ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ሳዊሮስ እና ብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ አቡነ ዲዮስቆሮስ ለ272 አገልጋዮች ሥልጣነ ክህነት ሰጡ።
ነሐሴ ፲፯ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ምብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የምስካየ ኅዙናን ገዳም የበላይ ጠባቂ እንዲሁም ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት በዓለምገና ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ተገኝተው ለ272 የአብነት ተማሪዎችና የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ሥልጣነ ክህነት ሰጥተዋል።
ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ እና ብፁዕ ዋና ፀሐፊው በቤተክርስቲያን ሥርዓት መሠረት ተምረው ፈተና ላለፉ ለ238 የዲቁና፣ ለ 33 የቅስና ሥልጣነ ክህነት ለ1 አባት ደግሞ የቁምስና ማዕርገ ክህነት ሰጥተዋል።
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ አባቶቻችን በጊዜያቸውን ቤተክርስቲያንን አገልግለው ለእኛ እንዳስረከቡን ሁሉ እኛ ደግሞ በጊዜያችን የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የተሳካና የተቃና ይሆን ዘንድ ያለ ዕረፍት ለ24 ሰዓት እያገለገልን ነው ብለዋል።
ብፁዕነታቸው ቤተ ክርስቲያን ተተኪ ምትክ አገልጋይ እንደሚያስፈልጋት በመግለጽ ትምህርታቸውን ሲከታቱሉ ቆይተው ትምርታቸውን ላጠናቀቁ ሥልጣነ ክህነት እንደሰጡ ተናግረዋል።
ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በዛሬ ዕለት ሥልጣነ ክህነት ለተቀበሉ ሁሉ ሃይማኖታቸውን ጠንክረው በመጠበቅ በትጋት ሊያገለግሉ እንደሚገባ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስም ክህነት መጠራት መሆኑን በመግለጽ ቅዱሳን ሐዋርያት ከልዩ ልዩ የሥራ መስክ ተጠርተው ቤተ ክርስቲያንን እንዳስፋፉ ሁሉ በዛሬው ዕለት ሥልጣነ ክህነት ለተቀበሉ አገልጋዮች ሰው ካልተማረ ማገልገል ኣይችልምና የቀረባቸውን ትምህርት በደምብ በመማርና የጎደላቸውን ትምህርት በማሟላት ምእመናንን በማስተማር የቤተ ክርስቲያን ተከታዮችን ማብዛትና መጠበቅና እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
ክህነት ሰማያዊ እና ሰማያዊ ንጉሥ ለማገልገል መሆኑን የገለጹት ብፁዕነታቸው ፣ በዛሬው ዕለት በክህነት እንድታገለግሉ ተጠርታቹኋል፤ የሰው አገልጋዮች ሳትሆኑ የሰማያዊ ንጉሥ አገልጋዮች ናችሁ፤ አሁን ተቀብታቹኋል ተቀድሳቹኋል እና በትሕትና በቅድስና ሁናችሁ ማገልገል አለባችሁ ብለዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መገናኛ ብዙኅን ሥርጭት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር አካለወልድ ተሰማ፣ የሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሰላም ዓለማዮ ተፈራ፣ ሊቀ ሥዩማን ተስፋዬ ለሜቻ የሸር ከተመ ሀገረ ስብከት ዋና ፀሐፊ፣ የሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት የሥራ ኃላፊዎች፣ የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ምሐረት ፀጋዬ፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና በርካታ ምእመናን ተገኝተዋል።
©EOTC TV
