የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ አሁናዊ ገጾች!
“ፈነወኒ እስብክ ዐመተ እግዚአብሔር ኀሪተ ወዘኮነ መዋዕለ”
የተወደደችው የጌታ ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል” /ሉቃ 4፡14/
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያ መዳረሻውን ቤተልሔም ሁለተኛ መዳረሻውን ደግሞ ቀራንዮ አድርጐ ወደ ምድራችን የመጣበትን ዓላማ ሲገልጽ “የጌታ
መንፈስ በእኔ ላይ ነው ለድሆች ወንጌልን እስብክ ዘንድ ቀብቶኛል፤ ለታሰሩትም መፈታትን ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ፣ የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ የተወደደችውንም የጌታ ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል” በማለት ተናግሯል፤ ይህ ንግግር መጀመሪያ በነቢዩ ኢሳይያስ አንደበት የተነገረ ሲሆን ቀጥሎ ጌታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ የራሱን አገልግሎትና የመጣበትን ዓላማ ለማስተዋወቅ የተጠቀመበት ጥልቅ መንፈሳዊ ኃይለ ቃል ነው፡፡
በብሉይ ኪዳን ሕግ (ዘሌዋ. 25) በየሃምሳ ዓመቱ በሚከበረው የኢዮቢልዩ ወይም የነፃነት በዓል ላይ በባርነት የተያዙ ባሪያዎች ነፃ የሚወጡበት ነበር፤ ዕዳም የሚሰረዝበትና የተያዘ መሬት ወደ ባለቤቱ የሚመለስበት እንዲሁም ለምድሪቱም ጭምር ብሔራዊ ዕረፍትም የሚደረግበት ነበረ የተወደደችውን የጌታን ዓመት የሚለው ሐሳብ በቀደመው ኪዳን ይደረግ የነበረውን የአካልና የቁሳቁስ ነፃነት ወደ መንፈሳዊ ልኬት ከፍ ያደረገ
ነው፡፡
የተወደደችውን የጌታ ዓመት እሰብክ ዘንድ ሲል በጥላነት መልኩ የአካልና የቁሳቁስ ነፃነት በመስጠት ሲከበር የነበረው የኢዮቤልዮ /የነፃነት በዓል/ አልፎ የኃጢያት ዕዳ
የሚሰረዝበት የሰይጣን ባርያዎች ነፃ የሚወጡበት እና ከእግዚአብሔር ጋር የታረቁበት የምሕረትና የይቅርታ የመንፈሳዊ ነፃነትና የድህነት ዘመን እንዲሁም እውነተኛና
ዘለዓለማዊ የነፃነትና የጸጋ ዘመን መምጣቱን ለማብሰር የተነገረ መንፈሳዊ አዋጅ ነው፡፡
ብፅዕ ወቅዱስ አባታችን፤
ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ፤
ብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ፤
ብፁዕ የመምሪያችን ሊቀጳጳስ፤
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ፤
የተከበራችሁ የዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ተሳታፊዎች
በዛሬው ዕለት ለሦስተኛ ጊዜ “በወንጌል ኮነ ሕይወትነ” በሚል መሪ ቃል በቅድስት ሥላሴ ዩንቨርስቲ ሁለገብ አዳራሽ እየተከበረ የሚገኘው ሦስተኛው ሀገር አቀፍ የስብከተ ወንጌል ቀን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በልዩ ልዩ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ችግሮች ውስጥ የነበሩትን ነፃ ለማውጣት እንደተላከ የተናገረውን መንፈሳዊ አዋጅ መነሻ በማድረግ ስለኢየሱስ ክርስቶስ የተነገረውን የመዳን መልዕክት፤ የሐዲስ ኪዳን የምስራች ቃል፤ የሕይወት መንገድና የተስፋ ቃል እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን በዚህ ምድር ላይ የመኖር ምስጢርና ዋና ተልዕኮ ስለሆነ ቅዱስ ወንጌል በሰፊው እንነጋገርበታለን፤በልዩ ልዩ መንገድም አስበነው እንውላለን፡፡
የበዓሉ/ጉባኤው ዋና ዓላማ፡-
የቅዱስ ወንጌሉን መልዕክት ማስታወስ፤ በተግባር መኖርን ማሳየት፤ እንዲሁም በጨለማ ሕይወት ላሉት ሁሉ የሕይወት ብርሃንን ለማካፈል ይሆን ዘንድ በክህነት ጥሪ
የተሰጠንን የአገልግሎት ቃል ኪዳን በድጋሚ ማደስ ሲሆን፡-
ግቡም፡- የምሥራች ዜናውን ማዳረስ፤ የአማኞችን መንፈሳዊ ሕይወት ማነቃቃት /ማነሳሳት/፤የቤተክርቲያንን አንድነት ማጠናከርና ቀጣዩን ትውልድ ማስተማር ነውና ለዚህ ቀንና ዕለት እንኳን በሰላም በጤና አደረሰን፤ አደረሳችሁ!!
