ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ “በቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት በአጭር ጊዜ የተሠሩ ሥራዎች ለሁላችን ተስፋ ለቤተ ክርስቲያን የውጤታማነት ማሳያ ግርማ ናቸው” በማለት ገለጹ
ኢኦተቤ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ
ሚያዚያ ፲፭/፳፻፲፰ ዓ/ም
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ “በቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት በአጭር ጊዜ የተሠሩ ሥራዎች ለሁላችን ተስፋ ለቤተ ክርስቲያን የውጤታማነት ማሳያ ግርማ ናቸው” በማለት ገለጹ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት በዛሬው ዕለት በሰባት ወራት የሠራቸውን የቢሮ እድሳት ፣ በዓባይ ባንክ 4 ኪሎ ቅርጫፍ አማካኝነት የተዘጋጀው የዲጅታል ክፍያ ሥርዓት ማከናወኛ እንዲሁም የድርጅቱን እንቅስቃሴና አጠቃላይ ታሪካዊ ዳራ የቤቶችን ዓይነትና ዝርዝር በማን ከማን እንደተሰጡ የሚያገልጽ የድረ ገጽ ልማቶች የሚሉት በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።
በመሆኑም በቢሮው የምርቃት ሥነ ሥርዐቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ መገኛ ጽርሐ መንበረ ፓትርያርክ በመሄድ ከቅዱስ አባታችን ቡራኬ በመቀበል በሥራውም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለነበራቸው የምስጋና እና የእውቅና መርሐ ግብር ተከናውኗል።
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ሥዩማን እስክንድር ገብረ ክርስቶስ የተሠሩትን ሥራዎች አስመልክተው አጭርና ግልጽ ሪፖርት ለቅዱስ አባታችን አቅርበዋል።
በሪፖርታቸውም የተሠሩት ሥራዎችን በመርዘር አስተውሰው ለዚህ መልካም ሥራ በመልካም አባትነት የመሩትን፣ በክትትላቸውና በድጋፋቸው ያልተለዩትን ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ሳዊሮስ ሊቀ ጳጳስ ፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጆች ፣ የድርጅቱ የሥራ ሐላፊዎች አመስግነዋል።
በተለይም ከግላቸው ገንዘብ ከ10 ሚሊዮን ብር ያላነሰ በማውጣት ቢሮውን ያደሱትን የአዶር ኮንስትራክሽን ባለቤት ኢንጅነር አዲሱ ደመቀ፣ በድረገጽ ማበልጸግ ሥራ ላይ ድርሻቸው ሰፊ የሆኑንት መምህር ዘሩ ብርሃኔ እንዲሁም ሌሎች በልግሥና የተባበሩትን በሐሳብ ያልተለዩትን አካላት በእጅጉ አመስግነዋል።
በመቀጠልም የሚነበብና አርያነት ያለው ሥራ ለሠሩት እንዲሁም በበጎ ሥራ ለተባበሩ ሁሉም የእውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸውዋል።
ከነዚህም የ10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ያደረጉት ለአዶር ኮንስትራክሽን ባለቤት ለኢንጅነር አዲሱ ደመቀ ከነባለቤታቸው የወርቅ ካባ ተሸልመዋል።
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ሊቀ ጳጳስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ በተሠራው መደሰታቸውን ገልጸው በተለይ የቴክኖሎጅ ሽግግሩን በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ለመተግበር ከፍተኛ እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጥተዋል።
ቅዱስነታቸው በተሾሙበት መልካም ሥራ መሥራት ክብር መሆኑን የገለጹ ሲሆን እንዲህ ትውልድን የሚጠቅሙ የቤተ ክርስቲያን አሠራርን አንድ ርምጃ ወደፊት የሚያሻግረውን ይህን መሰል ሥራ የሚሠሩት ደግሞ ለግላቸው ሳይሆን ለሁላችን ተስፋ ለቤተ ክርስቲያንም የውጤታማነት ማሳያ ግርማ ነው ብለዋል።
በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ አክለውም ጆሮችን መልካም ነገር መስማት ናፍቆት በሆነበትና አሉታዊ ክፉ ወሬዎች በሚሰማት ወቅት መልካም ወሬ ደግ ሥራ ሠርታችን ደስ ስላሰኛችሁን እግዚአብሔር ይባርካችሁ ብለዋል።
በመጨረሻም የኃላፊነት አደራን ለተወጣችሁ በሀብታችሁ በሞያችሁ እንዲሁም በሐሳባችሁ በመልካሙ ሥራ ጋር ለተባበራችሁ ሁሉ እናመስግናለን እግዚአብሌር ይጠብቃችሁ ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት በ1990 ዓ/ም በመዋቅር የተቋቋመ መሆኑን ታሪክ ያስረዳል።
