የገዳመ ኢየሱስ አዲሱ ሕንጻ ቤተክርስቲያን በብፁዓን አባቶችን ቡራኬ ተመረቀ
ኢኦተቤ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ
ግንቦት ፲፪/፳፻፲፰ ዓ/ም
የገዳመ ኢየሱስ አዲሱ ሕንጻ ቤተክርስቲያን በብፁዓን አባቶችን ቡራኬ ተመረቀ።
በሥርዐተ ቡራኬ ቤተ ክርስቲያኑ መርሐ ግብር ላይ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባና ሀዲያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ብፀለዕ አቡነ ናትኤል የቅድስት ሀገረ ኢየሩሳሌም ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ፣ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል በሰሜን አሜሪካ የኦሀዮና አካቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንትና የደቡብ ኦሞና አሪ ዞኖች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የሀገረ ስብከቱ የሥራ ሐላፊዎች ፣ ሊቀ ሊቃውንት አባ ጥዑመ ልሳን አዳነ የክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ መልአከ ገነት አበበ ምትኩ የደብሩ አስተዳዳሪ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በርካታ ምእመናንና ምእመናት ተገኝተዋል።
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ፣ በቂርቆስ ልደታና አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥር የሚገኘው የገዳመ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተው በ፲፱፻፹፫/1983/ ዓ/ም እንደሆነ ታሪክ ያስረዳል።
ይሁንን እንጂ ቦታው በተለይም 1968 ዓ/ም ጀምሮ የደብረ ቀራንዮ መድኃኔዓለም፣ የደብረ ገሊላ ቅዱስ አማኑኤል፣* የደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ እንዲሁም የጎላ ጽርሐ ጽዮን ቅዱስ ሚካኤል ታቦታት ለጥምቀት የሚያድሩበት ባሕረ ጥምቀት በመሆን አገልግሏል።
ዛሬ በብፁዓን አባቶችን ቡራኬ የተመረቀው አዲሱ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ጥቅምት 4/2005 ዓ/ም በብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ሊቀ ጳጳስ ቡራኬ የመሠረት ዲንጋይ የተቀመጠ ሲሆን ታኅሣሥ 13/2006 ቦታው ለግንባታ ዝግጁ መሆኑን በጸሎተ ማርያም ተጠይቆ የካቲት 6/2006 ዓ/ም የሕንጻ ግንባታው ተጀምሯል።
ሕንጻው በ1500 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን በመስቀለኛ ቅርጽ የተሠራ ቤተ ክርስቲያን ነው።
የሕንጻ ቤተ ክርስቲኑ የውጭ በሮች በጥንታዊ ጥበብ ያሸበረቁ በሁሉም አቅጣጫ ሦስት ሦስት በሮች ያሉት ሲሆን ልብን ከቅዱሳን መጻሕፍት ጋር የሚያገናኙ ቅዱሳት ሥዕላት ተሰለውበታል።
ዛሬ ለገዳመ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ካህናትና ምእመናን ልዩ ደስታ ነው።
በዚህም የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ገነት አበበ ምትኩ የሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ለበርካታ ዓመታት ሲታነጽ የቆየ መሆኑን በመገንዘብ ቡራኬው እንዲፈጸም የሚመለከታቸውን አካላት ለአንድ ሐሳብ እንዲገዙ በማድረግ ከፍተኛ ሥራ መሥራታቸው ተገልጿል።
የደብሩ አስተዳዳሪ በበኩላቸው ለምርቃት በመብቃት ደስታቸውን ገልጸው መልካም አስተዋጽኦ ላደረጉ ከብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ጀምሮ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ የደብሩ ሕንጻ ኮሚቴ፣ ሰበካ ጉባኤ፣ ሊቃውንት፣ ምእመናንና የደብሩ ሰንበት ትምህርት ቤት እንዲሁም የአካባቢው ወጣቶችን አመስግነዋል።
በመቀጠልም በሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ የበኩላቸውን ድርሻ ለተወጡ አካላት የእውቅና የምስጋና ሸልማት ከደብሩ ተበርክቶላቸዋል።
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ባዩትና በተመለከቱን ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ መደሰታቸውን የገለጹ ሲሆን እዚህ እንዲደርስ የተባበሩትን፣ ከሌላቸው ለሰጡት፣ ሁልጊዜ ላልታጠፉ የስጦታ እጆች አመስግነው እግዚአብሔር በበረከት ይጠብቃችሁ ብለዋል።
ይህንን ለማከናውን የመሪው ጥበብ የካህናቱና የምእምናኑን በተለይም የሕንጻ ኮሚቴውና ሰበካ ጉባኤው እንዲሁም የሰንበትና የአካባቢው ወጣቶችን ስምምነትና ለቤተ ክርስቲያን ዘለዓለማዊ ተልእኮ ልብን የመስጠት ውጤት ነው ብለዋል።
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አባታዊ ቃለ በረከትና የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ትምህርተ ወንጌል የሰጡት ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ሊቀ ጳጳስ ቤተ መቅደስ የሚሠራው እኛ እንድንባረክበትና በበረከት እንድንጎበኝበት በመሆኑ በብዙ መድከማችን ለዝናና ለስም ሳይሆን ለቅድስና ነው ብለዋል።
ዘለዓለማዊ ቃልኪዳን ያላት ይህች ቤተ ክርስቲያን ለእኛ የኃጢአት ማስተስሪያ፣ ከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኝባት የቅድስና ሙዳይ የሕይወት መገኛ በመሆኗ የሠራነው ሥራ በምድርም በሰማይም ዋጋ ያለው ነው ብለዋል።
እናም በሠራነው ቤተ መቅደስ እኛም መልካም በመሆንና በንስሐ ቤተ መቅደስ መሆናችን ልንሰብክ ይገባል ብለዋል።
በመጨረሻም አቡነ ሳሙኤል ሊቀ ጳጳስ በበኩላቸው ከብዙ ዓመታት በፊት በ1985 ዓ/ም የደብሩ አስተዳዳሪ እንደነበሩ አስተውሰው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ በዚህ መልክ ተሠርቶ በመጠናቀቁ ደስታቸውን የገለጹ ሲሆን እንኳን ለዚህ አበቃችሁ ብለዋል።
የሥርዐተ ቡራኬው በዓል በብፁዕነታቸው ቡራኬና ጸሎት ተጠናቋል።
