የለገዳዲ አንቀጸ ምሕረት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ሕንጻ ቤተክርስቲያን በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ሳዊሮስ ቡራኬ ቅዳሴ ቤቱ ተከበረ።
ኢኦተቤ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ
ግንቦት ፳፪ ቀን ፳፻፲፰ ዓም
በሸገር ሀገረ ስብከት የለገዳዲ አንቀጸ ምሕረት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቡራኬ ተመረቀ፡፡ ቤተክርስቲያኑን ለማጠናቀቅ ዐሥራ ሁለት ዓመት የፈጀ ሲሆን፤ በወቅቱ የመሠረት ድጋዩ የተጣለው በ፳፻፮ ዓ.ም በሰሜን ሸዋ ሰላሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ሲሆን፤ ለምርቃት የበቃውም በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ዕለት በዕለት ክትትልና አመራር ሰጪነት መሆኑን የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ምሕረት ቀሲስ ያሬድ ሺፈራው ያስረዳሉ፡፡ የደብሩ አስተዳዳሪ አያይዘውም አዲሱ ሕንጻ ቤተክርስቲያን ተመርቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ እንዳስደሰታቸው ጠቁመው፤ በቤተክርስቲያን ሕሙማንን የሚፈውስ ታሪካዊ፣ በርካታ ገቢረ ተአምራት የሚፈጸምበት ጠበል የሚገኝ በመሆኑ ምእመናን ወደ ሥፍራው መጥተው እንዲጠመቁ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ እንደተናገሩት “ ግሩም የሆነ፣ በጣም ያማረ ሕንጻ ቤተክርስቱያን አንጻችኋል፡፡ በድካማችኁ፣ በገንዘባችኁ ዘመን ተሸጋሪ፣ ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፍ ታካዊ ቤተክርስቲያን እግዚአብሔር ፈቅዶላችሁ፣ እናንተ የምትገለገሉበት፣ እግዚአብሔር የሚመሰገንበት ሠርታችሁ በማጠናቀቃችሁ እንኳ ደስ አላችሁ” ብለዋል፡፡ ብፁዕነታቸው አያይዘውም ቤተክርስቲያኑን በፍቅር፣ በሰላም በአንድነት እንድታመሰገኑ ሲሉ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የሕንጻ አሠሪ ኮሚቴ ጸሐፊ አቶ ዐቢይ አበበ እንደተናገሩት ይህን ቤተክርስቲያን ስንሠራ ብዙ ነገር አሳልፈናል፤ እግዚአብሔር ለዛሬዋ ለምርቃት ቀን ስላበቃን እግዚአብሔርን እናመሰግናለን ብሏል፡፡
ሊቀ ብርሃናት መምህር ተክለ ብርሃን “እናንተ እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆናችሁ ቤተክርስቲያን ሠርታችኋል፤ በቅዱስ መጽሐፍ እንደተገለጸው ቤተመቅደስ ሥሩልኝ እኔም በውስጡ እድራለሁ ያለውን ቃል ተግባራዊ ያደረጋችሁ በመሆናችሁ፤ ዕድለኞች ናችሁ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም ለሕንጻ ቤተክርስቲያኑ ግንባታ በዕውቀታቸው፣ በጉልበታቸውና በገንዘባቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ምእመናን፣ በጎ አድራጊዎችና በሕንጻ አሠሪ ኮሚቴ ሲያገለግሉ የነበሩ ከብፁዕነታቸው እጅ ሽልማትና የምስጋና ምስክር ወረቀት ተቀብለዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ መልአከ ኃይል አባ አፈወርቅ ዮሐንስ የለገጣፎ ለገዳዲ እና ኩራ ጂዳ፣ የመልካ ኖኖ፣ የጉጂ ገፈርሳ ክፍላተ ከተማ እንዲሁም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ሊቀ ልሣናት በዳሳ ቶላ የኮዬ ፈጬና ገላን ክፍላተ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና በርካታ የአካባቢው ምእመናን ተገኝተዋል፡፡
©EOTC_TV
