የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት “ቅድሚያ ለቅዱስወንጌል“ በሚል መሪ ሐሳብ የመጀመሪያን የወንጌል ጉባኤ በአቃቂ መጋላ ደብረ ምሕረት ቅዱስ አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን አከናወነ።ኢኦተቤ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ
ሰኔ ፴/፳፻፲፰ ዓ/ም
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት “ቅድሚያ ለቅዱስ ወንጌል“ በሚል መሪ ሐሳብ የመጀመሪያን የወንጌል ጉባኤ ሰኔ 28/2018 በዕለተ ሰንበት በአቃቂ መጋላ ደብረ ምሕረት ቅዱስ አማኑኤልና ቅዱስ መርቆሬዎስ ቤተ ክርስቲያን አከናወነ።
በጉባኤው ላይ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ ፣ ሊቀ ካህናት ዕዝራ ንዋይ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ሊቀ ጉባኤ አባ ኅሩይ የአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ፣መምህር ሐረገ ወይን የክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት የስብከ ወንጌል ክፍል ሐላፊ፣ መምህራነ ወንጌል እንዲሁም ሊቃውንትና በርካታ ምእመናን ተገኝተዋል።
በጉባኤው ትምህርተ ወንጌል በብፁዕነታቸው ፣ ዝማሬ በሊቀ መዘምራን ቴዎድሮስ ዮሴፍ፣ ቅኔ በደብሩ መምህር እንዲሁም የሥራ ሪፖርት በደብሩ አስተዳደሪ የቅድሚያ ለወንጌል አግልግሎት ገለጻ በሊቀ ካህናት ዕዝራ እንዲሁም ደብሩ ስለሚያሠራው መጠለያ ማስተባበር በመጋቤ ሐዲስ ምናለ ተከናውነውበታል።
የክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት የቅዱሱን ወንጌል አገልግሎት በተጠናከረና ዘመኑን በዋጀ መልኩ እንዲሁም በመልክአ ምድራዊ አቀማመጣቸውና ከሚገኙባቸው የአገልጋዮች ብዛትና ምእመናን ባገናዘበ መልኩ ጉባኤ በማዘጋጀት አገልገሎቱን ለማጠናከር እየሠራ እንደሚገኝ ሊቀ ካህናት ዕዝራ ንዋይ የክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ተናግረዋል።
ሊቀ ካህናት ዕዝራ ቀጥለው የጥምር ጉባኤው ዓላማ የቅዱስ ወንጌል አገልገሎት ከማጠናከር ባለፈ የአብያተ ክርስቲያናት አገልጋዮችና ምእመናን እንዲሁም ሰንበት ትምህርት ቤት አባላት እንዲተዋወቁ ፣ ተቀራርበውና ተደጋግፈው እንዲያገለግሉ መደለድልን የሚፈጥር እንደሆነም ገልጸዋል።
በመሆኑም የመጀመሪያውን “ቅድሚያ ለቅዱስ ወንጌል” የአንድነት ጉባኤ በአቃቂ መጋላ ደብረ ምሕረት ቅዱስ አማኑኤልና ቅዱስ መርቆሬዎስ ቤተ ክርስቲያን ለማከናወን ተችሏል ብለዋል።
ደብሩ የተመረጠበትን ምክንያት ሊቀ ካህናቱ ከዛሬ ወር በፊት ወደቦታ ባቀኑበት ወቅት ተግባብቶ የመሥራት ችግር ተግዳሮት የሆነበት ፣ የምእመናንን ቁጥር አነስተኛ የሆነበት እንዲሁም በርካታ አባቶችና የወንጌል አገልጋዮች ብዙም ሄደው የማያስተምሩበት ቤተ ክርስቲያን መሆኑን በወቅቱ መታዘባቸውን አስተውሰው “ቅድሚያ ለወንጌል” ጉባኤ በዚሁ እንዲጀመር መነሻ እንደሆናቸውን አብራርተዋል።
