“በአርሲ የተቃጠለውን ቤተ ክርስቲያን እንሠራልን” የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች
ኢኦተቤ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ
ሰኔ ፪/፳፻፲፰ ዓ/ም
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች በምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት በተፈጠረው የኦርቶዶክሳውያን ግድያና የቤተ ክርስቲያን መቃጠል ኀዘናቸውን ገልጸው በብፁዕነታቸውን መመሪያ ሰጪነት የተቃጠለውን ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት ፈቃደኛ መሆናቸውን አሳወቁ።
አስተዳዳሪዎቹ ይህንን ያሉት በዛሬው ዕለት በተካሄደው የጋራ ስብሰባ ለጽድቅና ለመንግሥተ ሰማይ ዓላማ የሚሰበሰብ የቤተ ክርስቲያን ገቢ አስመልክቶ ውይይትና ምክክር በተደረገበት ስብሰባ ላይ ነው።
በስብሰባው ላይ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና ሸገር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባና ሀዲያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ መልአከ ምሕረት አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ መጋቤ ትፍስሕት ሙሉጌታ ቸርነት የሀገረ ስብከቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ፣ የሀገረ ስብከቱ የዋና ዋና ክፍል ሐላፊዎች ፣ የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አክኪያጆች፣ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነትና የአድባራት የሒሳብ ሹሞች ተገኝተዋል።
የስብሰባው ጉዳይ እውነተኞች ምዕመናን የሰጡትንና በተለያዩ የሰዋዊና ቁሳዊ ልማት ምክንያት ለቤተ ክርስቲያን ገቢ ያደረጉትን ገንዘብ ሕግና አሠራርን በመጠበቅ ቤተ ክርስቲያን ለተመሠረተችበት ሕያው ዓላማና መንፈሳዊ ሥራ ላይ አገልግሎት ላይ ይውል ዘንድ ምክክር ለማድረግ የተጠራ ስብሰባ እንደሆነ ተገልጿል።
በጉባኤውም በሀገረ ስብከቱ የሒሳብና በጀት ዋና ክፍል ሐላፊ ሊቀ ኅሩያን አስናቀ ሸዋየ አጭር ሪፖርት የቀረበ ሲሆን በዚህ መነሻነትም ከሀገረ ስብከቱ ጀምሮ እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የያሉ ተሳታፊዎች ሐሳብና አስተያየት ሰጥተዋል።
አስተያያት ሰጪዎቹ እንዳሉት የቤተ ክርስቲያን ገቢዎችን ሕግና አሠራርን ጠብቆ ለተገቢው ዓላማ ማዋል፣ ተቋማዊ ተናብቦትና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባለችበት ሁሉ የተፈጠሩ ችግሮችና ቁስሎችን የጋራ በማድረግ ከግል ፍላጎትና ሐሳብ ይልቅ ቤተ ክርስቲያንን በማስቀድም መሥራት በሚሉ ጉዳዮች ላይ አስተያያቶች ቀርበዋል።
በተለይም በሀገረ ስብከቱ ደረጃ እየተለመዱ የመጡ ዘመኑን ያነበቡና ችግርን በችግር ሳይሆን በመፍትሔ እናክማቸው በሚል መንገድ የተጀመሩ የውስጥ አሠራሮችና ተጨባጥ የሆኑ የራስ አገዝ ልማቶች በእጅጉ የሚበረታቱና የሚያስመሰግኑ መሆናቸውን ከከፍተኛ አድናቆት ጋር ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስና መልአከ ምሕረት አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ እንዲሁም የሀገረ ስብከቱን የሥራ ሐላፊዎች አመስግነዋል።
በሌላ በኩል አስተዳዳሪዎቹ #በገጠሪቱ_ያለችው_ቤተ_ክርስቲያን_ስታነባ _ያመናል ፤ #ቁስሏም_ይጠዘጥዘናል፤ በመሆኑም በሰሙኑ በምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት የተቃጠለውን ቤተ ክርስቲያን በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ መመሪያ ሰጪነት ተባብረን ለመሥራት ፈቃደኛ መሆናችን እንገልጻለን ብለዋል።
የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ምሕረት አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ በበኩላቸው በብፁዕነታቸው የሚመራው ሀገረ ስብከት ነገን በማሰብ ዛሬ ላይ አቅዶ እየሠራ መሆኑን በማስታወስ በዚህም የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና የሥራ ሐላፊዎች ድርሻቸው ሰፊ ነው ብለዋል።
አክለውም የተቀበልነው ሕያው ተልእኮ ቤተ ክርስቲያንን የመጠበቅ ብቻ ሳይሆን በታማኝነት በመንፈሳዊ ትርፍ ዘመኑን በዋጀ መልኩ ለቀጣዩ ትውልድ በክብር የማስተላላፍ ድርሻ አለብን ለዚህ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ገቢ በአግባቡ መጠበቅና ቤተ ክርስቲያን ጠቀም ሥራዎችን በመሥራት መሆን አለበት ብለዋል።
የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የተሰጠንን ሐላፊነት በአግባቡ መተርጎምና ለቤተ ክርስቲያን ብልጫ ላለው አገልግሎት ማውል ይኖርብናል ያሉ ሲሆን በተለይም አሠራራችን ዘመኑን የዋጀ፣ ለምእመናን ቅርብ የሆነና ዘላቂ ለውጥ ላይ መሠረት ያደረገ መሆን አለበት ብለዋል።
ቀጥለውም #የቤተ_ክርስቲያን_ገቢ_ከምእመናን_መቀነት_እስከ_ጠቅላይ_ቤተ_ክህነት የሚደርስ መስመር ያለው ተቋማዊ አሠራር ያለው በመሆኑ አልቅሳ አንብታ ለሐጢአት ሥርየት ብላ የምትሰጥውን የአንዲት ምእመን ስጦታና ዛሬን ለነገ እናሻግር በሚል መርሕ የተሠሩ የራስ አገዝ ልማቶች ገቢዎች በሰዓቱ መሰብሰብና ለታለመው ዓላማ ማዋል ይገባናል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሁሉም አህጉረ ስብከት ደጋፊ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና መጋቢ የሁሉ መጠጊያ እንደሆነ የገለጹት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ሳዊሮስ ሊቀ ጳጳስ በቤተ ክርስቲያናችን ተቋማዊ ህልውና እና ተልእኮ ማስፈጸም ረገድ ድርሻው ሰፊ ነው ብለዋል።
በመሆኑም የሰው ልማት ላይና የተቋማት ዕድገት ላይ በእጅጉ መሥራት እንደሚገባው የተጠቆሙት ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የሚሠሩ ወንጌል የሚስፋፋባቸው፣ የገጠር አብያተ ክርስቲያናት የሚረዱበት እና ራሳቸውን ያልቻሉ አህጉረ ስብከት የሚደጎሙበት ሁሉን አቀፍ የራስ አገዝ ልማቶች ላይ በማገዝ ትልቁን ድርሻ እንደሚወጣ ተስፋቸውን ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በተለያዩ አህጉረ ስብከት በምእመናንና በአብያተ ክርስቲያናት ጉዳት ሲያጋጥም ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያዘው በፍጥነት ለችግር የሚደርስ ሀገረ ስብከት መሆኑ ይታወቃል።
በምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት ግንቦት 23/2018 ዓ/ም ጀምሮ በተፈጠረው ጥቃት ንጹሐን ምእመናን በግፍ እንደሞቱና ከመቶ ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረው የጠለታ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን እንደተቃጠለ የሚታወስ ነው ነው።
@የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ
