ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ሳዊሮስ 2018 ዓ.ም የትንሣኤ በዓል የእንኳን አደረሰዎ መርሐ ግብር ላይ ያስተላለፉት አባታዊ መልእክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይነበባል
“ወይእዜሰ በክርስቶስ ተሐድሰ ኵሉ ወኃለፈ ዘትካት ወናሁ ኮነ ሐዲስ ኵሉ … ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፏል እነሆ ሁሉም አዲስ ሆኗል” (2.ቆሮ 5÷17)
❖ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤
❖ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤
❖ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባ፣ የሐዲያና ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
❖ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት
ክቡር ንቡረ ዕድ ኤልያስ አብርሃ በመንበረ ፓትርያርክ ጠ/ቤ/ክ የመንፈሳዊ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ፤
ክቡር ረዳት ፕሮፌሰር ግርማ ባቱ በመንበረ ፓትርያርክ ጠ/ቤ/ክ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ፤
ክቡራን የመንበረ ፓትርያርክ ጠ/ቤ/ክ የየመምሪያውና የየድርጅቱ ኃላፊዎች፤
ክቡራን የመንበረ ፓትርያርክ ጠ/ቤ/ክ ሠራተኞች፤
ክቡራንና ክቡራት በዚህ መንፈሳዊ መርሐ ግብር የተገኛችሁ በሙሉ
በአምላካዊ ሥልጣኑ ሞትን ድል አድርጎ፣ ብርሃንን ተጎናጽፎ፣ ከሙታን የተነሣው፣ ሕያው እግዚአብሔር ቅዱስነታቸውን በሕይወት ጠብቆ አሮጌው ነገር አልፎ የአዲስ ሕይወት ኑሮ ለተጀመረበት በዓለ ትንሣኤ እንኳን አደረሰዎ በማለት ለቅዱስነትዎ ያለኝን ክብር በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሠራተኞች ስም ስገልጽ ምሉዕና ፍጹም በሆነ ደስታ ነው። (1.ቆሮ 15÷54)
የአዲስ ፍጥረት ምሥጢር ሰው ትንሣኤ ልቡና አግኝቶ በኢየሱስ ክርስቶስ ሲያምን የሚኖረውን አዲስ ሕይወትና ከአሮጌው ማንነቱ መለየቱን የሚያረጋግጥ ጥልቅ የሆነ ትርጉም ያለው በመሆኑ ትንሣኤውን እንደ ኃላፊ ኩነት ብቻ አስበን የምናልፈው አይደለም።
የክፋት ሁሉ ምንጭ የሆነው ዲያብሎስ በመሻሩ የሰው ልጅ ውጫዊ የሕይወት ለውጥን ብቻ ሳይሆን ፍጹም የሆነ ውስጣዊ ለውጥን ስላገኘ ትንሣኤው በዕለት ተዕለት የክርስትና ሕይወት ውስጥ ሁል ጊዜ የሚገለጥ አሁናዊ ጉዳይ ነው።
ከሞት በኋላ በሚቀጥል ሕይወት፣ አዲስ ፍጥረት ሆነን ለነፍሳችን ድኅነት ያገኘንበት የክርስቶስ ትንሣኤ በድካም ጊዜ ብርታት፣ በፈተና ጊዜ ሕያው ተስፋ፣ በጭንቀት ጊዜ ሰላም ከመሆኑም በላይ ክርስቶስ እኛን የወደደበት የታላቅ ፍቅሩ መገለጫ ነው።
በመሆኑም ክርስትና ሃይማኖታችን እርሱን መሠረት አድርጎ የቆመበት ትንሣኤው ታሪክ ብቻ ሳይሆን ዛሬም በሕይወታችን ላይ የሚሠራ ኃይል፣ የጨለማው መጨረሻ፣ ከጥፋት መንገድ የወጣንበት የንጋቱ መጀመሪያ መሆኑ አያጠያይቅም።
የመልእክታችን መነሻ የሆነው ሐዋርያዊ ቃልም «አሮጌው ነገር አልፎ እነሆ ሁሉም አዲስ ሆኗል» የሚል ነው። የክርስቶስ ትንሣኤና የምሥራቹ ዜና እስኪሰማ ድረስ የሰው ልጅ ያሳለፈው የመከራ ዘመን የሚረሳ አይደለምና አዲስ የሆነው ነገር ከአሮጌው ጋር መነጻጸሩ የማይቀር ነው።
በክርስቶስ ቤዛነት የተደረገልን ድንቅ ነገር ለመረዳትም ከአለፈው መነሣት የግድ ነው። የሐሳብ ቅንነት የጠፋበት፣ የመንፈስ ድካም የነበረበት ያ! አሮጌው ነገር በክርስቶስ አልፎ ዛሬ አዲስ የትንሣኤ ሕይወት አግኝተናል። በዚህም ሰው ሆኖ ያዳነን፣ በትንሣኤው አዲስ ሕይወት የሰጠንን አምላክ እናመሰግናለን።
ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን፤
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤
ክቡራንና ክቡራት በዚህ የእንኳን አደረሳችሁ መርሐ ግብር የተገኛችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን፤
ክርስቶስ ላንቀላፉት ሁሉ በኩራት ሆኖ በመነሣቱ በሰው ልጅ ሕይወት የነበረው ሥቃይና መከራ አልፎ፤ ሁሉም ነገር አዲስ በሆነበት የምሕረት ዘመን፤ የአሮጌው ማንነት መገለጫ ስንፍና፣ በሥራ ሲሸነፍ፣ ጥላቻ በፍቅርና በልማት ሊተካ አልቻለም ባይነት፣ አይቻልም ማለት በትንሣኤ ሕይወት ውስጥ ቦታ የላቸውም። (1.ቆሮ 15÷20)
በዚህ የሕይወት ጉዞ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሁለንተናዊ ተልዕኮና ራስን የመቻል ሁኔታ የተሟላ እንዲሆን የደከሙ፤ እነርሱ እየተራቡና እየተጠሙ የእኛ የልጆቻቸው ኑሮ እንዲሻሻል በመታመን አክብረው የሠሩ ቀደምት አባቶቻችንን የሚያስታውሱ በርካታ የልማት ሥራዎች በእግዚአብሔር ፈቃድ፣ በቅዱስነትዎ ጸሎትና አመራር ሰጪነት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ቀደም ሲል ተጀምረው ያልተጠናቀቁ የሕንፃ ግንባታዎችና በአዲስ መልክ የሚሠሩ ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው ጊዜ ተጠናቅቀው መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ተግተን በመሥራት ላይ እንገኛለን።
ከዚህም ጋር የተቋማት ማንነትና አሠራር የሚለካው በሚገለገሉባቸው ጽ/ቤቶች አያያዝና በሥራ አፈጻጸማቸው ስለሆነ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላላ ቤተ ክህነት ይዞታን በማስከበር ጽዱና ውብ ሥፍራ የማድረግ ሥራው በመገባደድ ላይ ይገኛል።
ያለ አግባብ የተከማቹ ንብረቶችም ተገቢውን መፍትሔ እንዲያገኙ፤ የግቢው ጽዳትና ውበት እንዲጠበቅ የማድረግ ሥራ ብዙ ጊዜና ጉልበት የሚጠይቅ የነበረ ቢሆንም በሁሉም የቤተ ክህነታችን የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ተሳትፎ በአግባቡ ተከናውኗል።
በመሆኑም ሥልጣነ ሞት የተሻረበትን የክርስቶስ ትንሣኤ ዛሬ በዚህ መልኩ ተሰብስበን በቅዱስነትዎ በራሄ የምናከብረው ከፍተኛ በሆነ የሥራ መነቃቃት ነው።
ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን፤
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤
ክቡራንና ክቡራት፤
ትንሣኤ የሥጋ መነሣት ብቻ አይደለም በእግዚአብሔር ቤት ሊሠራ የሚገባውን ሥራ በመሥራት ለኃጢአት ሞቶ፣ በአዲስ ሕይወት መኖር ማለት ነው። ትንሣኤ ልዩነትን ይሻገራል፣ በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር የሚታይ አንድነትንም ይፈጥራል። ከኃጢአት መራቅን፣ በፍቅር መኖርንና በተስፋ መጓዝን ያጎናጽፋል። ሰው ብቻውን ሲሠራ ውጤቱ ውስን ነው፤ በጋራ መሥራት ግን እጅግ ከፍተኛ ዋጋ ያለው በትንሣኤው የተገኘ የሕይወት መርሕ ነው።
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ዛሬ ያለችበት ደረጃ ላይ እንዲሁ በቀላሉ አልደረሰችም። በትንሣኤው የተገኘው አንድነት የበጎ ሥራ ሁሉ መሠረት መሆኑን በተረዱት፣ ለክብረ ስማቸው ይህን መታሰቢያ ትተውልን ባለፉት አባቶቻችንና እናቶቻችን ከፍተኛ ጥረት ነው። ዛሬ እኛ እየገነባን ያለነው እነርሱ ባኖሩት መሠረት ላይ ነው።
በመሆኑም ጊዜው የሥራ ጊዜ ነውና አሁን ያለነው የቤተ ክርስቲያን አባቶችና ምዕመናን የእምነታችንን ታሪክ ከሥርዓተ አምልኮው ጋር የመጠበቅና የማስጠበቅ፣ ለመንፈሳዊና ማኅበራዊ ዕድገት ልማትን አስፋፍቶ የመሥራት ኃላፊነት አለብን።
ስለዚህ በአዲስ መንፈስና በአዲስ ሕይወት እየተመላለስን የትንሣኤውን ብርሃን በማውጅ ለሀገር ሰላም፣ ለቤተ ክርስቲያን አንድነትና ለሐዋርያዊ ተልዕኮ መስፋፋት ሁሉም የቤተ ክርስቲያናችን አገልግሎቶች ለጥንታዊ ታሪካችን በሚመጥን መልኩ ድርሻችንን ልንወጣ ይገባል።
በታላቁ ዐቢይ ጾም ለሃምሳ አምስት ቀናት ያለ ዕረፍት ስታገለግሉ ከርማችሁ ደከመን ሳትሉ በተቀደሰው ኦርቶዶክሳዊ ትውፊት መሠረት ቅዱስ አባታችንን እንኳን አደረሰዎት ለማለት የሁላችን ማዕከል ወደ ሆነው መንበረ ፓትርያርክ መጥታችሁ የበረከቱ ተካፋዮች የሆናችሁትን ሁሉ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ስም ከልብ እናመሰግናችኋለን።
በመጨረሻም ቅዱስ አባታችን በልጁ ሞት ይቅር ያለን አምላካችን እግዚአብሔር በጸሎት፣ በሐሳብ ካልተለየዎትና ሁልጊዜም ከማይለየዎት ሕዝበ ክርስቲያን ጋር በሰላም፣ በጤና ጠብቆ እንኳን ለ2018 ዓ/ም በዓለ ትንሣኤ በድጋሚ አደረሰዎ እያልኩ መልእክቴን በዚህ አጠቃልላለሁ።
የቅዱስነትዎ ቡራኬ አይለየን
አባ ሳዊሮስ
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላላ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤
የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ የምስካዬ ኅዙናን ገዳም የበላይ ኃላፊ፤
ሚያዝያ 5 ቀን 2018 ዓ/ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
