ቅዱስ ሲኖዶስ የመጀመሪያ ቀን የዕለት ውሎ በአምስት አጀንዳዎች ላይ ውሳኔ መሰጠቱ ተገለጸ።
ጥቅምት 13 ቀን 2019 ዓ.ም)
በፍትህ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቁጥር 164 እንደተደነገገው ቅዱስ ሲኖዶስ ጥቅምት 12 ቀን ምልአተ ጉባኤውን እንደሚያደርግ ይታወቃል። የ2019 ዓ/ም የጥቅምት ሲኖዶስ የመጀመሪያ ቀን የዕለት ውሎ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፤ መሪነት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ገዳም ጥቅምት 11ቀን 2019 ዓ.ም በጸሎት መጀመሩ ይታወሳል ።
ቅዱስ ሲኖዶስ በብፁዕ አቡነ ሉቃስ ሥርዓተ ቀብር ምክንያት ጥቅምት 12 ቀን 2019 ዓ.ም ስብሰባውን አራዝሞ ጥቅምት 12 ቀን በቅዱስ ፓትርያርኩ መክፈቻ ንግግር ጉባኤውን ጀምሯል ።
ቅዱስ ሲኖዶስ በቀዳሚው ቀን በአምስት አጀንዳዎች ላይ ውሳኔ መሰጠቱ ተገለጿል።
ለመገናኛ ብዙኃን ሥርጭት አገልግሎት ድርጅት EOTCTV መግለጫ የሰጡት በረዳት ፕሮፌሰር ዳንኤል ሰይፈሚካኤል የቅዱስ ሲኖዶስ ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ምልዓተ ጉባኤው አጀንዳዎችን እንዲቀርጹ ሰባት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን መሰየሙን ገልጸዋል ።
ምልዓተ ጉባኤው በተመረጡት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት አቅራቢነት ሃያ አምስት አጀንዳዎችን በማጽደቅ ጉባኤውን ማካሄድ መጀመሩን አሳውቀዋል ። የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በአጅንዳዎቹ ቅድም ተከተልም በአምስት አጀንዳዎች ላይም ውሳኔ አስተላልፏል ብለዋል።
ቅዱስ ሲኖዶስ በአጀንዳ አንድ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የመክፈቻ መልዕክትን የተመለከተ ሲሆን ፤ ቅዱስነታቸው ያስተላለፉት አባታዊ መልእክት ቅዱስ ሲኖዶስ በሁሉም አህጉረ ስብከት የቤተ ክርስቲያናችን የሥራ መመሪያ ሆኖ እንዲተገበር መወሰኑን በዕለታዊ መግለጫው ተገልጿል።
ቅዱስ ሲኖዶስ በሁለተኛው አጀንዳ የ45ኛው ዓለም አቀፍ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ስብሰባ የአቋም መግለጫን በተመለከተ፤ ውይይት ያደረገ ሲሆን ፤ ቃለ ጉባኤውና የአቋም መግለጫውን በመስማት፤ የአቋም መግለጫው የተወሰኑ ማስተካከያዎችን በማካተት ተግባራዊ እንዲሆን ለሁሉም አህጉረ ስብከት መመሪያ መስጠቱን በረዳት ፕሮፌሰር ዳንኤል ሰይፈሚካኤል ገልጸዋል ።
ቅዱስ ሲኖዶስ በቀጣይነት በሀገራዊ ሰላምና ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ችግሮችን በተመለከተ የተወያየ ሲሆን ፤ የሰላም ኮሚቴው ያከናወናቸው ጉዳዮች በዝርዝር ተመልክቷል ።
ቅዱስ ሲኖዶስ በሀገራችን በካህናት አገልጋዮችእና በምእመናን ላይ እየደረሰ ያለውን አጠቃላይ የሰላም ጉዳይ ትኩረት በማድረግ ውይይት አድርጓል። በዚህም ባለፈው ዓመት እና በዚሁ ዓመት በአርሲ እና አከባቢው እንዲሁም በሌሎችም በኦርቶዶክሳውያን ላይ የተፈፀመውን ግድያ እና መፈናቀል አውግዟል።
ችግሩ እንዲቀረፍም ከመንግሥት ጋር ውይይት እንዲደረግ መመሪያ እና አቅጣጫ መስጠቱ ተመልክቷል ።
ቅዱስ ሲኖዶስ በቀዳሚው ቀን ጉባኤው ከወላይታ ሀገረ ስብከት የቀረበውን ሥርዓተ ትምህርት በተመለከተ የተወያየ ሲሆን፤ ሥርዓተ ትምህርቱና ጥያቄው በሀገረ ስብከቱ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ቀርቦ፤ በቋሚ ሲኖዶስ ታይቶ፣ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የትምህርትና ማሠልጠኛ መምሪያ ታይቶና ተገምግሞ፤ በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ በአስቸኳይ ታይቶ ለውሳኔ እንዲቀርብ መደረጉ ታውቋል።
የካህናት ማሠልጠኛው አስፈላጊነት ታምኖበት በቀድሞው ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት (አባ መላኩ) ስም በአካባቢው ያለውን አሁናዊ ወይም ነባራዊ ግምት ውስጥ በማስገባት ማሰልጠኛው እንዲከፈት ውሳኔ መስጠቱን ለመገናኛ ብዙኃን ሥርጭት አገልግሎት ድርጅት EOTCTV መግለጫ የሰጡት በረዳት ፕሮፌሰር ዳንኤል ሰይፈሚካኤል አስታውቀዋል ።
የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት/ EOTC Broadcasting Service Agency/
