የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ በዲግሪ መርሐ-ግብር ያሰለጠናቸውን ሊቃውንት በድምቀት አስመረቀ።
ኢኦተቤ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያሐምሌ 4/2018 ዓ/ም
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የዕውቀት ማዕከልና የሊቃውንት መፍለቂያ የሆነው አንጋፋው የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ ለዓመታት በሐዲሳት፣ በብሉያት፣ በሊቃውንት፣ በመነኮሳትና በነገረ መለኮት (ቲኦሎጂ) ትምህርት ዘርፎች ያስተማራቸውን 400 ሊቃውንት በዛሬው ዕለት በደመቀ መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓት አስመርቋል።
በምረቃት ስነስርዓቱ ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀደማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት
ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የቅርሳቅር ወመዘክር ቤተመጻሕፍት ፣ የማኅበራት ምዝገባ ፣ ክትትልና ቁጥጥር መምሪያወች የበላይ ኃላፊ ፣ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የከፋ፣ የሸካ፣ የቤንች ማጂ ፣ የምዕራብ ኦሞ ሊቀ ጳጳስና የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መይፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ኀላፊ፣

ሊቀ ኅሩያን ሰርፀ አበበ የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ዋና ዲን፣
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽሕፈት ቤት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣
የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎችና ሠራተኞች ፣ክቡራን ተመራቂዎችንና የተመራቂ ቤተሰቦች የተገኙ ሲሆን በመንፈሳዊ ኮሌጁ ጸሎተ ወንጌል አድራሽነት በቅዱስነታቸው መሪነት መርሐግብሩ ተከፍቷል።
ይህ የምረቃ በዓል ለኮሌጁ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የከፈተ ልዩ ክስተት ነው። ተቋሙ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በዲግሪ ደረጃ ተማሪዎቹን እንዲያስመርቅ ይፋዊ ፈቃድ በተሰጠው ማግስት የተከናወነ በመሆኑ፣ ለዘመናት ለለፋውና ለደከመው የትምህርት ማኅበረሰብ ትልቅ ብስራት ሆኗል።
ዛሬ የተመረቁትና ለቤተክርስቲያን ብርሃን እንዲሆኑ የተሰናዱት ሊቃውንት፣ በኮሌጁ ቆይታቸው ያካበቱት እውቀትና የመጻሕፍት ምስጢር ጥልቀት ከዲግሪ ማዕረግ በላይ የሆነና ሚዛን የሚደፋ የነበረ ቢሆንም ኮሌጁ ከዚህ ቀደም በዲግሪ ደረጃ እንዲያስመርቅ የሚያስችለው የሕግ ፈቃድ ስላልነበረው እነዚህ የቤተክርስቲያን ዓምዶች የትምህርት ብቃታቸውን የሚመጥን ይፋዊ የምስክር ወረቀት ሳያገኙ ለዓመታት ለመቆየት ተገድደው ነበር። ዛሬ ግን ተቋሙ በቅዱስ ሲኖዶስ ይሁንታ ያገኘውን አዲስ ዕውቅና ተንተርሶ፣ የሊቃውንቱን ልፋትና ደረጃ በጠበቀ መልኩ የዲግሪ ማዕረጋቸውን ሊያቀዳጃቸው ችሏል።
የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ለበርካታ አሠርት ዓመታት የቤተክርስቲያንን ሥርዓትና ዶግማ ጠብቀው የሚያስጠብቁ፣ የወንጌልን ብርሃን የሚፈነጥቁ ታላላቅ ሊቃውንትን፣ መነኮሳትንና ብፁዓን አባቶችን ያፈራ የመንፈሳዊ ዕውቀት አውድማ ነው።
ኮሌጁ ለትውልድ ካበረከተው ዘመን ተሻጋሪ አሻራዎች መካከል በጥቂቱ የብሉያትና የሐዲሳትን ምስጢር ጠንቅቀው የሚያውቁና የትርጓሜ መጻሕፍትን የሚተነትኑ የሊቃውንት መነሻ መሆኑ፣ የቤተክርስቲያንን መዋቅር በዕውቀትና በቅድስና የመሩና እየመሩ ያሉ ታላላቅ አባቶችንና መነኮሳትን ቀርጾ ማውጣቱ፣ በዘመናዊው የነገረ መለኮት (ቲኦሎጂ) ትምህርት የቤተክርስቲያንን ድምፅ ዓለም አቀፍ ለውጦች ጋር የሚያገናኙ ምሁራንን ማፍራቱ ተጠቃሽ ናቸው።
ይህ በዛሬው ዕለት የተከናወነው ታሪካዊ ምረቃ ኮሌጁ ላለፉት ዓመታት ለከፈለው መስዋዕትነት የተሰጠ ትልቅ ምላሽ ሲሆን፣ ተቋሙ ከትውፊትና ከጥንታዊ ዕውቀት ባሻገር በዘመናዊ የትምህርት ደረጃም የቤተክርስቲያንና የሀገር መመኪያ ሆኖ እንደሚቀጥል ማረጋገጫ የሰጠበት ክስተት ሆኖ ተመዝግቧል።
የኢኦተቤ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ
