ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡፡
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
የእግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ፣ የጌታችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አካልና የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የሆነችው ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ሲኖዶሳዊ በመሆኗ አበው ቅዱሳን በፍትሕ መንፈሳዊና በጉባኤ አድያም ዘአንጾኪያ “ወይኩን ሲኖዶስ ዘጳጳሳት ፪ተ ጊዜያተ በበዓመት – የጳጳሳት ጉባኤም በዓመት ሁለት ጊዜ ይሁን” ብለው በደነገጉት ቀኖና መሠረት፤ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የሚመራው፣ የሐዋርያት መንበር ወራሽ የሆነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤውን በኅብረተ መንፈስ ቅዱስ ከሚያዝያ 28 እስከ ግንቦት 6 ቀን 2018 ዓ/ም ድረስ አካሄዷል፡፡
ምልዓተ ጉባኤው ስለ ሀገር ሰላም፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን አንድነት፤ ስለ ሰው ልጅ ሁሉ ደኅንነትና ክብር፣ በአጠቃላይ ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ሰፊ ውይይቶችን በማድረግ ዘመኑን የዋጁ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ ከውሳኔዎቹም መካከል፡-
የቤተ ክርስቲያናችንን አንድነት መጠበቅና ማስጠበቅ የቅዱስ ሲኖዶስ ተግባር በመሆኑ ጥንታዊትና ሐዋርያዊት የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን በአንድነቷና በሉዓላዊነቷ እንደተረከብናት ለወደፊቱም ሉዓላዊ ክብሯ ተጠብቆ እንድትቀጥል በምልዓተ ጉባኤው የተሠየመው በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የሚመራው “የሀገራዊ ሰላምና የቤተ ክርስቲያን አንድነት” ኮሚቴ ሥራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ፍጹም ሰላማዊ ሆኖ በተረጋጋ መንገድ እንዲካሄድ፣ ለሀገር ሰላምና ለሕዝብ አንድነት በሚጠቅም ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምትጸልይ ሲሆን ምርጫው በሁሉም ወገን ለኢትዮጵውያን ዘላቂ ሰላምንና መረጋጋትን የሚያስገኝ ሆኖ እንዲፈጸም ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንዖት ያሳስባል፡፡
ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የአርሲ ሀገረ ስብከትን በሊቀ ጵጵስና በቋሚነት እንዲመሩ፣ ሕዝቡን እንዲያጽናኑ እየደረሰ ያለውን ችግር ከቋሚ ሲኖዶስና በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ከሚመራው የሰላም ኮሚቴ ጋር በመሆን የሚመለከተውን የመንግሥት አካል በማነጋገር ዘላቂ መፍትሔ እንዲያፈላልጉ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ወስኗል፡፡
ከጥንት ጀምሮ “ቅዱስ ሲኖዶስ” በሚል ርእስ እየተዘጋጀ ይታተም የነበረው ታሪካዊ መጽሔት የቅዱስ ሲኖዶስ ቀኖናዊ ውሳኔዎችን በማካተት በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት አስፈጻሚነት ሕትመቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
የቤተ ክርስቲያናችንን ደንቦች መመሪያዎች መርምሮ ማጽደቅ የቅዱስ ሲኖዶስ ሉዓላዊ ሥልጣን በመሆኑ፡-
የስብከተ ወንጌል ሐዋርያዊ ተልእኮ ማስፈጸሚያ ደንብ በብፁዕ አቡነ ማርቆስ ሰብሳቢነት
የአንድነት ገዳማት ኅብረት መተዳደሪያ ደንብ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስና ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ባሉበት በድጋሚ እንዲታይና ሌሎቹም ለውሳኔ የቀረቡ ደንቦች በሊቃውንትና በሕግ ባለሙያዎች ታርመው ለጥቅምት 2019 ዓ/ም ምልዓተ ጉባኤ እንዲቀርቡ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል
የቀድሞው የሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ “የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ”ና “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ” በሚሉ አርእስት አዘጋጅተው ያሳተሟቸው መጻሕፍትን የማሳተምና የማሰራጨት የባለቤትነት መብት ከሚያዝያ 29 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ለዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም እንዲሆን ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
ከተለያዩ አህጉረ ስብከት በቀረቡ ጥናቶችና የማጣራት ውጤቶች መሠረት፡-
የደቡብ ሱዳን ሀገረ ስብከት ከምሥራቅ አፍሪካ ሀገረ ስብከት ጋር ተደርቦ በብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ሊቀ ጳጳስ እንዲመራ፤
ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል ሊቀ ጳጳስ የጋምቤላንና የቤንሻንጉል ጉምዝ አህጉረ ስብከትን ብቻ እንዲመሩ፤
ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጰስ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከትን እንደያዙ እንዲቀጥሉ፤
ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም የቡኖ በደሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቄለም ወለጋ ሀገረ ስብከትን ደርበው በአባትነት እንዲመሩ፣
የኮንታ ዞን ሀገረ ስብከት እንዲሆን የቀረበው ጥያቄ የጸደቀ በመሆኑ ሀገረ ስብከቱ ራሱን ችሎ እንዲደራጅና በብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ሊቀ ጳጳስ እንዲመራ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፤
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የልማት ተግባራትን ምልዓተ ጉባኤው በከፍተኛ ደረጃ በማድነቅ፣ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ/ ዋና ሥራ አስኪያጅ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ሲቲ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ በአባታዊ አመራር የፈጸሙት አስደናቂ የሥራ አፈጻጸም በጉልህ የሚታይ ለውጥ፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የሚጠቅም፣ ሉዓላዊ ክብሯን የሚያስጠበቅ፣ ለሁሉም አበው ምሳሌነት ያለው በመሆኑ ምልዓተ ጉባኤው እጅግ ከፍ ባለ ክብር አመስግኗል፡፡
በዚህም መሠረት በብፁዕ ጠቅላይ ዋና ሥራ አስኪያጁ አባታዊ መሪነት እየተከናወኑ ያሉት ተግባራት ማለትም፡-
የቤተ ክርስቲያንን ቀደምት ሠነዶች በዲጂታል ቴክኖሎጅ እንዲደራጁ የተደረገበት ሥልት ተጠናክሮ እንዲቀጥል፤
ከ1970 ዓ/ም ጀምሮ በመጋዝን ተከማችተው የቆዩ በርካታ ልዩ ልዩ መጻሕፍትን የማሠራጨት ሂደት በተጀመረው መንገድ እንዲጠናቀቅ፤
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የኢንፎርሜሽንና ኮምኒኬሽን ተጠቃሚ እንድትሆን የተጀመረው ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂ በሁሉም የቤተ ክርስቲያናችን መዋቅር በየደረጃው ተጠናክሮ ተግባራዊ እንዲሆን፤
በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥር የተጀመሩ የሕንፃ ግንባታዎችና አጠቃላይ የልማት ሥራዎች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ሁሉም አህጉረ ስብከትና ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦና ትብብር እንዲያደርጉ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንዖት ያሳስባል፡፡
በሰሜን አሜሪካ የሰሜን ካሊፎርኒያ፣ ኔቫዳና አሪዞና ሀገረ ስብከት ኆኅተ ሰማይ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስና ቅድስት አርሴማ ገዳም የመንፈሳዊ ኮሌጅ፣ የአብነት ት/ቤት ሥርዓተ ትምህርት የቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፣ ቀኖና፣ ታሪክና ትውፊት በጠበቀ መልኩ ተጠናክሮ መዋቅራዊ ተጠሪነቱም በአግባቡ ተጠብቆ ሥራ ላይ እንዲውል ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ያቀረበውን የ2019 ዓ/ም በጀት በማጽደቅ በተገቢው መንገድ ሥራ ላይ እንዲውል ምልዓተ ጉባኤው ወስኗል፡፡
በመጨረሻም ቅዱስ ሲኖዶስ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በተነጋገረባቸው ጉዳዮች በትኩረት የተወያየው የቤተ ክርስቲያናችንን ሁለንተናዊ ዕድገትና ተቋማዊ ሕልውና ስለማስጠበቅ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ሀገራችንን ጨምሮ በመላው ዓለም እየታየ ያለው ግጭትና የሰላም መታጣት በእጅጉ አሳስቦታል፡፡
በመሆኑም ስለ ዓለምና ስለ ሀገራችን ሰላም፣ ስለ ሰው ልጆች ደኅንነት፣ በየቦታው በሃማኖታቸው ምክንያት መከራ የሚደርስባቸውን በየቦታው የሚገኙና ግጭት ባለባቸው ቦታዎች ያሉ ኦርቶዶክሳውያንን በማሰብ በመጪው የ2018 ዓ/ም ጾመ ሐዋርያት በመላው ዓለም ባሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት፣ አድባራትና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ጸሎተ ምሕላ እንዲደርስ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
በመላው ዓለም፣ በደቡብ አፍሪካና በሳውዲ ዐረቢያ የሚኖሩ ዜጎቻችን ሰብዓዊ መብት እንዲከበር፣ የርኅራኄ ምሕረትና ፍትሕ እንዲያገኙ የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ክትትል እንዲያደርጉ ቅዱስ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ጥሪውን በማቅረብ ለሰባት ቀናት ሲያካሂድ የሰነበተውን ቀኖናዊ ጉባኤ ዛሬ ግንቦት 6 ቀን 2018 ዓ.ም. በጸሎት አጠናቋል፡፡
“እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ”
አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም
ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት
አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ
ግንቦት 6 ቀን 2018 ዓ/ም
