ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ሳዊሮስ የቤተ ክርስቲያንናችን የሕዝብ ግንኙነት አሠራር ዙሪያ ላይ አቅጣጫ ሰጡ።
“እስካሁን የነበረን የሕዝብ ግንኙነት አካሄድ በአብዛኛው ጥቃት ሲሰነዘርብን ምላሽ የመስጠት ወይም የመከላከል ባሕርይ የነበረው ነው። አሁን ግን ይህ አሠራር ሊቀየር ይገባል። እኛ አስቀድመን የቤተ ክርስቲያናችንን እውነት፣ መልካም ሥራና ሰላማዊ ማንነት ለሕዝብ በግልጽና በቅድሚያ ማሳየት አለብን”።ስለሆነም
፩. የቅንጅትና የአንድነት አሠራርን መዘርጋት
የጠቅላይ ቤተ ክህነት የሕዝብ ግንኙነት መዋቅርና የአህጉረ ስብከቱ መዋቅሮች ልክ እንደ አንድ አካል ተሳስረው መሥራት ይኖርባቸዋል። በአንድ አህጉረ ስብከት ላይ የሚፈጠር ፈተና ወይም የሚመዘገብ ስኬት የሁላችንም ነው። መረጃዎችን በፍጥነት በመለዋወጥና በአንድ ድምፅ በመናገር የቤተ ክርስቲያናችንን ጥንካሬና አንድነት ለዓለም ማሳየት ይኖርባችኋል።
፪. ዘመናዊ የዲጂታል ሚዲያዎችን በአግባቡ መጠቀም
የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች የትውልዱ መገናኛና የሐሳብ መገበያያ ሆነዋል። እነዚህን መድረኮች በመልካም ሥነ ምግባር፣ በሳልና በጎ በሆነ ቋንቋ፣ እንዲሁም ማራኪ በሆኑ ዝግጅቶች በመጠቀም የቤተ ክርስቲያናችንን አስተምህሮና መልካም ሥራ ለዓለም ማሳወቅ አለባችሁ። ብዕራችሁ የሚገነባ እንጂ የሚያፈርስ መሆን የለበትም።
፫. ለዕርቅና ለሰላም ቅድሚያ መስጠት
የቤተ ክርስቲያን ድምፅ ምንጊዜም የሰላምና የዕርቅ ድምፅ ነው። በማኅበረሰቡ ውስጥ አለመግባባቶችና ግጭቶች ሲፈጠሩ የእናንተ መግለጫዎችና ዘገባዎች ቁስልን የሚፈውሱ፣ ወንድማማችነትን የሚያጸኑና ሰላምን የሚሰብኩ ሊሆኑ ይገባል።
ብፁዕነታቸውን የሕዝብ ግኑኙነት መምሪያ ባዘጊጀው የሁለት ቀን ሥልጠናና ምክክር ጉባኤ ላይ ካደረጉት የመክፈቻ ንግግር የተወሰደ ነው።
