በክቡር ዋና ሥራ አስኪያጅ የተመራ ከፍተኛ የሥራ ሐላፊዎች ልኡክ የሀገረ ስብከቱ የልሕቀት ማእከል ለማድረግ እየተሠራ በሚገኘው በቂሊንጦ ገላን ጉራ መንበረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴና ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ጉብኝትና ውይይት አካሄደ።
ኅዳር ፪/፳፻፲፱ ዓ/ምበክቡር ዋና ሥራ አስኪያጅ የተመራ ከፍተኛ የሥራ ሐላፊዎች ልኡክ የሀገረ ስብከቱ የልሕቀት ማእከል ለማድረግ እየተሠራ በሚገኘው በቂሊንጦ ገላን ጉራ መንበረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴና ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን ጉብኝትና ውይይት አካሄደ።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ሰሎሞን በቀለ ከሀገረ ስብከቱ ዋና ዋና ክፍል ኃላፊዎች ጋር በመሆን በቂሊንጦ ገላን ጉራ መንበረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴና ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር የመስክ ጉብኝት በማድረግ፣ በደብሩ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችንና የወደፊት ዕቅዶችን አስመልክቶ ውይይት አካሂደዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ሰሎሞን በቀለ፣ የሀገረ ስብከቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ መጋቢ ትፍስት ሙሉጌታ ቸርነት፣ የሀገረ ስብከቱ ዋና ዋና ክፍል ኃላፊዎች፣ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ካህናት ዕዝራ ንዋይ፣ የክፍለ ከተማው የሥራ ኃላፊዎች፣ የደብሩ የሰበካ ጉባኤና የልማት ኮሚቴ አባላት፣ ደብረ ካህናት፣ ዲያቆናትና የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ተገኝተዋል።
በውይይቱም የደብሩ የልማት መሪ ዕቅድ (ማስተር ፕላን) በኢንጂነር ፍቅሩ ቀርቧል። በቀጣይ ለመከናወን የታቀዱ ተግባራትን፣ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችን፣ የልማቱን ዓላማና የሚደርስበትን ግብ በሰፊው አብራርተዋል።
ደብሩ ከ44 ዓመታት በፊት የተመሠረተ ሲሆን፣ በተለያዩ ተፋሰሶችና ሸለቆዎች የተከበበ 14 ሄክታር መሬት ይዞታ አለው። ደብሩ ባለፉት ዓመታት ያለፈባቸው መንገዶች ከባድ ቢሆኑም፣ ቀደምት አባቶች ባሳዩት ብርታትና በአካባቢው ምእመናን ትጋት ይዞታውንና አገልግሎቱን አስጠብቆ እስከ አሁን ማቆየት መቻሉ ተገልጿል።
የመሪ ዕቅዱ ዋና ዓላማ የቂሊንጦ ገላን ጉራ መንበረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴና ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብርን ዘመኑን በዋጀ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ምሰሶዎች ላይ በማቆም፣ ጠንካራ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት፣ የአብነት ትምህርት ቤት፣ ዘመናዊ የትምህርትና የልማት ተቋማትን በመገንባት በአጠቃላይ በሀገረ ስብከቱ “የልሕቀት ማእከል” በማድረግ ለአካባቢው ማኅበረሰብ፣ ለምእመናንና በሀገረ ስብከቱ ለሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት አርአያ ማድረግ ነው።
በመሪ ዕቅዱ የታቀዱት የልማት ሥራዎች የመዋዕለ ሕፃናት መማሪያ ቤት፣ የመዳረሻ መንገድ፣ የአብነት ትምህርት ቤት ወይም ጉባኤ ቤት፣ የካህናት ማረፊያ ሕንፃ፣ የሰንበት ትምህርት ቤትና አዳራሽ፣ የእጓለ ማውታ ማሳደጊያ ማዕከል፣ የከተማ ግብርናና የገቢ ማመንጫ ማዕከላት፣ የቤተ ክርስቲያን ሕንፃ፣ የሕክምና ማስፋፊያ ማዕከላትና የአስተዳደር ቢሮ ሕንፃ ግንባታን ያካትታሉ። እነዚህ የልማት ሥራዎችም በሦስት ምዕራፎች ተከፍለው እንዲከናወኑ ታቅደዋል።
ፕሮጀክቱ ከመንፈሳዊ አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር ለሌሎች ተቋማት አርአያ የሚሆን የሰርቶ ማሳያ ተቋም ለመሆን ያለመ ነው። ፕሮጀክቱ በሥነ ምግባርና በእውቀት የታነፀ ትውልድ ከማፍራት ባሻገር፣ ለማኅበረሰቡ ማኅበራዊ አገልግሎትና የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ለቤተ ክርስቲያኑም ቋሚ የገቢ ምንጭ ለማስገኘት ያለመ መሆኑ በሪፖርቱ ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ሰሎሞን በቀለ በዚሁ ወቅት በሰጡት አስተያየት፣ ይህንን ቦታ ለቤተ ክርስቲያን የሰጡት ሰዎች ከግል ጥቅማቸው ይልቅ ለተቋሙ የወደፊት ዕድገት ቅድሚያ መስጠታቸው የሚያስመሰግን ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
