ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ በመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም እየተከናወኑ ያሉ የልማትና የሕንጻ ዕድሳት ሥራዎችን ጎበኙ።
ሰኔ 18 ቀን 2018 ዓ/ምብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ፣የአዲስ አበባ ሀዲያና ስልጤ አኅጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋር በመሆን በመንበረ መንግሥት ግቢ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም እየተከናወኑ ያሉ ልዩ ልዩ የሕንጻ ዕድሳትና አዳዲስ የግንባታ ሥራዎችን በቦታው ተገኝተው ተመልክተዋል።
ብፁዕነታቸው በገዳሙ ባደረጉት በዚህ የሥራ ጉብኝት፥ የቤተክርስቲያኑን ጥንታዊና ታሪካዊ ክብር በጠበቀ መልኩ እየተከናወነ ያለውን የዋናውን የሕንጻ መቅደስ ዕድሳት ሥራ ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
በተጨማሪም ለአገልግሎት መፋጠንና ለቤተክርስቲያኑ መንፈሳዊ ልዕልና ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል የተባሉትን፦
የካህናት ማረፊያ ሕንጻ ግንባታን፣
የጎብኚዎችና የበረከት ፈላጊዎች መጠለያ ሥራዎችን፣
እንዲሁም የሰንበት ትምህርት ቤት እና የጸበል ቤት ዘመናዊ ሕንጻዎችን የሥራ ሂደት በጥቅሉ ገምግመዋል።
ብፁዕነታቸው በጉብኝት ወቅት ባስተላለፉት አባታዊ መመሪያ፥ የቅዱሳን መካናትን ክብር መጠበቅና ለአገልግሎት ምቹ ማድረግ የትውልድ ድርሻ መሆኑን አስታውሰው፣ በገዳሙ እየተከናወነ ያለው ይኸው ሰፊ የሕንጻና የልማት ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና በተቀመጠለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ አባታዊ ቡራኬና መመሪያ ሰጥተዋል።
ክቡር መልአከ ምህረት ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ የአዲስ አበባ ሀገረስብከት ዋና ስራአስኪያጅ በበኩላቸው፥ አገረ ስብከቱ ለገዳማትና አድባራት መንፈሳዊና ማኅበራዊ ልማት የሚያደርገውን የተጠናከረ ክትትልና ድጋፍ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። የገዳሙ አስተዳደርና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችም በጉብኝቱ ላይ አብረው የተገኙ ሲሆን፥ የተጀመሩት ዘመናዊና መንፈሳዊ ይዘታቸውን የጠበቁ ግንባታዎች በታቀደላቸው መርሐ-ግብር መሠረት ለአገልግሎት ዝግጁ እንደሚሆኑ ታውቋል።
© Amdehaymanot Sundayschool
