“ስብከተ ወንጌል ትላንት፣ ዛሬና ነገ “በሚል ርዕስ የስብከተ ወንጌል ተደራሽነትና የአገልግሎቱን ስትራቴጂ የተመለከተ ውይይትና ሥልጠና ተካሄደ።
በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ተዘጋጅቶ፣ ለአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች፣ ለስብከተ ወንጌልና ለሰበካ ጉባኤ ማደራጃ ዋና ክፍሎች ኃላፊዎች የተሰጠ በስብከተ ወንጌል ተደራሽነትና በአገልግሎቱ ዙሪያ ያተኮረ ሰፊ ውይይትና ሥልጠና ተካሂዷል።
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ረዳት ፕሮፌሰር ግርማ ባቱ፣ ለውይይቱ መነሻ የሚሆን የጥናት ጽሑፍ፣ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል ጉዞ ትላንት፣ ዛሬና ነገ” በሚል ርዕስ አቅርበዋል።
በጥናታዊ ጽሑፋቸውም ስብከተ ወንጌል ምን እንደሆነ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያለው ታሪካዊ ጉዞ ምን እንደሚመስል፣ የአሁኑ ወይም የወቅቱ ሁኔታዎች ምን እንደሆኑ፣ እንዲሁም ያሉትን ጠንካራ ጎኖችና ፈታኝ ሁኔታዎች በዝርዝር አብራርተዋል።
በቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ መነሻነትም የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ አገልግሎት ወቅታዊ ሁኔታና ስትራቴጂ፣ አመራርና የሰባክያን ቅንጅት ድጋፍ፣ ወጣቶችንና የዘመኑን ትውልድ የማድረስ ሥራ፣ የአቅም ግንባታና ሥልጠና፣ ፈታኝ ሁኔታዎችና የወደፊት አቅጣጫዎች፣ መዋቅራዊ ግንኙነት፣ ልዩና መደበኛ ስምሪቶች እንዲሁም የአገልጋዮችን ሥነ ምግባር በተመለከተ የውይይት ነጥቦች ላይ ውይይት ተደርጓል።
በውይይቱም የስብከተ ወንጌል ተደራሽነትን ለማሳደግ የዲጂታል ሚዲያ አጠቃቀምን ማሻሻል፣ ዘመኑንና ጊዜውን የዋጀ የስብከት አገልግሎት መስጠት፣ የሰባክያንን እጥረት መፍታት፣ በተለያዩ ቋንቋዎች የስብከተ ወንጌል አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ፣ በጀትን ማሻሻልና ለአገልጋዮች ሰፊና ቀጣይነት ያለው የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠት በዋናነት ትኩረት ሊደረግባቸውና መፍትሔ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ተገልጿል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ፣ የምሥራቅ ሐረርጌ፣ የምሥራቅ ወለጋና የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኒቆዲሞስ፣ የሰሜን ወሎ፣ የደቡብ ወሎና የከሚሴ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ረዳት ፕሮፌሰር መምህር ግርማ ባቱ፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ኃላፊ መጋቤ ሐዲስ ፀጋ ወልደ ትንሣኤ፣ የአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች፣ የስብከተ ወንጌልና የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ ዋና ክፍሎች ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በተካሄደው የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያ ተልእኮ ሥልጠና መድረክ ላይ የተሳተፉ የስብከተ ወንጌል አገልጋዮች፣ የቤተ ክርስቲያኗን የወንጌል ስርጭት ሥራ በተሟላ አቅም ለማከናወን፣ የአገልግሎቱን መዋቅር ለማጠናከር፣ ተከታታይ ሥልጠናና ውይይት ለማካሄድ፣ ወጣቶችን በልዩ ጉባኤያት ለማገልገል፣ የቋንቋ አገልግሎትንና ዘመናዊ የመገናኛ ዘዴዎችን ለማሻሻል፣ የመምህራንን እውቀት፣ ክህሎትና ሥነ ምግባር ለማስጠበቅ፣ እንዲሁም የሥራ አፈጻጸምና ክትትልን ለማጠናከር የስብከተ ወንጌል ሐዋርያዊ ተልዕኮን በተቀናጀና በተከታታይ መንገድ ለመፈጸም ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ የአቋም መግለጫ በሥልጠናው መድረክ ላይ ተነቧል።
በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክት፣ ስነ ምግባር ላይ በተሻለ መጠን ልንዘጋጅና ልንሰራ ይገባል ። ሥነ ምግባርን ሰው ራሱ ካላመነበትና በሕይወቱ ካልተገበረው፣ ሌሎችን እናስተምራለን ማለት አዳጋች ነው ሲሉ አሳስበዋል ።
መርሐ ግብሩም በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ማርቆስ ጸሎት ና ቡራኬ ተጠናቋል።
ዘጋቢ ጽናት አስቻለው