ለአካባቢው ካህናት፣ ለማኅበረሰቡ፣ ለሰበካ ጉባኤ አባላትና ለልማት ኮሚቴው ያላቸውን ሰፊ ራዕይና ዝግጁነት በማድነቅ፣ ይህም ለፕሮጀክቱ ስኬት ትልቅ አቅም እንደሚሆን አመልክተዋል። ፕሮጀክቱ በግለሰባዊ ፍላጎት ሳይሆን በተቋማዊ አስተሳሰብና በጋራ ትብብር መመራት እንዳለበትም ጠቁመዋል።
ሀገረ ስብከቱም ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በባለቤትነት ተሳትፎ በመሥራት፣ ለፕሮጀክቱ ስኬት አስፈላጊውን አመራርና ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። ፕሮጀክቱ በሀገረ ስብከቱ ከተያዙ የልማት ዕቅዶች አንዱ መሆኑንና በ45ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ በሪፖርት መቅረቡንም አስታውቀዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የሀገረ ስብከቱ የዋና ዋና ክፍል ሐላፊዎች የሰው ልጅ ሕይወት ጊዜያዊ በመሆኑ በተሰጠው ጸጋ በጎ ሥራዎችን መሥራትና በፍቅርና በአንድነት መኖር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የደብሩን ዋና አስተዳዳሪና በጎ ፈቃደኛ አገልጋዮችን ለሚያደርጉት ትጋትና አገልግሎት አድንቀው፣ ፕሮጀክቶቹ ለመጪው ትውልድ ዘላቂ አሻራ የሚያሳርፉ በመሆናቸው የሁሉንም ትብብር እንደሚጠይቁ ገልጸዋል።
ለፕሮጀክቶቹ ስኬትም በሀገረ ስብከቱ ደረጃ ኮሚቴዎችን በማዋቀር፣ የገዳማትና አድባራት ተወካዮች በማሳተፍ፣ በሚዲያ በማስተዋወቅና የባለሀብቶችን ድጋፍ በማሰባሰብ በጋራ መንቀሳቀስ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል። በተጨማሪም በስደትና በግድያ ለሚጎዱ ክርስቲያኖች ድጋፍ ማድረግና በአንድነት መቆም እንደሚገባ አሳስበዋል።
ሊቀ ካህናት እዝራ ንዋይ ፣ የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ሰላም አበበ በአምስት ዓመታት የአገልግሎት ዘመናቸው ለደብሩ ልማት ያሳዩትን ትጋትና ቁርጠኝነት አድንቀዋል። አስተዳዳሪው ከሰበካ ጉባኤውና ከልማት ኮሚቴው ጋር በመተባበር የደብሩን የልማት ሥራዎች ከማስተባበር ባለፈ፣ ለታቀዱት ፕሮጀክቶች እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት እያደረጉ ያሉትን ጥረት ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ደብሩ በክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት በቅድሚያ ከሚደገፉና ትኩረት ከሚሰጣቸው የልማት ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ መሆኑን ገልጸዋል። በቀጣይም የሚጠናቀቁ ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች ለሀገረ ስብከቱ እንዲቀርቡና የሚገባቸውን ድጋፍ እንዲያገኙ የሚያስችል ዝግጅት መኖሩንም አስታውቀዋል። በመጨረሻም ለደብሩ ልማት እየተደረገ ያለውን ጥረት በማድነቅ፣ ክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት በበኩሉ የሚችለውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸው፣ ለተገኙት እንግዶች ምስጋና አቅርበዋል።
በደብሩ የሚገኘውን 139,132 ካሬ ሜትር ስፋት ያለውን ይዞታ ለልማት በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችሉ የልማት አቅጣጫዎችን ለመወያየትና ያለውን ሁኔታ ለመጎብኘት የመስክ ጉብኝት ተካሂዷል። ጉብኝቱ የሀገረ ስብከቱን የልማት ዕቅድ መሠረት በማድረግ፣ ከሰበካ ጉባኤውና ከልማት ኮሚቴው ጋር በመተባበር በደብሩ የሚከናወኑ ቀጣይ የልማት ሥራዎችን ለመለየትና በተቀናጀ መንገድ ለማስፈጸም ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
በደብሩ የተገነባውና በአሁኑ ወቅት አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘውን አዲሱን የመዋዕለ ሕፃናት ትምህርት ቤት የአዲስ አበባ ሥራ አስኪያጅና የሥራ ኃላፊዎች ጎብኝተዋል።
ዘጋቢ ጽናት አስቻለው
ነቢዩ ሚክያስ
