ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በኢትዮጵያ የጆርዳን ኤምባሲ አምባሳደር አምጃድ አል ሙማኒ (Amjad Al Moumani) በቢሮአቸው ተቀብለው አነጋገሩ።
ኅዳር ፯ ቀን ፳፻፲፱ ዓ.ም)ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በኢትዮጵያ የጆርዳን ኤምባሲ አምባሳደር አምጃድ አል ሙማኒ (Amjad Al Moumani) በቢሮአቸው ተቀብለው አነጋገሩ።
ክቡር አምባሳደሩ እንደተናገሩት በጆርዳን እንደ እ.ኤ.አ በ2030 ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀበትን ሁለት ሺኛ ዓመት ለማክበር በዝግጅት ላይ እንገኛለን። ቅዱስነትዎ ወደ ጆርዳን መጥተው ቢባርኩን፣ የሚዲያ አካላት፣ ሌሎች ልዑካንም መጥተው እንዲጎበኙት ቢደረግ ቦታው በይበልጥ እንዲታወቅ ያደርጋል ብለዋል።
አምባሳደሩ አያይዘውም በዮርዳኖስ ጥምቀተ ባሕር አጠገብ ለቤተክርስቲያን በተሰጠው ቦታም አዲስ ሕንጻ ቤተክርስቲያን ሠርታችሁ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ ቢቻል መልካም ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ለአምባሳደሩ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ለመካከለኛው ምሥራቅ ሀገረ ስብከት የመደባቸው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ድሜጥሮስ ስላሉ፣ ማንኛውንም ጉዳይ ከብፁዕነታቸው ጋር በመወያየት ማመቻቸት ይቻላል ሲሉ አብራርተዋል።
ቅዱስነታቸው አያይዘውም ወደፊት ብፁዕነታቸው በሚያቀርቡት ምክረ ሐሳብ በመነሣት በቀጣይ በጋራ የምንሠራቸውን የምንወስን ይሆናል ሲሉ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል::
የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት/ EOTC Broadcasting Service Agency/
