ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስና ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ገዳምን የሕንጻ ቤተክርስቲያን የዕድሳት ሥራ አፈጻጸም ሂደትን ተዘዋውረው ተመለከቱ።
ሰኔ 9 ቀን 2018 ዓ.ምብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣
የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ክቡር ንቡረዕድ ኤልያስ አብርሃ የጠቅላይ ቤተክህነት የመንፈሳዊ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅና የጠቅላይ ቤተክህነት የመምሪያ ኃላፊዎች በቁልቢ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የሕንጻ ቤተክርስቲያን የዕድሳት ሥራ አፈጻጸም የደረሰበትን ሁኔታ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
በዚሁ ጊዜ የሕንጻ ቤተክርስቲያኑ የዕድሳት ሥራ በተያዘለት ጊዜ ገደብ ውስጥ በጥሩ ሁኔታ እየተካሔደ የሚገኝ ሲሆን የግንባታ ሥራውም ሰባ ፐርሰንት ተሠርቶ የተጠናቀቀ መሆኑንና በቀሪው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ የግንባታ ሥራው ተጠናቆ
ሐምሌ 17 ቀን ታቦተ ሕጉ ከመቃኞ በመውጣት ወደ ሕንጻ ቤተክርስቲያኑ እንደሚገባ አማካሪ መሐንዲሱ ፕሮፌሰር ፋሲል
እና የሕንጻ ሥራ ተቋራጩ የአዶር ኮንስትራክሽን ባለቤት ኢንጂነር አዲሱ ደመቀ ገልጸዋል።
በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ባስተላለፉት አባታዊ የሥራ መመሪያ ቀደምት አባቶች ሠርተው ያቆዩልንን ይህን የመሰለ ጥንታዊ ገዳም ተንከባክቦና ጠብቆ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ይቻል ዘንድ በሚቻለው መጠን በርካታ ሥራዎች እየሠራን መሆኑን በተግባር የሚያረጋግጥ ሥራ በዚህ ታላቅ ገዳም እየተከናወነ ስለሆነ ቀሪ ሥራዎች የቤተክርስቲያኑን ጥንታዊነትና ታሪካዊነትን በጠበቀ መልኩ በጊዜው ተጠናቆ ለምርቃት እንዲበቃ።ጠንክራችሁ ሥሩ ካሉ በኋላ የዕድሳት ሥራውን በማከናወን ላይ የሚገኘው አዶር ኮንስትራክሽን በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ይህን ሥራ እዚህ ደረጃ ላይ ማድረስ በመቻላቸው ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።
በመቀጠልሞ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክት የዚህ ታሪካዊ ሥራ አካል በመሆናችን እድለኞች
ነን ካሉ በኋላ በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ አባታዊ አመራር ሰጪነት
ይህን ታሪካዊ ቤተክርስቲያን ለማደስ በመቻላችን ደስተኞች ነን ብለዋል።አያይዘውም እየተሠራ ያለው ሥራ በጣም የሚደነቅና አፈጻጸሙም የሚያስመሰግን በመሆኑ ሥራውን የምታከናውኑ ባለሙያዎችም ምስጋና ይገባችኋል ካሉ በኋላ ይህ አንጋፋ ቤተክርስቲያን የእድሳት ሥራው እጅግ በጥንቃቄ መሰራት
የሚገባው መሆኑን ተገንዝባችሁ ሥራችሁን ከአሁን በበለጠ ትጋት እንድትፈጽሙ አደራ እንላለን በማለት አባታዊ መልዕክታቸውን አጠቃለዋል።
©የኢኦተቤ ሕዝብ ግንኝነት መምሪያ
