በሀገረ ስብከቱ ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት የሁሉም ትብብር እንደሚያስፈልጋቸው መልአከ ብርሃን ሰሎሞን በቀለ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ገለጹ።
ነሐሴ ፰/፳፻፲፰ ዓ/ም አ/አ/ሀገረ ስብከት ሚዲያበሀገረ ስብከቱ ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት የሁሉም ትብብር እንደሚያስፈልጋቸው መልአከ ብርሃን ሰሎሞን በቀለ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ገለጹ።
የሀገረ ስብከቱ አዲሱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ይህንን ያሉት በዛሬው ዕለት በተከናወነው የእንኳን ደህና መጡ አቀባበልና ትውውቅ መርሐ ግብር ላይ ነው።
በመርሐ ግብሩ ንቡረ ዕድ ኤልያስ አብርሃ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የመንፈሳዊ ዘርፍ ምክልት ሥራ አስኪያጅ፣ መልአከ ሰላም ዶ/ር አባ ቃለጽድቅ ሙሉጌታ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ዋና ሐላፊ፣ የሀገረ ስብከቱ የዋና ዋና ክፍል ሐላፊዎች የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጆች፣ የሀገረ ስብከቱና የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ሠራተኞች ተገኝተዋል።
በመቀጠልም የሹመት ደብዳቤው በመልአከ ገነት አባ ተክለ ማርያም አምኜ የሀገረ ስብከቱ የትምህርትና ማሰልጠኛ ዋና ክፍል ሐላፊ የተነበበ ሲሆን ሹመቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ በሐምሌ 29 ቀን 2018 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ለሀገረ ስብከቱ የሥራ ሐላፊነት የትምህርት ደረጃቸው የሥራ ልምዳቸውና ሥነ ምግባራቸው ታይቶ እንዲመደቡ ሲል ያሳለፍን ውሳኔን መሠረት በማድረግ መልአከ ብርሃን ሰሎሞን በቀለ ከነሐሴ 8/2018 ዓ/ም ጀምሮ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው እንዲያገለግሉ መመደባቸውን ደብዳቤው ይጠቁማል።
በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ የተፈረመው ደብዳቤ አዲስ ሥራ አስኪያጅ በዋናነት ስብከተ ወንጌልን፣ሰበካ ጉባኤን፣ሰንበት ት/ቤትን በማደራጀትና በማስፋፋት፣ እንዲሁም የሀገረ ስብከቱንና የቤተ ክርስቲያንን ሀብትና ንብረት ጠብቆ በማስጠበቅ በየደረጃው ያለው ሁለንተናዊ ልማት በፍትሐዊነት እንዲጠናከርና እንዲስፋፋ በማድረግ፣ በተጨማሪም ሕገ ቤተ ክርስቲያንና ቃለ ዓዋዲው እንዲሁም የሀገረ ስብከቱ መተዳደሪያ ደንብ ተጠብቆ በሀገረ ስብከቱ እየተስተዋለ ያለውን የመልካም አስተዳደርና የሙሰኝነት ችግር ለመቅረፍ ፍትሐዊ የአሠራር ሥርዐት በመዘርጋት ሥር ነቀል ለውጥ ሊመጣ እንዲችል ሓላፊነትን በትጋትና በታማኝነት እንዲወጡ የሚያሳስብ የሹመት ደብዳቤ ነው።
በመርሐ ግብሩ ከሀገረ ስብከቱ ሊቃውንት ጉባኤ አባላት መካከል መጋቤ ሐዲስ ቆሞስ አባ ክንፈ ርግብ ቅኔ ያቀረቡ ሲሆን ቀጥሎም የተለያዩ የእንኳን ደህና መጡ መልእክቶችም ተላልፈዋል።
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃ፣ ለአዲሱ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ የእንኳን ደና መጡ መልእክት አስተላልፈዋል ። የብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ሳዊሮስ አደራ በሀገረ ስብከቱ ነገን ያለመ፣ የቤተ ክርስቲያን ክብር የጠበቀ እና ዘመኑን የዋጀ ስር ነቀል ለውጥ እንዲመጣ መሆኑን አስታውሰዋል።
ሀገረ ስብከቱ ከቅጥርና ከዝውውር ሥራ ተሻግሮ ትውልዳዊና ቤተ ክርስቲያናዊ አደራን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።
በሀገረ ስብከቱ የሚስተዋሉ ችግሮች የአንደ ወገን የሊቀ ጳጳስ ወይም የሥራ አስኪያጅ ብቻ አለመሆኑን ጠቁመው ችግሩ ደረጃውና መጠኑ ይላያይ እንጂ ከአጥቢያ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት እንዲሁም ሀገረ ስብከትና ጠቅላይ ቤተ ክህነት ድረስ በመሆኑ ለመትሔውም ሁላችን የበኩላችን ድርሻ ልንወጣ ይገባል ብለዋል።
አክለውም በተዋቀረና በተስተካከለ አሠራር እንዲመሩ፣ እንደትናንቱ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን በእኩል ዓይን እንዲመለከቱ አደራ ብለዋል። በተጨማሪም የተሻለ የአሠራር ሥርዓት ለመፍጠር ተጠያቂ የሚቀጣና የሚያሸልም አሠራር ያለውን የሥራ ሥርዓትን እንዲዘረጉ አሳስበዋል።
የሀገረ ስብከቱን የሥራ ሐላፊዎችና ሠራተኞችን በመወከል የሀገረ ስብከቱ ሊቃውንት ጉባኤ ዋና ሰብሳቢ መልአከ ፀሐይ ቆሞስ አባ ኃይለ መለኮት በበኩላቸው፣ መልአከ ብርሃን ሰሎሞን ከልጅነት ጀምሮ በትጋትና በቁርጠኝነት ቤተክርስትያንን ያገለገሉ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ አሁንም በማእከላዊነት ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል መመደባቸው የቀደመው አገልግሎታቸው ምስክር መሆኑን ገልጸዋል። በዚህም የሀገረ ስበከቱ የሥራ ሐላፊዎችና ሠራተኞችን ቤተ ክርስቲያንን በሚጠቅም ተልእኮና ትውልድን በሚያተርፍ ሁለንተናዊ ሥራዎች በአንድነት ከጎናቸው እንደሚቆምና እንደሚተባበር ተናግረዋል። ለተሰጣቸውም ኃላፊነት መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆንላቸው ተመኝተውላቸዋል።
የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነትን በመወከል የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ገነት መምህር ልሣነ ወርቅ ተስፋም፣ አዲሱ የሥራ ዘመን የተሻለ ውጤት የሚመዘገብበት እንዲሆን ተመኝተውላቸዋል። የቤተ ክርስቲያናችን የውስጥ አንድነትን በመጠበቅና ውጫዊ ተግዳሮቶችን በብልሃት ወደ መልካም አጋጣሚ ለመቀይር ይቻል ዘንድ ሁላችንነ ለቤተ ክርስቲያናችን ተልእኮ መቆም አለብን ብለዋል። ይህን መሠረት በሚያደርግ አገልግሎትም የክፍላተ ከተማ ሥራ አስኪያጆችም በትብብር እንደሚሠሩና ከጎናቸው እንደሚቆሙ ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው የተመደቡት መልአከ ብርሃን ሰሎሞን በበኩላቸው፣ ለተሰጣቸው ሐላፊነትና በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያር ጀምሮ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ሳዊሮስ ለሰጡኝ የአገልግልቶ ዕድል በእጅጉ አመሰግናለሁ ቡራኬያቸው አይለየኝ ብለዋል።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ ብዙ ስመ ብዙም በመሆኑ የተሻለና ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት በጋራ መሥራት፣ መናበብና መደማመጥ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው።
በመሆኑም በክብር የተሰጣቸውን ሐላፊነት በመልካም ውጤት መልሶ በክብር እንደወጣ በጸሎት አስቡኝ ብለዋል።
አክለውም ክቡር ሥራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ሰሎሞን በቀለ ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል በእግዚአብሔር ስም ምስጋና አቅርበዋል።
በመጨረሻም መርሐ ግብሩ በመልአከ ሰላም ቆሞስ አባ ቃለ ጽድቅ ሙሉጌታ (ዶ/ር) በጸሎት ተጠናቋል።
መልአከ ብርሃን ሰሎሞን በቀለ በሀገረ ስብከቱ በሚገኙ ታላቅ ገዳማትና አድባራት በአገልጋይነት በሥራ መሪነት በጸሐፊነት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በቦሌ ደብረ ሴሌም መድኃኔዓለምእና በሌሎች እንዲሁም ዛሬ ለሥራ አስኪያጅነት እስከተጠሩበት ጊዜ በሰሚት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን፣ እንዲሁም እስካሁኑ ሰዓት በቦሌ ኆኅተ ብርሃን ቅድስት ማርያም ካቴድራል ላለፉት 6 ዓመታት በአስተዳዳሪነት ሲያገለግሉ መቆየታቸው ታሪካቸው ያስረዳል።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ አገልግሎት/Addis Ababa Diocese Media Service
