የደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን በኮሪደር ልማቱ ምክንያት የተወሰደበትን ቦታ ምትክ 3000 ካሬ ሜትር ማግኘቱን የደብሩ አስተዳዳሪ ገለጹ።
ሐምሌ ፲/፳፻፲፰ ዓ/ም የአ/አ/ሀገረ ስብከት ሚዲያየደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን በኮሪደር ልማቱ ምክንያት የተወሰደበትን ቦታ ምትክ 3000 ካሬ ሜትር ማግኘቱን የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ሰላም ዓይነ ኩሉ ታደሰ ገለጹ።
የኮሪደር ልማቱን ተከትሎ የተወሰደውን የደብሩ ሕጋዊ ይዞታ ከ2017 ዓ/ም ጀምሮ ምትክ ቦታ እንዲሰጥ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ጥያቄ ሲቀርብ የቆየ ሲሆን በተለይም ከታኅሣሥ 1/2018 ዓ/ም ወዲህ ከፍተኛ ክትትል ማድረጋቸውንና ከወራት በኋላም ጥሩ ምላሾች እንዳገኙ የደብሩ አስተዳዳሪ ተናግረዋል።
በመሆኑም በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 ቡልጋሪያ ተብሎ በሚጠራው ሠፈር 3000 ካሬ ሜትር ለደብሩ እንዲሰጥ የሚመለከተው የመንግሥት አካል መስጠቱን አክለው ገልጸዋል።
ከበርካታ ጊዜያት በኋላ ምትክ ቦታው በመገኘቱ የደብሩ ማኅበረ ካህናትና ማኅበረ ምእመናን በእጅጉ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
በዚህ ምትክ ቦታ በማግኘት ጉዞም ላይ የሕዝብ ሐላፊነታቸውን በቀናናት ለተወጡ የከንቲባ ጽ/ቤት ጀምሮ የመሬት አስተዳዳርና ልማት ቢሮ እንዲሁም በሁሉም አቀፍ ትብብራቸውን ላሳዩን የመንግሥት መሥሪያ ቤት የሥራ ሐላፊዎችና ለወጡ ለደከሙ የሰማዕቱ የቅዱስ እስጢፋኖስ ወዳጆች ከፍተኛ ምስጋና አቀርባለሁ ብለዋል።
በተገኙው የምትክ ቦታ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ጥናትን መሠረት በማድረግ ዘመኑን የዋጀና የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ የሚደግፍ የራስ አገዝ ልማት የሚሠራበት መሆኑን አብራርተዋል።
ደብሩ ቀደም ባለው ጊዜ ስመ ገናና ባለ ሠፊ አገልግሎት የነበረ ሲሆን የአካባቢው ምእመናን በልማት ምክንያት ወደ ሌላ አካባቢ በመሄዱና በሌሌች ተያያዥ ምክንያቶች የቀደመውን ዝና ለመመለስ ተግዳሮት ላይ የቆየ ሲሆን በአሁኑ ሰዓትም የትናትናው የደብሩን ዝናና ክብር በሚመጥን አገልግሎት ለመስጠት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የደብሩ አስተዳደሪ መልአከ ሰላም ዓይነ ኩሉ ታደሰ ገልጸዋል።
የደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን በመስቀል ዓደባባይ የሚገኝ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ በንግሥት ዘውዲቱ ዘመነ መንግሥት በ፲፱፻፱ ዓ/ም የተመሠረተ ቤተ ክርስቲያን ነው።
በዚያን ጊዜም ዘመኑ በፈቀደው መልክ የቤተ ክርስቲያኑ ሕንጻ ተጠናቆ ሲገለገልበት ሳለ በጣልያን የወረራ ዘመን፣ በ፲፱፻፴፪ ዓ/ም ባልታወቀ ምክንያት የእሳት አደጋ ደርሶበት ሕንጻው ተቃጠለ።
ከፋሺስት ወረራ በኋላ የአሁኑ ሕንጻ ግንባታ ፍጻሜ አግኝቶ
ጥቅምት ፲፯ ቀን ፲፱፻፶፫ ዓ/ም ቅዳሴ ቤቱ የግብጽ ኮፕት ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቄርሎስ ፮ኛ በተገኙበት ቡራኬ መፈጸሙን የደብሩ ታሪክ ያመለክታል።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ አገልግሎት/Addis Ababa Diocese Media Service
