የታሪካዊው የምሁር ኢየሱስ ገዳም አዲሱ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቤት ተከበረ
የምሁር ኢየሱስ ገዳም በጉራጌ ዞን፣ በምሁር አክሊል ወረዳ የሚገኝ ከአዲስ አበባ በ207 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን ጥንታዊና ታሪካዊ ገዳም ነው። ገዳሙ የተመሰረተው በ14ኛው ክፍለ ዘመን በታላቁ አባት በአቡነ ዜና ማርቆስ እንደሆነ የገዳሙ ታሪክ ይነግረናል።
ገዳሙ የከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ማዕከል በመሆን፣ጥንታዊና ብርቅዬ የብራና መጻሕፍትና ንዋያተ ቅድሳትን ጠብቆ በማቆየት፣እንዲሁም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ያላቸው ሊቃውንትን በማፍራት ይታወቃል።በተለይም በውስጡ የሚገኘውና እጅግ ተአምረኛ እንደሆነ የሚነገረው “የምሁር ኢየሱስ” ስዕለ አድኖ ለብዙዎች የፈውስና የበረከት ምንጭ ሆኖ ቆይቷል።
ገዳሙ በቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ ውስጥ ስመ ጥር የሆነ የጉባኤ ቤት መገኛም ነው። በተለይም በቅኔ፣ በዜማና በመጻሕፍት ትርጓሜ ጥልቅ እውቀት ያላቸውን ሊቃውንት በማፍራት፣በመላው ኢትዮጵያ ለሚገኙ አድባራትና ገዳማት ባለ ውለታም ነው።
ገዳሙ ከመንፈሳዊ ሥራው ባሻገር ለኅበረተሰቡ አገልግሎቶች የሚውሉ በሐዋርያት ከተማ ውስጥ የመዋዕለ-ሕጻናት ትምህርት ቤት፣ የእንግዳ መቀበያና ማረፍያ ቤት፣ በገዳሙ ግቢ ውስጥ ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ት/ቤት፣ በወልቂጤ ከተማ ደግሞ ከመዋዕለ-ሕጻናት እስከ 10ኛ ክፍል ባለሶስት ፎቅ ሕንጻ ት/ቤት አስገንብቶ በማስተማር የአካባቢውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ እያደረገ ነው፡፡
በገዳሙ የተለያዩ ክብረ በዓላት የሚከበሩ ሲሆን በዋናነት ታህሳስ ሶስት የአቡነ ዜናማርቆስ የእረፍት ቀን መታሰቢያ፣አብይ ፆም አጋማሽ(ደብረዘይት) ልዩ የበገና ምሽት፣ በግንቦት ወር ውስጥ አብይ ፆም በተፈታ አርባኛው ቀን(የእርገት በዓል) ሲሆኑ በእነዚህ በዓላት ወቅት ቁጥሩ በዛ ያለ ከተለያዩ የአካባቢው፣ የሃገሪቱ ክፍሎች እና ከሃገር ውጪ በሚመጡ ቱሪስቶች በድምቀት ይከበራል።
በዛሬው ዕለት ደግሞ ይህንን ታሪካዊ ገዳም ከነበረበት የቆየ ህንጻ ቤተ ክርስቲያን ወደ ዘመናዊና ሰፊ ቤተ ክርስቲያን ለመቀየር በርካታ ምእመናን፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚኖሩ የገዳሙ ልጆችና በጎ አድራጊዎች በገንዘባቸው፣ በጉልበታቸውና በዕውቀታቸው ደክመዋል። ሚያዚያ 24 ቀንም ይህ ድካም ፍሬ አፍርቶ የገዳሙ አዲሱ ቤተ ክርስቲያን የቅዳሴ ቤት (ምረቃ) በታላቅ ድምቀት ተከብሯል።
በዕለቱ በተለያየ ልብሰ ተኬህኖ በለበሱ ካህናትና ሰንበት ተማሪዎች በተጨማሪ ከገዳሙ አቅራቢያ ከሚገኘው ከሐዋርያት ከተማ ጀምሮ በባንዲራ የተዋበ አካባቢ፣ የሚጥለውን ዝናብና ንፋስ ተቋቁመው ገዳሙ ድረስ በተለያዩ መኪኖች ያጀቡ የዞኑ ፖሊሶች፣ ሞተር ሳይክሎችና ባጃጆች እንዲሁም በየራሳቸው ባህልና ወግ የሚዘምሩ ነዋሪዎችን በዓሉን ልዩ ድምቀት ሰጥተውት ውለዋል።
በክብረ በዓሉ ላይ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣የገዳማት አስተዳዳሪዎች ፣የገዳሙ መነኮሳትና አባቶች፣ጥሪ የተደረገላቸው የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ሐላፊዎች፣እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ ምእመናን በስፍራው ተገኝተው ይህንን ታሪካዊ በዓል በዝማሬና በደስታ አክብረዋል።
በተጨማሪም የብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ካልኣይ የመታሰቢያ ሐውልት እና ቤተ መዘክር በገዳሙ ግቢ ተመርቋል።
ዘገባ ©eotc tv
