ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ሳዊሮስ እና ብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ አቡነ ዲዮስቆስ በማኅበረ ቅዱሳን ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ በመገኘት አባታዊ መልእክት አስተላለፉ።
ነሐሴ 23 ቀም 2018 ዓ.ምብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ሳዊሮስ እና ብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ አቡነ ዲዮስቆስ በማኅበረ ቅዱሳን የዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ በመገኘት አባታዊ መልእክት አስተላለፉ።
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣የደቡብ ምዕራብ ሸዋና ሸገር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በማኅበረ ቅዱሳን 17ኛ ዓለም አቀፍ ጠቅላላ ጉባኤ በተገኙበት ወቅት ባስተላለፉት መልእክት ማኅበረ ቅዱሳን ከገጠር እስከ ከተማ፣ከሀገር ውስጥ እስከውጭ ሀገር ብዙ ሥራ ይሰራል። ብዙ ፈተና አልፎ ለዚህ መድረስ ቀላል አይደለም ስንተባበርና አንድ ስንሆን ደግሞ ብዙ እንሰራለን ችግሮችንም መቅረፍ እንችላለን ብለዋል፡፡
ብፁዕነታቸው ሥራችሁ የሰመረ ነው ብዙ እያገለገላችሁ ነው፡፡ ሁሉን ትታችሁ ቅድሚያ ለቤተ ክርስቲያን ሰጥታችሁ እዚህ ተገኝታችሁ በመወያየታችሁ ለቤተ ክርስቲያን ትልቅ ጉልበት ትልቅ ሥራ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በቅዱስ ሲኖዶስ መልካም ፍቃድ የተበላሸውን ለማቀናት እየሞከርን ስለሆነ ደግፉን፣አብረን እንቁም፣አብረን እንሥራ፡፡ የበለጠ አንድ ስንሆን ድግሞ ቤተ ክርስቲያንን እናሻግራለን በማለት አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ አቡነ ዲዮስቆሮስ በበኩላቸው ማኅበረ ቅዱሳን ከተመሠረተ ጀምሮ ለ34 ዓመታት በገጠር፣ገዳማት ፣አብነት ት/ቤቶች፣በካህናት ማሠልጠኛዎችና በሌላም አገልግሎት መንፈሳዊ ሠራተኛ ሁኖ ሲሠራ ቆይቷል ያሉት ብፁዕነታቸው ይህንንም ሁላችንም በየቦታው ስንመሰክር ኑረናል፡፡
የአባቶቻችሁ ልጆች በመሆናችሁ አባቶችን በማክበር፣ በጋራ በመሮጥ፣ቤ/ክ በመውደድና ጥብቅና በመቆም አገልግሉ ሲሉም አባታዊ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ችግር የለም ባንልም የውስጣችንን ችግር በውስጣችን መፍታት አለብን፤ ሁላችንም ተቀራርበን በቤተ ክረስቲያንን ድርሻችንን አውቀን ስናገለግል ውጤታማ እንሆናለን በማለትም ገልጸዋል።
ይህ መንፈሳዊ ሠራዊትም ሕገ ቤተ ክርስቲያንን የሚያስጠብቅ መሆን አለበት በማለትም አጽዕኖት ሰጥተዋል፡፡
© Mk TV
