ወገኖቻችንም በቋንቋ እጥረትና በሕግ አማካሪ እጦት ለሞት እንዳይዳረጉ ከአደራ ጭምር እናሳስባለን ፡፡(ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ)

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሳዑዲ ዓረቢያ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው በአስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን በማስመልከት ለኢትዮጵያና ለሳዑዲ መንግሥታት፣ ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት እና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አባታዊ መልእክት አስተላለፉ።
ግንቦት 4 ቀን 2018 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
ቅዱስነታቸው ያስተላለፉት አባታዊ መልእክት እንደሚከተለው ነው፦
መልእክተ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
‹‹ተዘከሩ መቁሓነ ዘከመ ተሞቃሕክሙ ምስሌሆሙ ወእለ ተሣቀዩ ከመ ዘሀለውክሙ በሥጋክሙ፡-
ከእነርሱ ጋር አብራችኋቸው እንደታሰራችሁ ሆናችሁ እስረኞችን ዐስቡ፤ መከራ የጸናባቸውንም በሥጋችሁ ከእነርሱ ጋር እንዳላችሁ ሆናችሁ ዐስቡ››
(ዕብ. 13፡3)
እውነተኛ እምነትም ሆነ ጤናማ አመለካከት የሚመዘነው መከራ ስለሚቀበሉ ሰዎች ሰምቶና አይቶ በዝምታ ባለማለፍ፤ ይልቁንም በእነርሱ ሕመም ውስጥ ራስን በማስገባት በሚሰማው ጥልቅ ኀዘን እና በሚደረገው ድጋፍ ነው፡፡ ይልቁንም በዚች ዓለም የምንኖር ለችግርና ለመከራ ቅርብ እንደመሆናችን የታሰሩትን መጎብኘት፣ የተገፉትን ማጽናናት፣ በስደት ምድር ላይ ሆነው በሞት ፍርድ የሚጨነቁትን ወገኖች ስቃይም እንደራሳችን ስቃይ በመቁጠር ስለእነርሱ ድምፅ መሆንና ማዘን ስንችል በሰማያዊው መንግሥት የማይጠፋ የጽድቅ ዋጋን እናከማቻለን፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን!
እረኛ በበረት ውስጥ ያለችው አንዲት በግ ስትጠፋ ወይም ለአደጋ ስትጋለጥ ዝም ብሎ እንደማያይ ሁሉ፣ በሳዑዲ ዓረቢያ ምድር በሞት ጥላ ሥር ሆነው ‹‹የፍትሕ ያለህ›› እያሉ የሚጮኹ፤ በጭንቀት ቀናትን የሚቆጥሩና ድምፅ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን የተሻለ ኑሮ እናገኛለን ብለው በተሰደዱበት ሀገር ሕይወታቸው በጅምላ ሊቀጠፍ እንደሆነ መረጃውን ከልዩ ልዩ መገናኛ ብዙኃን የተገነዘብን በመሆኑ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ጠቀሜታው የሰው ልጆችን ሕይወት ለመጠበቅ ነውና የኢትዮጵያ መንግሥት በከፍተኛ ደረጃ ከሚገኙ ከሳዑዲ ባለሥልጣናት ጋር በመነጋገር በግፍ የተፈረደባቸው ልጆቻችን የሞት ፍርድ እንዲነሳላቸውና ወደ ሀገራቸው የሚመለሱበት መንገድ ይመቻች ዘንድ የተጀመሩ ሥራዎች ልዩ ትኩረት እንዲሰጥባቸው፤ ወገኖቻችንም በቋንቋ እጥረትና በሕግ አማካሪ እጦት ለሞት እንዳይዳረጉ ከአደራ ጭምር እናሳስባለን ፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ለሰው ልጅ የሰጠው ታላቅ ስጦታ ሕይወት ነው፤ “አትግደል” የሚለው ሕግም በማንኛውም ምድርና ቋንቋ የሚሠራ ሲሆን ፍርድ ያለ ምሕረት ከሆነ አምላካዊ ቁጣን ይጋብዛልና የሳዑዲ ባለሥልጣናት የሁለቱን ሀገራት የቆየ ታሪክና ወዳጅነት አስበው፣ በሞት ፍርድ ጥላ ሥር ላሉት ወገኖቻችን ምሕረትን እንዲያደርጉ፣ ቅጣቱንም ወደ እስራት እንዲቀይሩ በአባታዊ ርኅራኄ እንጠይቃለን ፡፡
ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችም በማያውቁት ቋንቋ እንዲሁም ባልተረዱት የሕግ ሂደት ሞት የተፈረደባቸውን ወገኖች ስቃይ ተመልክተው የፍትሕ መዛባትን እንዲቃወሙና የንጹሐንን ነፍስ እንዲታደጉ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
በመጨረሻም፣ ማንኛውም በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ሰው ሕይወቱ ሊጠፋ አይገባምና ኦርቶዶክሳውያን ልጆቻችን የክርስትናችን አንዱ መገለጫ የአንደኛው ወገን ሕመምን በጋራ መካፈል እንደሆነ ተረድታችሁ ወደ ፈጣሪያችን በጸሎት እንድትማጸኑ፤ መላው ኢትዮጵያውያንም ለመፍትሔው የበኩላችሁን ጥረት እንድታደርጉ ስንል አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን።
እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!
አሜን።
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ግንቦት 4 ቀን 2018 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
© የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት