የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ሰሎሞን በቀለ ከገዳማትና አድባራት የአገልግሎት መሪዎች ጋር ትውውቅ አደረጉ።
ነሐሴ ፲፱/፳፻፲፰ ዓ/ም አ/አ/ሀገረ ስብከት ሚዲያመልአከ ብርሃን ሰሎሞን በቀለ ከነሐሴ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ኃላፊነት ተረክበው በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት መመደባቸውን ተከትሎ፣ ከሀገረ ስብከቱ እና ከገዳማትና አድባራት የሥራ ኃላፊዎች ጋር የትውውቅ መርሐ ግብር ተካሄደ።
መርሐ ግብሩ ጸሎተ ወንጌል የተነበበ ሲሆን ወቦሌ ኆኅተ ብርሃን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተክርስትያን በሊቃውንት ያዘጋጁት ያሬዳዊ ዜማ ቀርቧል።በማስከተልም ቅኔ በተመረጡ ሊቃውንት ቀርቧል።
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ምክትል ሥራ አሥኪያጅ በመጋቢ ትፍስት ሙሉጌታ የሹመት ደብዳቤው ተነቧል። አክለውም የእንኳን ደና መጡ መልዕክ አስተላልፈዋል።
በትናንትናው ዕለትም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አዳዲስ የዋና ክፍልና የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጆች የተመደቡትን የትውውቅ መርሐ ግብር ተካሂዷል።
የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ዋና ጸሐፊዎች እንዲሁም ምክትል ሊቃነ መናብርት የወከሉ አባቶችን እንኳን ደህና መጡ በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
አክለሁም በፊት በሠሩባቸው ሥራዎች ታታሪነታቸውንና በሥራቸው የሚታወቁ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ ይህም በሀገረ ስብከቱ እየታየ ላለው የአሠራር ብልሹነት መፍትሔ ይሆናል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ቤተ ክርስቲያንን ለቀጣዩ ትውልድ ማሻገር የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን ጠቁመው፣ ይህንን ማድረግ ካልቻልን እግዚአብሔር የራሱን ሰው ያዘጋጃል፤ እኛ ሳንሻግር እንቀራለን እንጂ ቤተ ክርስቲያን ግን ተሻጋሪ መሆኗን ገልጸዋል። በመጨረሻም ከጎናቸው በመሆን ለሥራቸው ሙሉ ድጋፍና እገዛ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
በአስተዳዳሪነት ከሚመሩት ከኆኅተ ብርሃን ቅድስት ማርያም ካቴድራል ተወክለው ምስክርነት የሰጡት አቶ አቤል አሰፋ እንዳሉት “መልአከ ብርሃን ሰሎሞን በቀለ የወንጌል ተደራሽነትን ለምእመናን በማስፋፋትና ትምህርተ ወንጌልን በቀላሉ ተደራሽ በማድረግ ረገድ በትጋት የሠሩ እንዲሁም ለቤተክርስቲያንና ለምእመናን የሚጠቅሙ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በማከናወን፣ ቀደም ሲል ተጀምረው በተለያዩ ምክንያቶች ተቋርጠው የነበሩ የልማት ሥራዎችን ዳግም በማስጀመርና በማስቀጠል የተገኙት ውጤቶች ተጠቃሽ በማድረግ በእነዚህ ሥራዎች በተለይም የወንጌል መልእክት ለምእመናን በሰፊው እንዲደርስ በተግባር ለማስፈጸም ብርቱ ተነሳሽነት፣ ትጋትና ትዕግሥት የሚጠይቅ መሆኑን በመጥቀስ፣ በሥራቸው ጠንካራና ታታሪ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ሰሎሞን በቀለ፣ የሥራ አስኪያጅነት ማዕረግ ለእሳቸው የሥልጣን ማዕረግ ሳይሆን የትሕትና ታላቅ አደራ መሆኑን ገልጸዋል ። ብፁዓን አባቶችን፣ የቤተ ክርስቲያን አባቶችን፣ ሊቃውንትን በማመስገን ይህችን ቤተ ክርስቲያን ጠብቀውና ተንከባክበው እስካሁን ስላቆዩአት በእግዚአብሔር ስም ምስጋና አቅርበዋል።
አክለሁም ሕጉ፣ ሥርዓቱና መመሪያው ከሚያስቀምጠው በተጨማሪ፣ እንደ ልጅ ታዘው በመሥራት የቤተ ክርስቲያኗን ተልእኮ ለማሳካት እንደሚጥሩ ገልጸዋል።
ትምህርተ ወንጌል ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን፣ ምእመናን በእምነታቸው እንዲጠነክሩ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኗን ሀብትና ንብረት በፍርሃተ እግዚአብሔር፣ በታማኝነትና በሐቀኝነት፣ በግልጽነትና በተጠያቂነት መንፈስ መምራትና ማስተዳደር እንደሚገባ አስታውቀዋል።
