በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁና በብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊው የሚመራ የቤተክርስቲያናችን ልኡክ አርሲ አቦምሳ ወረዳ ተገኝቶ ምዕመናንን አጽናና ጊዜያዊ ርዳታም አበረከተ።
ሰኔ 4 ቀን 2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ በአርሲ ዞን አንዳንድ ወረዳዎች የተከሰተውን ችግር ተከትሎ በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁና በብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊው የሚመራ የቤተክርስቲያናችን ልዑክ በሥፍራው በመገኘት ተጎጂዎችን እንዲያጽናና ጊዜያዊ ርዳታም እንዲያደርግ
ያስተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ዛሬ ማለዳ ወደ አርሲ ዞን አቦምሳ ወረዳ በመጓዝ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች አጽናንቷል፤ ጊዜያዊ ርዳታም አበርክቷል።
በአቦምሳ ወረዳ የትንሣኤ ብርሃን ደብረ ገነት መድኀኔዓለም ቤተክርስቲያን በመገኘት ተጎጂ ኦርቶዶክሳዊያንን ያጽናኑት
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክት ቅድስት ቤተክርስቲያን በበኦርቶዶክሳዊያን ልጆቿ ላይ በደረሰው ጉዳት እጅግ በጣም ማዘኗን ገልጸው እግዚአብሔር አምላክ ለሞቱት ወገኖቻችን መንግስተሰማያትን እንዲያወርስልን፣ለቤተሰቦቻቸው መጽናናት እንዲያድልልን የዘወትር ጸሎታችን ነው።በርቱ፣ጠንክሩ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን ብለዋል።
አያይዘውም ቋሚ ሲኖዶስ በአካል ተገኝቶ እናንተን ለማጽናናትና ጊዜያዊ ድጋፍ ለማድረግ በመካከላችሁ ተገኝተናል ያሉት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታትና የተቃጠለውን ቤተክርስቲያን ለመሥራት የሚያስቼል አቢይ ኮሚቴ በጠቅላይ ቤተክህነት ተሰይሞ ወደ ሥራ ገብቷል ብለዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት ብፁዕ አቡነ ጎርጎሬዎስ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክት ቅድስት ቤተክርስቲያን በተከሰተው ችግር ጥልቅ ኀዘን የተሰማት መሆኑን ገልጸው ምዕመናን በሃይማኖታቸው እንዲጸኑ፣በፈተና ሁሉ እንዲታገሱ አደራ ካሉ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ ኀዘንተኞችን እንዲያጽናና ከዳግም ኀዘን እንዲሰውርልን ዘወትር እንጸልያለን በማለት ቃለ ምዕዳንና ቃለ ቡራኬ ሰጥተዋል።
በመጨረሻም ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ለተፈናቀሉ ወገኖች የተዘጋጀውን ርዳታ ለሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ለብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ አስረክበዋል።በዚሁ ጊዜ የአቦምሳ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎችና አባ ገዳዎች ብፁዓን አባቶችን እንኳን ደህና መጣችሁልን በማለት በሀገሩ ባህል መሰረት የሰንጋ ስጦታ ካበረከቱ በኋላ የደረሰውን ጉዳት በመኮነን ሕዝቡ በስምምነት፣
በአንድነትና በመቻል የኖረና ወደፊትም የሚኖር ሕዝበብ መሆኑን ጠቅሰው የተፈጠረውን ችግር ሃይማኖታዊ መልክ ለማስያዝ የሚደረገው ጥረት ተገቢነት የሌለው ነው ብለዋል።ለብፁዓን አባቶች የተበረከተው የሰንጋ ስጦታም ለተፈናቀሉ ወገኖች እንዲደርስ ተደርጎ የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል።
©የኢኦተቤ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ
