የበዓለ ትንሣኤ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የእንኳን አደረሰዎ መርሐ ግብር ተከናወነ
ኢኦተቤ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ
ሚያዚያ ፭/ ፳፻፲፰ ዓ.ም.
በየዓመቱ በትንሣኤ ማግስት ፣ በአዲስ ዓመት ማግስትና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ማግስት ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽሕፈት ቤት ጀምሮ እስከ አዲስአበባ ሀገረ ስብከት አድባራትና ገዳማት አገልጋዮች በመሰባሰብ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ የእንኳን አደረሰዎ መርሐግብር ይካሄዳል።
በዚሁ መሠረት የዘንድሮ የ2018ዓ.ም የትንሣኤ በዓል ምክንያት በማድረግ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የምስካየ ኅዙናን መድኀኔዓለም ገዳም የበላይ ኀላፊ፣ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ፣ የራያ ስድስቱ ወረዳዎች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የቅርሳቅርስ ወመዘክርና ቤተመጻሕፍት ፣ የማሕበራት ምዝገባ ፣ ክትትልና ቁጥጥር መምሪያዎች የበላይ ኀላፊ፣
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስአበባ፣ የሐድያና ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዓን አበው ለቃነ ጳጳሳት፣
ንቡረእድ ኤልያስ አብርሃ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት በመንፈሳዊ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ
ረ/ፕ ግርማ ባቱ (ቀሲስ) የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ፣
መ/ም አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ የአዲስአበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክልነት ጽሕፈት ቤት ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎችና ሠራተኞች ፣የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎችና ሠራተኞች፣የአዲስአበባ ሀገረ ስብከት አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ፣የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ፣ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት መርሐግብሩ ተካሂዷል።
መርሐግብሩ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃና ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት መሪነት የደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን አገልጋይ ካህናት ጸሎተ ወንጌል አድራሽነት በጸሎት የተከፈተ ሲሆን የበርካታ ሊቃውንት መፍለቂያ በሆነውና በአንጋፋው በሰዋስዋወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀመዛሙርትና መምህራን አማካኝነት ያሬዳዊ ዜማ መነሻነት የእለቱ ተከታታይ መርሐግብራት መቅረብ ጀምረዋል።
ከሊቃውንቱ ያሬዳዊ ዜማ በመቀጠል የአዲስአበባ ሀገረ ስብከት አድባራትና ገዳማት ተወካዮች የትንሣኤውን ምስጢር በሚያብራራ መቅድም በመነሣት በልጅነት መታዘዝ ለቅዱስነታቸው የእንኳን አደረሰዎ መልእክት በጽሑፍ አቅርበው በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽሕፈት ቤት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማዕከላውያን የሰንበት ትምህርት ቤት አባላትና የጋሞኛ ዘማርያን በያሬዳዊ ዜማ ቅዱስነታቸውን እንኳን አደረሰዎ ብለዋል።
በመቀጠልም ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እለቱን የሚመለከት ቅኔ በማቅረብ መርሐግብሩ ቀጥሏል። ከሊቃውንቱ ቅኔ በመቀጠል ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ለቅዱስነታቸው የእንኳን አደረሰዎ መልእክት ሲያቀርቡ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው በሚል ሐይለ ቃል በመነሳት የአሮጌው ዘመን ልዩ መገለጫ የሆነውን ስንፍና በሥራ ጥላቻን በፍቅር በመተካትና ዛሬን የሰጡንን የአባቶቻችንን ውለታ ባለመርሳት የቅድስት ቤተክርስቲያንን ይዞታዋን ማስከበር፣ የተጀመሩ ሕንጻዎችን ማስፈፀም፣ ቅጥር ጊቢውን ውብና ጽዱ ለማድረግ የቅዱስነታቸው ጸሎትና አባታዊ መመሪያ ዋጋው ላቅ ያለ መሆኑን ገልጸው ቅዱስነታቸው ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ እንዲሰጡ ጋብዘዋል።
በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ በዚህ መልኩ በተዘጋጀው የእንኳን አደረሰዎ መርሐግብር ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው ጌታችን እና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር በሥጋ ማርያም በመገለጥ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሥጋውን የቅረሰውና ደሙን ያፈሰሰው ይህንን ዓለም ለማዳንና ለማደስ ነው።
እግዚአብሔር ይህንን ዓለም አመቻችቶ ክቡር ለሆነው ለሰው ልጅ ሲሰጥ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለውን የጥል ግድግዳ በማፍረስና የዲያብሎስን ስልጣን በመሻር ነበር። ነገር ግን የተከፈለልንን የክርስቶስ ዋጋ የረሳ በሚመስል መልኩ እርስ በእርሳችን እየተበላላን እንገኛለን በማለት ማንኛውም አማኝ በተከፈለለት ልክ እንዲኖር አባታዊ መመሪያ ሰጥተው በቅዱስነታቸው ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል።
ዘገባው የኢኦተቤ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ነው።
