቸላቸውን እንዲሁም በብዙ አቻ ግፊቶች የሚፈተኑትን የከተማ ልጆችን የቤተ ክርስቲያን ሀብት የማድረግ ተልእኮን በመፈጸም የሚገኝ በመሆኑ ለሌሎች አርአያ ነው ብለዋል።
ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችን የውስጥ ውበቷ የውጭ ጌጧ የአብነት ትምህርት ቤት መሆኑን አስታውሰው በክፍለ ሀገርና በገጠር የሚሰጠውን የአብነት ትምህርት ወደ ከተማው በሚመጥንና ዘመኑን በዋጀ መልኩ መስጠት ይኖርብናል።
በከተሞች ለሚገኙ ልጆች መስጠት ካልተቻለ በነገ ትውልድ ልብ ላይ የቤተ ክርስቲያናችንን የዜማና የአገልግሎት ሀብት መሳልና ማስቀመጥ አይቻልም። ስለሆነም ይህንን ሐሳብ ማእከል በማድረግ #የሚያዜሙ_ዶክተሮች፣ #የሚቀድሱ ኢንጂነሮች፣ #ማኅሌት_የሚቆሙ_ዳኞች እና በጸገ የተቀበሉትን በጸጋ የሚሰጡ ካህናት እንዲበዙ አጠናክረን ልቀጥል ይገባል ብለዋል።
በመሆኑም የደብሩ አስተዳዳር የሰውና የራስ አገዝ ልማቶች ላይ በተናበበና ተልእኮን መሠረት በማደረግ ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአስኮ ደብረ ገነት ቅዱስ ገብርኤል አስተዳዳሪ መልአከ ምሕረት አበበ የሺጌታና ዋና ጸሐፊ መጋቤ ምሥጢር ፍቃዱ አረጋ ቀደም ሲል በካቴድራሉ ተፈጥሮ የነበረውን የአስተዳደርና የተግባቦት ችግር በመቅረፋቸው ምክንያት ጥር 3/2018 ዓ/ም ከማኅበረ ካህናቱ የምስጋና ሽልማት እንደተበረከታላቸው የሚታወስ ነው።
ካቴድራሉ በ1969 ዓ/ም እንደተመሠረተ የሚነገር ሲሆን የመጋቤ እልላፍ ነቅዐ ጥበብ ያለው ጉባኤ ቤት ደግሞ በ2000 ዓ/ም ጀምሮ በርካታ ደቀ መዛሙርት የተማሩበት ጉባኤ ቤት እንደሆነ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