ከዚህም በተጨማሪ ሦስተኛውን ሀገር ዓቀፍ የስብከተ ወንጌል ቀንን በዚህ መልኩ ተገናኝተንና ተሰባስበን ስናከብር የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያው
የቅዱስ ወንጌልን አገልግሎት ለማዳረስ ከቢሮ ጀምሮ በየደረጃው ያከናወናቸውን የ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት የሥራ ክንውን ሪፖርት በማቅረብ እና በቀጣይ በመምሪያው ሊሠሩ
የታሰቡትን በመግለፅ ጭምር ይሆናል፡፡
ስለሆነም የበጀት ዓመቱን የ10 ወራት ዋና ዋና የሥራ ክንውን ሪፖርት እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡
1.የቢሮ አደረጃጀትና ዕድሳትን በተመለከተ ቀደም ሲል መምሪያው የነበረበት ቢሮ ለሥራ ተነሳሽነት የማይመች ከመሆኑም ባሻገር በመምሪው ሥር ያሉትን የየዘርፍ ኃላፊዎች ለማስተናገድ የማይበቃ _ ስለነበር፤ ስፓንሰርሽፕ በማፈላለግና በተገኘው ድጋፍ በፓርትሽን በመከፋፈል እንዲሁም ያለሥራ የተቀመጡ ቢሮዎችን በማስፈቀድ ቢሮውን ለሥራ ምቹ በሆነ መልኩ ከማድረግም
ባሻገር ቀድሞ ከነበሩት በቁጥር 5 ቢሮዎች ወደ 9 በማሳደግ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
ለዚህም ስፖንሰር በማድረግ ለተባበሩን ሁሉ ከልብ የሆነ ምሥጋናችንን እናቀርባለን፡፡
2.የመምሪውን አዲስ አደረጃጀትና የሥራ አፈጻጸም መመሪያ ማዘጋጀትና ማጽደቅን አስመልክቶ፣ ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ ያለው የመምሪያው መተዳደሪያ ደንብና የክፍሎች አደረጃጀት በጊዜው ቢሠራበትም በአሁኑ ወቅት ግን የትውልዱን ጥያቄ የማይመልስና ዘመኑን የማይዋጅ በመሆኑ መምሪያው ዘመኑን ያገናዘበ አዲስ አደረጃጀትና የሥራ አፈጻጸም መመሪያ ማዘጋጅት አስፈላጊ መሆኑን አምኖበት ክርስቲያናዊ የምክክር አገልግሎት ዋና ማስተባበሪያ የአጫጭር ሥልጠናዎች ዋና ማስተባበሪያ ዘርፍ፤ የሚዲያና ሕትመት ዋና ማስተባበሪያ ዘርፍ፤ የጥናትና ምርምር ዋና ማስተባበሪ ዘርፍ ወዘተ የሚሉ 10 ዋና ዋና ማስተባበሪያ ዘርፎች እና 36 ንዑሳን ዘርፎች ያሉት
የአፈጻጸም መመሪያ /ደንብ/ አዘጋጅቶ በማቅረብ በጠቅላይ ቤተክህነት አስተዳደር ጉባኤ ጸድቆ የመጨረሻውን ዕውቅና ለማግኘት የግንቦት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤን በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡
3.መጠነኛ ቤተመጻሕፍት ማደራጃትን በተመለከተ
የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ሰፊ ዝግጅት እና በየጊዜው ራስን ማሻሻልን የሚጠይቅ የአግልግሎት ዘርፍ በመሆኑና መምሪያው በሥሩ ከ30 በላይ ተዘዋዋሪ ሰባክያነ ወንጌል
ያሉት መምሪያ ስለሆነ ለአገልግሎት ዝግጅ የሚጠቅሙና የአመለካከት ከፍታን የሚጨምሩ መንፈሳዊ ሥነ ልቦናዊ፧ ማህበራዊና ፍልስፍናዊ ይዘት ያላቸውን መጻሐፍት በማሰባሰብና መጠነኛ ቤተመጻሕፍት በመምሪያው ቢሮ በማደራጀት አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፤ በዚህ ሂደት መጻሕፍቱን ሂደት መጻሕፍቱን በመለገስ አስተዋጽኦ
