“ዘፍልሰተ ሥጋከ ኮነ በግንቦት {የሥጋህ “የዐፅምህ” ፍልሰት በግንቦት ወር ሆነ) ቅ/ያሬድ
በመልአከ ምሕረት አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ (ቆሞስ)
የዐዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ
እንኳን ለጻድቁ አባታችን ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት ዓመታዊ የፍልሰተ ዐፅም በዓል በሰላም አደረሳችሁ!
መፍቀሬ ጥበብ ሰሎሞን፦ “የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው” ምሳሌ 10፥7 በማለት በተናገረው አምላካዊ ቃል መሠረት ጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት በየዓመቱ ግንቦት 12 ቀን ፍልሰተ ዐፅማቸው የሚከበር መሆኑ ግልጽ ነው።
1. ልደት (መወለድ)
ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በኢትዮጵያ በሰሜን ሸዋ (ቡልጋ) ልዩ ስሙ ኢቲሳ በተባለ ቦታ ከአባታቸው ከካህኑ ጸጋ ዘአብ እና ከእናታቸው ከቅድስት እግዚእ ኀረያ መጋቢት 24 ቀን ተፀንሰው ታኅሣሥ 24 ቀን በ1197 ዓ.ም ተወለዱ።
✍️ በተወለዱ በሦስተኛው ቀን “አሐዱ አብ ቅዱስ፣ አሐዱ ወልድ ቅዱስ፣ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ” በማለት ቅድስት ሥላሴን አመስግነዋል።
2. ዕድገትና ትምህርት
በመጀመሪያ ስማቸው “ፍሥሐ ጽዮን” ይባል ነበር። በአባታቸው አማካኝነት የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት (ብሉያትና ሐዲሳትን) በሚገባ የተማሩ ሲሆን፣ በሥጋዊው ጎዳና ደግሞ እንደ ዘመኑ ወጣቶች ፈረስ መጋለብንና አደንን ያውቁ ነበር። ዲቁናን ከአባ ጌርሎስ ተቀብለዋል። በኋላም ጌታችን በክብር ተገልጦላቸው ስማቸውን “ተክለ ሃይማኖት” (የሃይማኖት ተክል) በማለት ለውጦታል።
3. ገቢረ ተአምር (ድንቅ ሥራዎች)
ጻድቁ አባታችን በሕይወት ዘመናቸው በርካታ ተአምራትን አድርገዋል።
• የጣዖት ዛፍ መቁረጥ፦ በዳሞት (ወላይታ) ዲያብሎስ አድሮበት ሕዝቡን ያስት የነበረውን ትልቅ ዛፍ በጸሎታቸው ከሥሩ ነቅለውታል።
• ሞቶሎሚን ማስተማር፦ አላዊ የነበረውን ንጉሥ ሞቶሎሚን በተአምራትና በትምህርት ወደ ክርስትና መልሰዋል።
• የአውሬውን ራስ መቀጥቀጥ፦ በወንጌል ኃይል የዘንዶውን (ዲያብሎስን) ራስ ቀጥቅጠው አጥፍተዋል።
4. ትምህርትና ምንኩስና:-
ጻድቁ ለኢትዮጵያ “ብርሃን” ተብለው ይጠራሉ፤ ምክንያቱም በሀገራችን ተዘዋውረው ሕዝቡን ከክህደት ወደ ሃይማኖት መልሰዋል። በደብረ ዳሞ አባ ዮሐኒ ዘንድ መነኩሰው፣ በኋላም በደብረ ሊባኖስ ገዳምን መሥርተው ለብዙዎች መምህርና አባት ሆነዋል።
5. ዕረፍትና ፍልሰተ ዐፅም:-
ጻድቁ አባታችን በ99 ዓመታቸው በነሐሴ 24 ቀን በ1296 ዓ.ም ዐርፈዋል። ካረፉ ከ57 ዓመታት በኋላ በዕጨጌ ሕዝቅያስ ዘመን፣ ጌታችን በገባላቸው ቃል ኪዳን መሠረት ዐፅማቸው ከደብረ አስቦ ወደ ደብረ ሊባኖስ ግንቦት 12 ቀን ፈልሷል።
✍️ ቅዱስ ያሬድ፦ “ዘፍልሰተ ሥጋከ ኮነ በግንቦት፤ ከመ ትንሣኤሁ ለክርስቶስ በጽባሕ፤ ጸሊ በእንቲአነ ተክለ ሃይማኖት ጻድቅ፤ ከመ ያድኅነነ እምኵሉ እኩይ {የሥጋህ/የዐፅምህ ፍልሰት እንደ ክርስቶስ ትንሣኤ በማለዳ በግንቦት ወር ሆነ፤ ጻድቁ ተክለ ሃይማኖት ሆይ ከክፉ ሁሉ ያድነን ዘንድ ስለ እኛ ጸልይ} በማለት የጻድቁን ዐፅም ፍልሰት ከክርስቶስ ትንሣኤ ጋር በማመሳሰል ስለእኛ ይማልድልን ዘንድ በመመኘት ያመሰግኑበታል።
ክርስቶስ ለዓለም ድኅነት እንደተነሣ፣ የጻድቁ ዐፅም መፍለስም ለምእመናን የቃል ኪዳን በረከትና የምሕረት ምልክት ነው።
በዚህ ታላቅ ዕለት፦
• የጻድቁ ድንቅ ሕይወትና ገድል ይነገራል፤
• ከቅዱስ ያሬድ ድርሰት “ዘፍልሰተ ሥጋከ ኮነ በግንቦት” በሚል ዜማ ዚቅና ማኅሌት ይቆማል፤
• በጻድቁ ደጅ ተገኝተው የቃል ኪዳኑን በረከት ምዕመናን ያገኛሉ።
“የአባታችን የቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ጸሎትና በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን!” አሜን
ቅድስት ሀገሬ ኢትዮጵያ!!!
የወለድሻቸው ልጆችሽ ይውለዱሽ!!!
ልጆችሽ ይሟገቱልሽ እንጂ አይሞግቱሽ!!!
በስደት ያሉ ልጆችሽ በበረከት ይመለሱልሽ!!!
ድንበርሽን እሳት መሀልሽን ገነት አድርጐ የዓለም ማረፍያ ያድርግሽ አሜን
በመልአከ ምሕረት አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ (ቆሞስ)
የዐዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ
