ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ በኢትዮጵያ የግሪክ አምባሳደር ሚስተር አንቶንዮስ ስጉሮፖሎስን (Antonios Sgouropoulos) በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ።
ነሐሴ ፯ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም አ/አ/ሀገረ ስብከት ሚዲያብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በኢትዮጵያ የግሪክ ኤምባሲ አምባሳደር አንቶኒዮስ ስጉሮፖሎስን (Antonios Sgouropoulos) በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በኖርዲክና ግሪክ ሀገረ ስብከት በግሪክ አቴንስ ከተማ በምትገኘው ምክሐ ደናግል ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን በምእመናንና በቤተክርስቲያኑ አስተዳደር ጋር በነበረው አለመግባባት የተነሣ በተፈጠረው ችግር ምክንያት ከ40 ዓመታት በላይ አገልግሎት ስትሰጥ የነበረችው ቤተክርስቲያን አገልግሎቷ ሊቋረጥ ችሏል፤ በዚህም የተነሣ በሀገሪቱ ሕግ መሠረት በግሪክ የሃይማኖት ሚኒስቴር ትእዛዝ መሠረት ተዘግታለች። ይህች ቤተክርስቲያን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናንን በአቴንስ አገልግሎት ስትሰጥ የነበረ ታሪካዊ ማዕከል መሆኗ ይታወቃል።
ይህን የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ቅዱስ ሲኖዶስ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ቅዱስነታቸው በኢትዮጵያ የግሪክ ኤምባሲ አምባሳደር ከሆኑት አንቶኒዮስ ስጉሮፖሎስ ጋር ቤተክርስቲያኗ ስለምትከፈትበትና አገልግሎቱ የሚጀመርበትን አካሄድ በተመለከተ ሰፊ ውይይት አድርገዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በውጩ ሀገራት ለሚገኙ ምእመናን መንፈሳዊ አገልግሎት የምትሰጥ ብቻ ሳይሆን ትውልዱ በመልካም ሥነ ምግባር ተኮትኩቶ እንዲያድግ የምታደርግ ናት፡፡ ቤተክርስቲያኗ ባህላዊ ማዕከል (በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ልጆቻቸው ባህላቸውንና እምነታቸውን እንዲይዙ የምታደርግ)፣ በማኅበራዊ ጉዳይም (በስደት ዓለም ለሚኖሩ ምእመናን መጠጊያና መጠለያ) በመሆን ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ የምትሰጥ ተቋም መሆኗ ይታወቃል፡፡
©EOTC TV