ላደረጉልን ሁሉ በዚሁ ጉባኤ ፊት ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡
4.የ120ው ቤተሰብ ፕሮጀክት የ1% ወርኃዊ የስብከተ ወንጌል መዋጮ አሰባሰብን በተመለከተ
ቀደም ሲል የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የስብከተ ወንጌል አገልግሎቱን ከከተማ እስከ ገጠሪቱ ቤተክርስቲያን ለማዳረስ ታሳቢ በማድረግና በበጀት ዕጥረት ችግር
እንዳይገጥመው የ120 ቤተሰብን ከመመሥረትና ወርኃዊ መዋጮ እንዲደረግ ከማዘዝ ጀምሮ በየትኛውም የቤተክርስቲያን መዋቅር የሚያገለግል አገልጋይ ወይም ሠራተኛ ከሚከፈለው ወርኃዊ ደመወዝ ላይ _ 1% ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት እንዲያበረክት በተወሰነው መሠረት የ1% ወርኃዊ መዋጮው ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጅምሮ እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲናት ድረስ መምሪያው በከፍተኛ ሁኔታ በመንቀሳቀስ ውሳኔው ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፤ በሚገኘው ገቢም የስብከተ ወንጌል ተደራሽነት በእጅጉ እየሰፋ መሆኑን ሁሉም የሚረዳው ሐቅ ነው፤
የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ከሀገረ ስብከቱ እስከ ገዳማትና አድባራቱ ድረስ እንዲወርድ እና ተግባራዊ እንዲደረግ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ
ከልብ የሆነ ምሥጋና እናቀርባለን፤ጉባኤውም ከፍተኛውን ድርሻ ስለተወጡልን ከልብ ያመስግንልን፤
4.የመምሪያውን ሚዲያ አጠቃቀም በተመለከተ
መምሪያው ዘመኑ ያፈራውን ቴክኖሎጅ ምህበራዊ ሚዲያና ልዩ ልዩ መተግበሪያዎች ተጠቅሞ የቅዱስ ወንጌሉን አገልግሎት ለዓለም ሁሉ ማዳረስ ዋና ተግባሩ በመሆኑ
ለዚህ አገልግሎት የሚበጁ አስፈላጊ መሳሪዎችን ከማሟላት ጀምሮ በመምሪያው ስም ልዩ ልዩ ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመክፈት ስብከተ ወንጌል ነክ ዜናዎችንና ልዩ ልዩ ትምህርቶችን እያስተላለፈ ይገኛል፤ ከፍተኛ የሚባል እምርታም አግኝቶበታል፡፡
በሕትመት ሚዲያው ረገድም ቀደም ሲል በመምሪያው እየታተሙ ሲሰራጩ የቆዩትን የመጽሔትና የጋዜጣ ሕትመት በተሻለ ይዘትና አቀራረብ በድጋሚ ለመጀመርና በዲጅታል መልኩም ለማዳረስ የሚያስችል ጥናት ቀርቦ በዝግጅት ላይ ይገኛል፤
ዓመታዊ በዓላችንን ታሳቢ ተደርጎ የታተመውን ብሥራት መጽሔት ጨምሮ ለበዓለ ጥምቀትም በርካታ መምህራንን ያሳተፈ ልዩ እትም መጽሔት በማዘጋጀት በነፃ
ለምዕመናን እንዲሰራጭ ተደርጓል፡፡
በመደበኛ ሚዲያውም ከኢቢኤስ ቴሌቭዥን ጣቢያ በተገኘው ሳምንታዊ ነጻ የአየር ስዓት መምሪያው ትምህርትና ስብከቶችን እያዘጋጀ፡- ረቡዕ ከቀኑ 9 ስዓት እና እሁድ ከጠዋቱ
4 ስዓት ላይ ቅዱስ ወንጌልን ተደራሽ እያደረገ ይገኛል፤ በዚህም አገልግሎት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገልን ላለው ኢቢኤስ ቴሌቭዥን ጣቢያ ከልብ የሆነ ምሥጋናችንን
