የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አስተዳደር ጉባኤ የሚታይ የሚጨበጥ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አሳለፈ።
ነሐሴ ፳፮/፳፻፲፰ ዓ/ም አ/አ/ሀገረ ስብከት ሚዲያየአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አስተዳደር ጉባኤ በተቋሙ የሚታይ የሚጨበጥ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አሳለፈ።
በቅርቡ የተመደቡት መልአከ ብርሃን ሰሎሞን በቀለ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ አዲሶቹንና ነባር የዋና ክፍል ሐላፊዎች ጋር መደበኛ የአስተዳዳር ጉባኤ ማካሔድ ጀምረዋል።
በቋሚ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መነሻነት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የተመደቡ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ሰሎሞን በቀለ ከአዲሶቹና ከነባሮቹ የዋና ክፍል ሐላፊዎች ጋር በመሆን መደበኛ የአስተዳዳር ጉባኤ ጀምረዋል።
የጉባኤ ላይ ነባሮቹ የሥራ ሐላፊዎች ለአዲሶቹ የዋና ክፍል ሐላፊዎች እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት መልካም አገልግሎት ምኞት የተመኙ ሲሆን በአንድነትና በኅብረት የቤተ ክርስቲያን የጣለችብንን አደራ ለመወጣት የሚቻለንን ሁሉ እናደርጋለንም ብለዋል።
አዲሶቹ የሥራ ሐላፊዎች በበኩላቸው ስለተደረጋላቸው መልካም አቀባበል አመስግነው አገባባችን መልካም እንደሆነ በሥራችን ለመግለጥ የእግዚአብሔርን ቸርነት ተማምነን የበኩላችንን እንወጣለን ብለዋል።
ክቡር መልአከ ብርሃን ሰሎሞን በቀለ በበኩላቸው “ሰማይ ሩቅ አደራ ጥብቅ” እንደሚባለው ከቤተ ክርስቲያን የተሰጠንን ሕያው ተልእኮ ለውጥ በማምጣት ያከበረችንን ቤተ ክርስቲያን፣ የመረጡንን አባቶችን፣ ተስፋ ያደረጉንን የሀገረ ስብከቱንና የአብያተ ክርስቲያናቱን አገልጋዮች እንዲሁም ቡሩካን ምእመናንን ማስደሰት ይገባናል ብለዋል።
ስለሆነም ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ድጋፍ ሊሆኑ የሚችሉ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን፣ ቃለ ዓዋዲን፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የሠራተኛ መተዳደሪ ደንብንና የሀገረ ስብከቱን ደንብ በተጨማሪም በቅዱስ ሲኖዶስና ቋሚ ሲኖዶስ የተሰጡ መመሪያዎችን ጋር በማገናዘብ መፍትሔ የሚሰጥና ሐላፊነትነ ከተጠያቂነት ጋር የጣመረ የውስጥ አሠራር System ለመዘርጋት ውሳኔ አሳልፏል።
