በአፍሪካ ኅብረት ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ለካህናት የተሰጠው የአቅም ማሳደጊያ ሥልጠና ተጠናቀቀ።
ሐምሌ ፲፱ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም የአ/አ ሀገረ ስብከት ሚዲያበአፍሪካ ኅብረት ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ለደብሩ ካህናት ለሦስት ተከታታይ ቀናት ሲሰጥ የነበረው የአቅም ማሳደጊያ ሥልጠና በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁ ተገለጸ።
የደብሩ አስተዳደር እንዳስታወቀው፣ የመንፈሳዊ አገልግሎት ልማት የሚለካው በሕንፃ ግንባታ ብቻ ሳይሆን በዋነኝነት በሰው ኃይል ግንባታና ምዕመናንን በዕውቀት ወደ ቤተ ክርስቲያን በማቅረብ እንደሆነ በመታመን ሥልጠናው መዘጋጀቱን ተገልጿል።
በመግለጫው መሠረት፣ ካህናት በቂ ዕውቀት ሲጨብጡ ምዕመናንን በተግባር ማስተማር እንደሚችሉና ይህም ክርስቲያኖች በቁጥርም ሆነ በሃይማኖታዊ ዕውቀት እንዲበዙ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ተጠቁሟል።
የሥልጠናውን አስፈላጊነት በመገንዘብ የሦስቱን ቀናት መርሐ ግብር ሙሉ ወጪ ለመሸፈን ስፖንሰር ያደረጉት የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ዋና ጸሐፊ ሊቀ ኅሩያን ይልማ ጌታሁን መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፣ የሰጡት ድጋፍ ሥልጠናው በተሳካ ሁኔታ ወደ ሥራ እንዲገባ አስችሏል ተብሏል።
ሥልጠናው ካህናት ቀደም ሲል የነበራቸውን ዕውቀት በማዳበር ለምዕመናን ተደራሽ የሆነ ትምህርት እንዲሰጡ ታስቦ የተዘጋጀ ሲሆን፣ በስልጠናውም ላይ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን መምህራን ተጋብዘው በሚከተሉት አምስት ዋና ዋና ርእሰ ጉዳዮች ላይ ትምህርት ሰጥተዋል፦
1.ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን
2.ዕቅበተ እምነት
3.ትምህርተ አበ ነፍስ
4.ተልዕኮን መወጣት
5.የሰው ኃይል አስተዳደር ስልጠና ተሰጠዋል።
የደብሩ ዋና ጸሐፊ መጋቢ ጥበብ ሰናይ አየለ ሥልጠናው በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን በመግለጽ፣ ለዝግጅቱ ድጋፍ ላደረጉት የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ሰለሞን ዘነበ፣ ለአባቶች፣ ለአስተማሪዎች እና ለሁሉም ተባባሪዎች ምስጋና አቅርበዋል።
በተለይም የሊቀ ኅሩያን ይልማ ጌታሁን የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ዋና ጸሐፊን አስተዋጽኦ በማድነቅ፣ የሰጡት ድጋፍ በተሳታፊ ካህናት አገልጋዮች ሞራልና በአገልግሎት ቁርጠኝነት ላይ በጎ ተፅዕኖ ማሳደሩን ገልጸዋል።
በመጨረሻም በመርሐ ግብሩ ማኅበረ ካህናቱ በሥልጠናው ያገኙትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ አገልግሎታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ቃል በመግባት መጠናቀቁ ተገልጿል።
ዘጋቢ ጽናት አስቻለው
በረከት ኃይለ ሚካኤል