እናቀርባለን፤በቅርቡ በዕረፍተ ሥጋ የተለዩንን የድርጅቱ ባለቤት የአቶ አማኑኤልን ነፍስ በቅዱሳኑ ዕቅፍ እንዲያሳርፍልንም እንጸልያለን ፡፡
በተጨማሪም መቀመጫውን በሀገረ ኖርዌ ካደረገው አጥቢያ ዶትኮም የተባለ የቴክኖሎጅ ድርጅት ጋር መምሪያው በኢንተርኔቱ ዓለም ሰርበር ላይ የራሱ አድራሻ እንዲኖረው በመነጋገር በመምሪያው ስም ድህረ ገጽ የማበልጸጉ ሥራ ተጠናቅቆ በዛሬው ዕለት በይፋ
የሚመረቅ ይሆናልና እንኳን ደስ አላችሁ::
5.መስከረም 6 ቀን 2018 ዓ.ም በኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል የተደረገውን ምክክርና ውይይት በተመለከተ
መምሪያው ከሁሉም አህጉረ ስብከት ጋር ያለውን መዋቅራዊ ግንኙነትና የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ተደራሽነት ዙሪያ መሪነትና ተልእኳችን በሚል መሪቃል ምክክርና ውይይት ለማድረግ መስከረም 6 ቀን 2018 ዓ.ም ባዘጋጀው ጉባኤ ከየአህጉረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጆች ጋር በቀረቡት ሁለት ጥናታዊ ጽሑፎች መነሻነት ምክክርና ውይይት ተደርጓል፤ መምሪውም ለቀጣይ ሥራዎቹ የሚጠቅሙ የሐሳብ ግብዓቶችን አግኝቶ በሥራ ላይ እያዋለው ይገኛል፡፡
6.ስምሪትን በተመለከተ የስብከተ ወንጌል፣ ስምሪት ወይም ተልእኮ የቅድስት ቤተክርስቲያን ዋና ተልዕኮ ማስፈጸሚያ መንገድ በመሆኑ ላለፉት ሦስት ዓመታት ተቋርጦ የቆየውን ስምሪት በድጋሚ በማስጀመር ዓመታዊ ክብረ በዓላት ተጠብቆ ከሚደረገው ስምሪት በተለየ መልኩ የስብከተ ወንጌል ተደራሽነትና የምዕመናን ቁጥር አነስተኛ በሆነባቸው ጠረፋማና አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው 34 አህጉረ ስብከቶች የመምሪውን ሰባክያን ከድጋፍ ሰጭ ሰባክያነ ወንጌል ጋር በማቀናጀትና የአሰልጣኞች ሥልጠና በመስጠት ባደረገው ስምሪት የቤተ ክርስቲያን ተልእኮ፤ ዕቅበተ እምነትና የቤተክርስቲያን ታሪክ በሚል በተመረጡ
ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ለአገልጋይ ካህናት ሥልጠና ተሰጥቷል፤ ጉባኤያትም ተከናውነዋል፡፡ በስምሪቱም ልዩ ልዩ ድጋፍ ላደረጉልን ሁሉ ምሥጋናችን ላቅ ያለ ነው፡፡
7.ሚያዝያ 18 ቀን 2018 ዓ.ም በተመረጡ 12 አብያተ ክርስቲያናት የተደረገውን ሕዝባዊ የስብከተ ወንጌል ጉባኤ በተመለከተ ሦስተኛውን ሀገረ አቀፍ የስብከተ ወንጌል ቀን ከሚያዝያ 18 -19 ቀን 2018 ዓ.ም ለሁለት ተከታታይ ቀናት ለማክበር በመምሪያው በተያዘው ዕቅድ መሠረት በዓሉ
ምዕመናንንም እንዲሳትፍ በማሰብ ሚያዝያ 18 ቀን 2018 ዓ.ም የዋናው ጉባኤ ማብሰሪያ ሆኖ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በተመረጡ 9 ገዳማትና አድባራት እንዲሁም
በሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት በተመረጡ 3 አብያተ ክርስቲያናት በድምሩ በ12 ቦታዎች በመምሪያው አስተባባሪነትና አስፈላጊውን ወጪ ሁሉ በመሸፈን ወጥ የሆነ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በተመሳሳይ ስዓት ተከናውኗል፤ እግዚአብሔረም በህብረ ዝማሬ ተመስግኗል፡፡
