የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት 14ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በተገኙበት በመንበረ ጸባዖት ቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል በመከበር ላይ ይገኛል።
ነሐሴ 10ቀን 2018 ዓ.ም አ/አ/ሀገረ ስብከት ሚዲያየአምስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚደንትና የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም ምክር ቤት የክብር ፕሬዚደንት አሥራ አራተኛ ዓመት የመታሰቢያ በዓል ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያው ኃላፊዎች በተገኙበት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እየተከበረ ነው።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ከሐምሌ 5 ቀን 1986ዓ.ም. ጀምሮ ለ20 ዓመታት ቤተ ክርስቲያንን በርእሰ አበውነት ሲመሩ ከቆዩ በኋላ በ76 ዓመት ዕድሜያቸው ነሐሴ 10 ቀን 2004 ዓ.ም. ሐሙስ ከንጋቱ 11 ስዓት ላይ በደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል የሕክምና ርዳታ ሲደረግላቸው ከቆዩ በኋላ የዘመናት ባለቤት እግዚአብሔር የመደበላቸውን ጊዜ በታማኝነትና ይህ ቀረው በማይባል ስኬት አጠናቀው ከዚህዓለም በሞተ ሥጋ ተለይተዋል፡፡
ቅዱስነታቸው በጾመ ማርያም የመጀመሪያውን ሳምንት ሱባኤ በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ቀድሰው በማቊረብና በማስተማር መሰንበታቸውና የመጀመሪያው ሳምንት ሱባኤ በተጠናቀቀበት ወቅት፦ “አባቶች ሱባኤው ተጠናቋል” በማለት በወቅቱ አብረዋቸው ለነበሩ ብፁዓን አባቶች መግለጻቸውና አባቶችም፦ “ቅዱስ አባታችን ገና እኮ ሳምንት ይቀራል” ሲሏቸው “የእኔን አጠናቅቄአለሁ”ማለታቸውን ብፁዓን አባቶች ያስታውሳሉ፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በ1928 ዓ.ም. በትግራይ ክፍለ ሀገር በአድዋ አውራጃ ተወለዱ፡፡ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በአቅራቢያቸው በሚገኘው የአባ ገሪማ ገዳም መንፈሳዊ ትምህርታቸውን በመጀመር በዚሁ ገዳም ከዲቁና እስከ ምንኩስና መዓርግ የደረሱ ሲሆን፤ በመቀጠል የቤተ ክርስቲያንን ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ትምህርቶች አጠናቀው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ጨርሰዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በመንፈሳዊውም ሆነ በዓለማዊው ዕውታቸው ጣምራ ችሎታ የነበራቸው ለመንበረ ማርቆስ የተገቡ ዓለም አቀፋዊ የጥበብ ሰው እንደነበሩ፡፡ የውጭ ምሁራን ሳይቀሩ “ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በጣት ከሚቆጠሩ ጥቂት ታላላቅ ምሁራን ውስጥ አንዱ የሆኑና በኢትዮጵያ አርእስተ አበው (ፓትርያርኮች) ታሪክ ውስጥ ወደር ያልተገኘላቸው ብቸኛው ፓትርያርክ ናቸው” በማለት ምስክርነታቸውን ሰጥተውላቸው ነበር።
ስም ወደ ሥራ ይመራል እንዲሉ፥ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የመናገር ተሰጥዖ የነበራቸው፥ በወንጌል ስብከታቸው የብዙኃኑን ልቡና የዳሰሱና አጥንትን የሚያለመልም አንደበት የነበራቸው የወንጌል ገበሬ ነበሩ፡፡ ቅዱስነታቸው በፓትርያርክነት ዘመናቸው ያስመዘገቡት አስደናቂ ታሪክ ሁሉ በተጋድሎና በፍጹም የእምነት ጽናታቸው መሥዋዕትን ከፍለው የሠሩት እንጂ ነገሮች ሁሉ ቀና ሆነው የአልጋ በአልጋ የሆነ ውጤት የተመዘገበበት አልነበረም፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የልዩ ልዩ ሃይማኖት ተቋማት መሪዎች የሆኑ ኢትዮጵያውያን ወገኖች ለሀገር ሰላምና ዕድገት ከመቸውም ጊዜ በበለጠ መልኩ በሀገራዊ ፍቅር በሰላምና በፍቅርበጋራ እንዲሠሩና ሀገራቸውን እንዲገነቡ በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት የበላይ ጠባቂነታቸው አማካኝነት ከፍተኛ ጥረትን አድርገዋል፤ ተጨባጭ ውጤትም አስመዝግበዋል፡፡ በተቋሙ ውስጥም በሁሉም የሃይማኖት አባቶች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን ያተረፉ አባትም ነበሩ፡፡
©የኢኦተቤ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ
