የ፳፻፲፱ የምሕረት ዓመትን አስመልክቶ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የእንኳን አደረሰዎ መርሐ ግብር በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ተከናወነ።
ከዘመነ ማርቆስ ወደ ዘመነ ሉቃስ መሻጋገር አስመልክቶ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የእንኳን አደረሰዎ መርሐ ግብር መልእክት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት ተካሄደ።በመርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ሳዊሮስ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የመንበረ ፓትርያርክ ምክልት ዋና ሥራ አስኪያጆች፣ የሃይማኖት ተቋማት ጠቅላይ ጸሐፊ፣ የተለያዩ እንግዶች፣ የመምሪያ ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ሰሎሞን በቀለ፣ የሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍል ኃላፊዎች፣ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ ዋና ጸሐፊዎች ፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እና ሰንበት ተማሪዎች ተገኝተዋል።
በመርሐ ግብሩ ጸሎተ ወንጌል በደብረ ምጥማቅ ሰአሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን የደረሰ ሲሆን፣ በታዕካ ለማርያም ገዳም ሊቃውንትና የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማዕከላውያን መዘምራን ዝማሬ ቀርቧል።
በመቀጠልም በጋሞ ኦርቶዶክሳውያን በጋሞኛ ቋንቋ መዝሙር ቀርቦ በማስከተልም በደብረ ምጥማቅ ሰአሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን የቅኔ መምህር መምህር ፈቀደ እና የታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም ቤተ አስተዳዳሪ ሊቀ ሊቃውንት አባ ተክለሃይማኖት ወልዱ ቅኔ ተበርክቷል።
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የአዲሱን ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።
አክለውም በ2018 ዓ.ም. በቅዱስነታቸው ጸሎትና መመሪያ ሰጪነት በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸው፣ በዓመቱ የተከናወኑ ዋና ዋና ሥራዎችንም ዘርዝረዋል።
ከእነዚህም የጠቅላይ ቤተ ክህነት ግቢን ማስፋትና ማስዋብ፣ የቤተ ክርስቲያን ይዞታዎችን ማስከበር፣ በፒያሳ የነበረውን ቦታ በተመለከተ አዳዲስ ተተኪ ቦታዎችን ለማግኘት የተደረገው ጥረት እና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተከናወኑ የዘመናዊ አስተዳደር ሥራዎችን ጠቅሰዋል።
ለዚህም ክብርት ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤን ድርሻቸው ሰፊ በመሆኑ ምስጋና ይገባቸዋል በማለት አመስግነዋል።
የተሰጠን ጊዜ ዕድል የሕይወት ዕድል ነው ከተጠቀምንበት ድል እናገኛለን ካበከነው ደግሞ ዕዳ ይሆንብናልና በአግባቡ መጠቀም ይኖርብናል ብለዋል።
በመሆኑም በየደረጃው አደራ የተባልነውን የቤተ ክርስቲያን ሐላፊነት በተቀመጠው ጊዜ በፍጥነትና በጥራት መሥራት ይኖርብናል በማለት አሳስበዋል።
አያይዘውም የ2019 ዓመተ ምሕረት፣ ዘመነ ሉቃስ፣ የሰላምና የጤና፣ እንዲሁም ስኬታማ የሥራ ዘመን እንዲሆንልን እመኛለሁ ሲሉ፣ እንዲሁም በሐሰተኛ መረጃና በከፋፋይ አጀንዳዎች ሳይከፋፈሉ፣ በኅብረትና በትጋት መሥራት እንደሚገባም መልእክት አስተላልፈዋል።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር የሚገኙ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና አበምኔቶችም የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።
በመልእክታቸው በቅድሚያም ብፁዕ ቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ “እንኳን ከዘመነ ማርቆስ ወደ ዘመነ ሉቃስ በሰላምና በጤና አሸጋገረዎ” በማለት የአዲስ ዓመት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በቅዱስነታቸው መሪነት አባታዊ ጸሎት አጋዥነት ባሳለፍነው ዓመት ለተሠሩ ሥራዎችና ለመጡ ለውጦች አመስግነዋል።
የቀድሞውን ዘመን በማስታወስ ብቻ ሳይሆን፣ ያለፈውን ዘመን ድክመትና ስህተት በመገምገም፣ ራስን ማረምና ወደ እግዚአብሔር በእውነተኛ ንስሐ መመለስ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
አዲሱ ዓመት የቀን ቁጥር መቀየር ብቻ ሳይሆን፣ ሕይወትን ለማደስ፣ ያለፈውን ለመገምገምና መጪውን ዘመን በተስፋ ለመመልከት የሚያገለግል አዲስ ዕድል መሆኑንም አመልክተዋል።
በተለይም “ዘመኑን ዋጁ” የሚለውን የሐዋርያው ጳውሎስ ቃል በማስታወስ፣ የተሰጠንን ጊዜ በአግባቡ በመጠቀም፣ ለሚጠቅሙ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ሥራዎች መስጠት እንደሚገባ ገልጸዋል።
በመልእክታቸውም በቤተ ክርስቲያን የተሰጠንን ኃላፊነት በትጋት መወጣት፣ ከሥራ ባልደረቦች ጋር በመናበብ መሥራትና ከቅርብ አስተዳደራዊ መዋቅር የሚሰጡ መመሪያዎችን በማክበር ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረውን የሰላም፣ የፍቅር፣ የዕርቅና የአንድነት መልእክት በተግባር ለማሳየት ሁሉም የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
አስተዳዳሪዎቹ በተለይም ምእመናን በቃለ ወንጌል እንዲጸኑ፣ በንስሐ እንዲመላለሱና ቅዱስ ቃሉን በመስማት በሃይማኖታቸው እንዲጸኑ ማብቃት የቤተ ክርስቲያን ዋነኛ ተልዕኮ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከበረከቱ ውጪ ያሉ ምእመናንንም በወንጌል ትምህርት መመለስና የጠፉትን በጎች ወደ ቤተ ክርስቲያን ማምጣት የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን አስገንዝበዋል።
በመልእክታቸው መጨረሻም የዘመን ባለቤት የሆነው እግዚአብሔር ለብፁዕ ቅዱስ አባታችን ረጅም ዕድሜና ጤና እንዲሰጥ፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንንም በሰላምና በአንድነት እንዲጠብቅላት በማለት ገልጸዋል።
በመርሐ ግብሩ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ ሥራን ለማጠናከር የአንድ ፐርሰንት አስተዋጽኦ በአግባቡ እንዲሰበሰብና ለታለመለት ዓላማ እንዲውል አባታዊ መመሪያ መሰጠቱን ተከትሎ፣ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ለጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ለብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ እና ለቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ለብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ በብፁዕ አቡነ ማርቆስ፣ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ፣ ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።
በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ለተደረገው መርሐ ግብር አመስግነው ዘመኑ የሰላም እንዲሆን ሁላችንም ልንጸልይ ይገባል ብለዋል።
አክለውም የሰላም ጉዳይና ተፈጥሯዊ የዝናብ ዕጥረቶች በሕዝባችን ትከሻ ላይ የከበዱ መሆናቸውን አስታውሰው መፍትሔው ሰውኛ አይደለም ከእግዚአብሔር መሆኑ አውቀን ከፊት ይልቅ በጸሎቱ ልንተጋ ይገባል በማለት አባታዊ መልእክት አስተላላፈዋል።
ቀጥሎም በቅዱስነታቸው ጸሎትና ቡራኬ መርሐ ግብሩ ተጠናቋል።
“የቅዱስነታቸው ቡራኬ አይለየን”
ዘጋቢ /ጽናት አስቻለው
ደብረ ምጥማቅ ሰአሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ካቴድራል የዕውቀድ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ አገልግሎት/Addis Ababa Diocese Media Service