8.ለደቡብ ኦሞ ኮሚቴ የተደረገውን የገንዘብ ድጋፍ በተመለከተ፣
የደቡብ ኦሞ የስብከተ ወንጌል ማስፋፋትና ሕንጻ ቤተክርስቲያን አሠሪ ኮሚቴ ባኮስ ሚዲያ) በደቡብ ኢትዮጵያ በተለይም በደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ከሀገረ ስብከቱ ጋር በመተባበር ያላመኑትን በማሳመንና የሥላሴ ልጅነት በማሰጠት ያመኑትን በማጽናትና ተተኪ ደቀመዛሙርት በማፍራት እያደረገ ለሚገኘው ከፍተኛ አገልግሎት መምሪያው የዕውቀትና የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያደርግለት በተደጋጋሚ ጥያቄ ባቀረበው መሠረት መምሪያው ምንም እንኳን የራሱ የሆነ በቂ በጀት ባይኖረውም ሥራው መደገፍ
እንዳለበት በመምሪያው ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ታምኖበት መምሪያው ከሚሰበስበው አንድ ፐርሰንት ገቢ ላይ 259,000 ብር ድጋፍ እንዲደረግ ተፈቅዷል፡፡
በቀጣይም ከሀገረ ስብከቱና ከኮሚቴው ጋር በመተባበር በጋራ ለመሥራት ዕቅድ ተይዟል፡፡
በቀጣይ በመምሪያው የሚሠሩ ዋና ዋና ሥራዎችን ለማመላከት ያክል
1. በመምሪው የተዘጋጀውን የሰባክያነ ወንጌልና የዘማሪያን አጠቃላይ የአገልግሎትና የሥነ ምግባር ደንብ በቅዱስ ሲኖዶስ አጸድቆ ሥራ ላይ ማዋል ፣
2. ከጽርሐ ጽዮን አንድነት ኑሮ የካህናት ማሠልጠኛ ጋር በመተባበር ከአህጉረ ስብከቱ ተተኪ የቋንቋ አገልጋዮችን በመመልመል አሰልጥኖ ማሰማራት፣
3. ሳምንታዊ የረቡዕ ተከታታይ የዮሐንስ ወንጌል ጥናት ላይ በተጨማሪነት የሚሰጡ አጫጭር ኮርሶችን በማከልና ልዩ ድጋፍ በመስጠትና ቋሚ የሥልጠና ቦታ በማዘጋጀት
ማስቀጠል፣
4. ልዩ ድጋፍና ክብካቤ የሚሹ ወገኖችን ማለትም
ማውታ ማዕከላት በሆስፒታልና በማረሚያ ቤት ያሉ
ጋር በመቀናጀት ቀሚ አገልግሎት መስጠት፣ በአረጋውያን መጦሪያ እና በእጓለ ወገኖችን በትኩረት ከሚመለከተው
5. የስብከተ ወንጌል በሚዲያ ተደራሽነት ዙሪ አሁን ካለው አጠቃቀም በተሻለ መልኩ ራሱን የቻለ የባለሙያ ቡድን በማደራጀትና ሱቱድዮ በማዘጋጀት ሥራውን መጀመር፧
6. 4ኛውን ሀገረ አቀፍ የስብከተ ወንጌል ቀን ከቀናት ስያሜ ከፍ በማለት የሰብከተ ወንጌል ሳምንት በማለት በተመረጡ የክልል ከተሞች ለማክብር ዝግጅት ማድረግ፤
7. ወጥ የሆነ የሥልጠና ማንዋል በማዘጋጀት በየአህጉረ ስብከቱ ውጤት ተኮር ተደጋጋሚ ሥልጠናዎችን መስጠት፣
8. መምሪያው የራሱ የሆነ ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት እና ለተለያዩ ሁነቶች የሚሆነ ሳውንድ ሲስተም መግዛት፣
9. ከመዋቅር ውጭ የሚያገለግሉ አገልጋዮችን በሚመለከት የራሱ የሆነ ወጥ መመሪያ በማዘጋጀት በመምሪያው መሠረት እንዲመሩ ማድረግ፣
10.ከተለያዩ ኮሌጆች ጋር ግንኙነት በመፍጠር በስብከት አገልግሎት ዙሪያ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሳለጥኑ ማድረግ፣ እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡
11የመምሪያውን የሰው ኃይል አደረጃጀት በተሻለና ሙያውና ብቃቱ ባላቸው አገልጋዮች በድጋሚ ማደራጀት የሚሉት ይገኙበታል።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ፡
