“በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ሳይሆን፣ በቤተ ክርስቲያን ሰዎች አሰራር ውሱን ሕፀፅ ባይጠፋም፣ መዓዛ መንፈስ ቅዱስ አይለያትምና አሁንም ዓለም መታመንን ከቤተ ክርስቲያን ሰዎች ትጠብቃለች” ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ
ጥቅምት ፲፫/፳፻፲፱ ዓ/ም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ዓመታዊው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዛሬው ዕለት መከፈቱን በዛሬው ዕለት በቃለ በረከት አብስረዋል።
ቅዱስነታቸው በመክፈቻ መልእክታቸው ለሹመትና ለኃላፊነት መታመን መሠረታዊ እውነት መሆኑን አስምረውበታል።
ለዚህም ሊቀ ነቢያት ሙሴ ለሾመው የታመነ እንደነበር በሚናገረው የዕብራውያን መጽሐፍ ምንባብ መሠረት በማድረግ እግዚአብሔር ሙሴን ለላቀ ኃላፊነት የመረጠው ታማኝ መሆኑን አይቶ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ሙሴ የንጉሥ ልጅ ከመባል ይልቅ ከወገኖቹ ጋር መከራ መቀበልን፣ ከብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ስለእግዚአብሔርና ስለህዝቡ መነቀፍን፣ እንዲሁም በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ መሰደድን በመምረጥ ታማኝነቱን በተግባር እንዳረጋገጠ አብራርተዋል።
“በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ሳይሆን በቤተ ክርስቲያን ሰዎች አሠራር ውሱን ሕፀፅ ባይጠፋም” መዐዛ መንፈስ ቅዱስ አይለያትምና ዓለም አሁንም መታመንን ከቤተ ክርስቲያን ሰዎች እንደምትጠብቅ ገልጸው፣
ጉባኤው በቤተ ክርስቲያን መታመን እንዲኖር አብዝቶ የመሥራትና የማሠራት መለኮታዊ ኃላፊነት እንዳለበት አሳስበዋል።
የመክሊት ባለቤቶች የተመሰገኑትም ታማኝ ሆነው በመገኘታቸው እንደሆነ አስታውሰዋል።
ቅዱስነታቸው ቀጥለውም ጉባኤ የሚያስፈልግበት ዋና ምክንያት የተሳሳተውን ለማስተካከልና የተዛባውን ለማቅናት መሆኑን ጠቁመው፣ በአንዳንድ አህጉረ ስብከት የሰው ኃይል አስተዳደር፣ የሀብት አጠባበቅ፣ የምእመናን አያያዝና ሐዋርያዊ ተልእኮ ለዘመኑ የማይመጥን መሆኑ በስፋት እየተነሳ እንደሆነ ተናግረዋል። አሳሳቢ ምልክቶችም እየታዩ በመሆኑ፣ ጉባኤው የአሠራር ክፍተቶችን በሚገባ ፈትሾ “ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ” ዘላቂ መፍትሔ እንዲያስቀምጥ አሳስበዋል።
በተጨማሪም በሀገር ውስጥና በውጭ አህጉረ ስብከት፣ በተለይም በአፍሪካና በላቲን አሜሪካ ያሉ ዕድሎችን በታቀደና በተጠናከረ ሁኔታ መሥራት የሚቻልበትን ሁኔታ ጉባኤው እንዲመለከት ጠይቀዋል።
ቅዱስ ሲኖዶስ ከእግዚአብሔር የተቀበለውን መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተልእኮ በአግባቡ መወጣት የሚችለው በሀገር ሰላም ሲኖር መሆኑን ቅዱስ ፓትርያርክ ያስታወሱ ሲሆን ሕዝቡ ካጋጠመው ያልተቋረጠ መከራና ጭንቀት እንዲያርፍ ከመጸለይ ባሻገር የማግባባት፣ የማስታረቅና የማስማማት ሥራ ከሲኖዶሱ እንደሚጠበቅ ጠቁመው፣
አያይዘውም ምልዓተ ጉባኤው በዚህ ጉዳይ እንዲወያይና ለባለድርሻ አካላት የሰላም ጥሪ እንዲያስተላልፍ ቅዱስነታቸውን አሳስበዋል።
