በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁና በብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊው የተመራ የቤተክርስቲያናችን የልኡክ ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሰላም ሚኒስቴርና ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያየ።
ኢኦተቤ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ
ግንቦት 27 ቀን 2018 ዓ.
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት አንዳንድ ወረዳዎች በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት በኦርቶዶክሳውያን ወገኖቻችን ላይ የደረሰውን ሕልፈተ ሕይወትና የቤተ ክርስቲያን መቃጠልን በማስመልከት የተሰማትን ጥልቅ ኀዘን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አማካኝነት ከገለጸች በኋላ ቋሚ ሲኖዶስ በጉዳዩ ዙሪያ ጥልቅ ውይይት በማድረግ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣
የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና በብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የተመራ ከፍተኛ የቤተክርስቲያናችን የልዑካን ቡድን ከሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መሀመድ እድሪስ፣
ከሚኒስትር ዲኤታው ከዶ/ር ኸይረዲን ተዘራና ከሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ ወቅት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስና ብፁዕ አቡነ ዲዮስሮስ በምሥራቅ አርሲ በአሰኮ፣ በሺርካ፣ በሆንቆሎ ዋቤ ወረዳዎች በኦርቶዶክሳውያን ወገኖቻችን ላይ በደረሰው የሕይወት ጉዳት እና በጥንታዊው ቤተ ክርስቲያን መቃጠል እጅግ ማዘናቸውን ገልጸው መንግሥት የችግሩን ምንጭ አጣርቶ ዘላቂ መፍትሔ እንዲፈልግና በአካባቢውም አስተማማኝ ሰላምን እንዲያሰፍን አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።
አያይዘውም በአሁኑ ወቅት በችግሩ ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቀያቸው የሚመለሱበትና መልሰው የሚቋቋሙበት ሥራ እንዲሠራ፣ ወንጀሉን የፈጸሙ ሰዎችም ለፍርድ ቀርበው
ቅጣታቸውን እንዲያገኙ እንዲደረግ ጠይቀዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የምሥራቅ አርሲና የጅግጅጋ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሀገረ ስብከታቸው የተከሰተውን ችግር በማስመልከት ዝርዝር መረጃዎችን በቊጥራዊ ማስረጃዎች አስደግፈው አቅርበዋል።
የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መሐመድ እድሪስ በበኩላቸው
በተፈጠረው ችግር እጅግ በጣም ማዘናቸውን ገልጸው በመንግሥት በኩል በአስቸኳይ አጣሪ ቡድን ተቋቁም ወደ ስፍራው ተልኳል ካሉ በኋላ የአጣሪ ቡድኑን ሪፖርት መሠረት በማድረግም አስፈላጊው እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።
ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ብፁዓን አባቶቻችን በኦሮሚያ ፕ/ት ጽ/ቤት ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ከብልጽግና ፓርቲ ድ/ ቤት አመራሮች ጋር ዝርዝር ውይይት አድርገዋል። በውይይቱ ወቅት የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንደገለጹት የክልሉ መንግሥት በሥፍራው የተከሰተውን ችግር ለመቆጣጠርና ሊከሰት ይችል የነበረውን ተጨማሪ አደጋን ለመከላከል የሚያስችል ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረጉን፣ በአሁኑ ወቅትም ወደ ሥፍራው አጣሪ ቡድን መላኩንና የማጣራት ውጤቱን ተከትሎም አጥፊዎችን ለሕግ የማቅረቡ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው ቤተክርስቲያኗ ምዕመናንን ለማጽናናትና ድጋፍ ለማድረግ በምታደርገው ጥረት ሁሉ የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደረግላት ገልጸዋል።
በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ እና የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍ፣ወደ ቀያቸው ለመመለስ እንዲሁም የተቃጠለውን ቤተ ክርስቲያን መልሶ ለመገንባት እና በአካባቢው ዳግመኛ መሰል ችግር እንዳይፈጠር ለማድረግ የሚያስችል ሥራ በተጠናከረ መልኩ እንደሚያከናውኑ ከልዑካን ቡድኑ ጋር ባደረጉት የማጠቃለያ ውይይት ገልጸዋል።
©ኢኦተቤ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ
