የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አሠራሯን ወደ ዲጂታል ሥርዓት ለማሸጋገር የሚያስችሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን አጠናቃ ተግባራዊ ልታደርግ መሆኑን ተገለጸ።
ነሐሴ 7 ቀን 2018 ዓ.ምየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአሠራር ሥርዓቷን ከወረቀት ንክኪ ነፃ ወደ ሆነ የዲጂታል አሠራር ለማሸጋገር የሚረዱ የመሠረተ ልማት እና የሶፍትዌር ፕሮጀክቶችን አጠናቃ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ልትሸጋገር መሆኑ ተገለጸ።
በዚሁ ጉዳይ በተዘጋጀው ውይይት መድረክ ላይ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የምዕራብ ሸዋ እና የሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የተለያዩ መምሪያ ኃላፊዎች እና በዘርፉ በኩል የተዋቀሩ ኮሚቴዎች ተገኝተዋል።
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የአይሲቲ እና ዲጂታል ሽግግር አማካሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ቀሲስ ዮሐንስ ተስፋዬ፣ ቀደም ሲል በቅዱስ ሲኖዶስ የፀደቁትና አቅጣጫ የሚያሳዩት ሰነዶች በቀጥታ ወደ ተግባራዊ ሥራ የሚመሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የአማካሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ ለጊዜው ተጠናቀው የተዘጋጁ የተለያዩ ሲስተሞችን በውይይት መድረኩ ላይ አቅርበዋል። እነዚህም፦
1. በቤተ ክርስቲያኗ መምሪያዎችና አህጉረ ስብከት የሚካሄዱ በርካታ ድረ-ገጾችንና የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾችን ጠቅልሎ እንደ ዋና መግቢያ በር የሚያገለግል ዋና የመረጃ መግቢያ ድረ-ገጽ (Web Portal) ተገንብቷል። ይህ ፖርታል የቤተ ክርስቲያኗን ስያሜ፣ ማንነትና ታሪክ የሚያሳይ ሲሆን፣ በውስጡም የሰነድ ማደራጃ (Documentation)፣ የእውቀት ማኔጅመንት (Knowledge Management) እና የአርካይቭ ሥርዓቶችን ያካተተ ነው።
2. የሰበካ ጉባኤ ምዕመናን መመዝገቢያ የዲጂታል ሥርዓት ሲሆን የምዕመናን፣ የጥምቀት፣ የጋብቻ እና የዕረፍተ ሥጋ (ሞት) መረጃዎች በማዕከል ደረጃ የሚመዘገቡበት ሥርዓት ነው። መረጃው በአድባራቱ ደረጃ የሚመዘገብ ቢሆንም፣ አደረጃጀቱ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጀምሮ በአህጉረ ስብከት፣ በወረዳና በክፍለ ከተማ እስከ ደብር ድረስ ወርዶ የበላይ ኃላፊዎችና አባቶች ሙሉ መረጃውን በቀላሉ ማየትና መከታተል የሚያስችላቸው ነው።
3. የሰው ኃይል አስተዳደር ሥርዓት (HR System) ሲሆን በቤተ ክርስቲያኗ መዋቅር በሁሉም ደረጃ የሚገኙ አገልጋዮችና ሠራተኞች የሚመዘገቡበት ነው። ጊዜና ቦታ ሳይገድበው ባለሙያዎች ባሉበት ቦታ ሆነው በኢንተርኔት አማካይነት መረጃዎችን ማስገባትና በአንድ ማዕከል ማየት የሚያስችልም ነው ብለዋል።
በተጨማሪም የሀብት አስተዳደር የኢአርፒ (ERP) ሲስተሞች፣ የዲጂታል ላይብረሪ እና የቅርስ ጥበቃ ሥራዎች የቀረቡ ሲሆን፤ የዲጂታል ሽግግሩ ዋና መርሕ ቴክኖሎጂን ለመግዛት ብቻ ሳይሆን ተቋማዊ ተልዕኮን ለማሳካትና አሠራርን ለማዘመን እንደሆነ ተጠቅሷል።
ቀሲስ ዮሐንስ አክለውም ሥራው ቢጀመርም ወደ ዲጂታሉ ዓለም ለመውሰድ የታቀዱ በርካታ ተግባራት የሚቀሩ በመሆኑ፣ በዘርፉ ዕውቀቱና አቅሙ ያላቸው የቤተ ክርስቲያኗ ልጆች ባሉበት ሆነው የቴክኖሎጂ ዕድገቷን እንዲደግፉና አሻራቸውን እንዲያኖሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በመድረኩ የመምሪያ ኃላፊዎች ለዘርፉ ባለሙያዎች ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፣ ይህ ተግባር የቤተ ክርስቲያኗን ጥንታዊነትና ልዕልና ለዓለም የሚያስተዋውቅ፣ ከአኃት አብያተ ክርስቲያናት ጋር የሚኖራትን ግንኙነት የሚያጎለብትና ገጽታዋን የሚቀይር በመሆኑ በፍጥነት ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ ደብር መዋቅሩ ተዘርግቶ መሬት ላይ ወርዶ ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
እንዲሁም ሥራውን ወደ ተግባር ለማውረድ ከፍተኛ በጀት የሚጠይቅ በመሆኑ ሁሉን አቀፍ ትብብርና ድጋፍ ሊደረግ እንደሚገባ በመድረኩ ተነስቷል።
የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ከልማት ሥራዎች ሁሉ በላይ ሆኖ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ አፅንዖት በመስጠት ተናግረዋል። “ቤተ ክርስቲያናችን ትልቅ ናት፤ አሁን ላይ ከቴክኖሎጂ አንጻር ወደ ኋላ ቀርተናል” ያሉት ብፁዕነታቸው፣ ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም፣ የቤተ ክርስቲያኗን ክብርና ልዕልና ጠብቆ ከዓለም እና ከአኃት አብያተ ክርስቲያናት ጋር ማቀራረብና አብሮ መፍጠን እንደሚገባ ገልጸዋል።
ቤተ ክርስቲያን የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂን የሚመራ ክፍል በመምሪያ ደረጃ አዋቅራ እየተንቀሳቀሰች መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ከሀገረ ስብከት ጀምሮ እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ድረስ መዋቅሩ እንዲዘረጋ መመሪያ የወረደ መሆኑ ተገልጿል።
©የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት/ EOTC Broadcasting Service Agency/