መልአከ ብርሃን ሰሎሞን በመልእክታቸው መጨረሻም፣ በወንድማዊነትና በአባታዊነት ሐሳባቸውን እንዲያካፍሏቸው፣ ምክራቸውን እንዲለግሷቸውና በጸሎታቸው እንዲያስቧቸው በትሕትና ጠይቀዋል።
ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ሳዊሮስ በመልእክታቸው፣ ቤተ ክርስቲያን በዘመኑ ከሚያጋጥሟት ውጫዊና ውስጣዊ ፈተናዎች ተሻግራ ወደ ቀድሞ ታሪኳና ክብሯ እንድትመለስ በንስሐና በአዲስ መንፈስ መነሳት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ብፁዕነታቸው የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የዘመኑን የዋጀ አመራር ማነስ፣ የንብረት አያያዝ፣ የራስ አገዝ ልማት መዳከም እና የአገልጋዮች መንፈሳዊነት ተግዳሮት ከውስጣዊ ፈተናዎች መካከል ጠቅሰው፣ እነዚህን ለመፍታት ቤተ ክርስቲያንን ማእከል ያደረገ፣ ከቡድንና ከብሔር ነጻ የሆነ አድሎአዊ ያልሆነ አሠራር መዘርጋት እንደሚገባ እንዲሁም የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔና ልዕልና በማክበር፣ የበላይ አካል የሰጠውን ደንብ በመጠበቅ፣ በቴክኖሎጂ የታገዘና ግልጽ የፋይናንስና የንብረት አስተዳደር በመዘርጋት ለሙስናና ለብልሹ አሠራር መወገድ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
ቤተክርስቲያን የሁሉም ወገን እናት እንጂ የቡድኖች መጠቀሚያ ልትሆን እንደማይገባ አሳስበዋል።
ብፁዕነታቸው ለአዲሱ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ሰሎሞን በቀለ ትልቅ ተስፋና አደራ መጣሉን ገልጸው፣ ሀገረ ስብከቱን ወደ ቀድሞ ክብሩ ለመመለስ ሁሉም የየድርሻቸውን እንዲወጡ አባታዊ ጥሪ አቅርበዋል።
በመጨረሻም ቤተክርስቲያን የሁሉም ወገን እናት እንጂ የቡድኖች መጠቀሚያ ልትሆን አይገባም፤ “በደመወዛችሁ ኑሩ እንጂ በማንም ግፍ አትሥሩ፣ ማንንም አትቀሙ፣ አትበድሉ” በሚለውም የወንጌል ቃል መጠቅለያ ሐሳብ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
“በፊታችሁ ያለውን ተመልከቱ” በሚለው በ2ኛ ቆሮንቶስ 10፥7 መሠረት፣ የእግዚአብሔር ሰዎች ወደ ፊት እንጂ ወደ ኋላ ሊመለከቱ እንደማይገባቸው ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ አሳስበዋል።
ተስፋ ወደ ፊት ሲሆን፣ ታሪክ ደግሞ ወደ ኋላ እንደሆነ ያስታወሱት ብፁዕነታቸው፣ ያለፈውን በመተው ወደ ፊት መመልከት፣ ያለፉትን ችግሮች እየረሱና የተፈጸሙ ስህተቶችን እያረሙ ወደ ፊት መጓዝ እንደሚገባ እንዲሁም የተሰጠንን የቤተ ክርስቲያን አደራ በታማኝነት መጠበቅና ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ አለብን በማለት ገልጸዋል።
ስለሆነም ይላሉ ብፁዕነታቸውን ያለፈውን በትምህርትነት ተጠቅመን፣ ስህተቶችን እያረምንና ተስፋችንን በፊታችን ላይ አድርገን ወደ ፊት መመልከት እንደሚገባ በአጽንኦት ገልጸዋል።
በትውውቅ መርሐ ግብሩ ላይም ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የደብቡ ምዕራብሸ ሸዋና ሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የምስካየ ኅዙናን ገዳም የበላይ ጠባቂ ፣ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ የከምባታ፣ ሐላባ፣ ጠምባሮ እና የዳውሮ ኮንታ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት መምሪያ ሐላፊዎች፣መልአከ ብርሃን ሰሎሞን በቀለ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ፣ የሀገረ ስብከቱ የዋና ዋና ክፍል ሐላፊዎች፣ የ8ቱ የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጆችና የሰው ኃይል አስተዳደር ሐላፊዎች፣ የሀገረ ስብከቱ የገዳማትና አድባራት ዋና አስተዳዳሪዎች፣ የሰበካ ጉባኤ ምክትል ሊቃነ መናብርትና ዋና ጸሐፊዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ ጽናት አስቻለው