መጋቤ ሐዲስ ምናለ በክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት የቅዱስ ወንጌል ጉባኤ አስተባባሪ ኮሚቴና የአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል ክፍል ሐላፊ በበኩላቸው ደብሩ የተመሠረተው አጭር ጊዜ ከመሆኑ ጋርና ከከተማና ከዋና መሥመር ትንሽ ወጣ ያለ በመሆኑ ምክንያት እንደሚፈለገው የወንጌል አገልግሎትን ለመስጠት አለመቻሉን ጠቁመዋል።
ይሁንና እግዚአብሔር ፈቅዶ በሊቀ ካህናት ዕዝራ መሪነት እንዲህ ባለ መልኩ ለማዘጋጀት ተችሏል ብለዋል።
ደብሩ ከአቃቂ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን በቅርብ ርቀት ስለሚገኝ በሠርክ ጉባኤና በሰንበት ትምህርት ቤት መርሐ ግብራት መጋቤ ሐዲስ ምናለ መጥተው እንደሚያገለግሉ የደብሩ ሰንበት ትምህርት ቤት አባላት የገለጹ ሲሆን በዚህም ለመምህሩ አገልግሎት ዕውቅና በመስጠትና በማመስገን በብፁዕነታቸው ቡራኬ ሽልማት አበርክተዋል።
የደብሩ አስተዳዳሪ በደብሩ እየተሠሩ የሚገኙትን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ሥራዎችን በሪፖርት መልክ አቅርበዋል ። በቀጣይም በቅዱስ ወንጌል አገልግሎት ጠንክሮና ተናቦ ለመሥራት በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ሊቀ ጳጳስ “የሚሰማ ጆሮ ያው ይስማ ” በሚል ርእስ መነሻነት ቅዱስ ማቴዎስ በጻፈው ቅዱስ ወንጌል ምዕ.13:9 መነሻነት ስለዘሪውና ስለ ዘሩ እንዲሁም ዘሩ ስለወደቀበት የመሬት ዓይነት በማብራራ አስተምረዋል።
ብፁዕነታቸው ፍቅር ተዘርቶብን ያልበቀለብን ፣ ቅንነት ወድቆልን ያላፈራን ፣ ዋጋ ተከፍሎልን ያልተረዳን ብዙዎች የሆነው ቅዱሱን ወንጌል በሚገባ ሆነን ስላልሰማነውና አገልጋዮቹም የቱ ይቅደም የሚለውን አሠራር ባለመልመዳችን ነው ብለዋል።
በመሆኑም እንዲህ ከከተማ በራቁ የሰው ቁጥር አነስተኛ በሆኑባቸው የመንገድም ተግዳሮት በሚሆኑባቸው ቦታዎች እንዲህ ዓይነት ልዩ አንድነት ጉባኤ ክፍለ ከተማው ቤተ ክህነትን በእጅጉ የሚያስመሰግን ነው ብለዋል።
ይህም ቃሉ የሚዘራው መልካም ገበሬ፣ የሚወድቅበት ለም መሬት የሚፈራውም መቶ ፍሬ እንዲሆን ትልቁን መደላድል ይፈጥራል በማለት ገልጸዋል።
ሊቀ ካህናት ዕዝራ ንዋይ ቀደም ሲል በነበራቸው አገልግሎት ዘርፍ በስብከተ ወንጌል ኃላፊነት፣ በጸሐፊነት እንዲሁም በደብር አስተዳዳሪነት ለቅዱስ ወንጌል አገልገሎት የነበራቸው ትጋት በዚህም ሥራ አስኪያጅነት ደረጃም እንዲሁም “ቅድሚያ ለወንጌል ” በሚል መሪ ቃል ማስቀጠላቸው በእጅጉ የሚያስደንቅ ነው። ለዚህም ከጎን በመሆን ማበረታታትና ማገዝ እንዲሁም መታዘዝ ያስፈልጋል ብለዋል።
አክውም “ቅድሚያ ለወንጌል ጉባኤን ላስተባበረው ለክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ላዘጋጀው ለደብሩ አስተዳደር ሰበካ ጉባኤ እንዲሁም ለተባበሩ አካላት ምስጋና አቅሮው ቡራኬ የሰጡ ሲሆን በቀጣይም በደብሩ የቅዱስ ወንጌል አገልግሎት እንዲጠናከር ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።
በመጨረሻም ብፁዕነታቸውን በቀጣይ ጊዜያትም መጥተው እንደሚያገለግሉ ቃል ገብተው ጉባኤውን በጸሎትና በቡራኬ አጠናቀዋል።
የአቃቂ መጋላ ደብረ ምህረት ቅዱስ አማኑኤልና ቅዱስ መርቆሬዎስ ቤተ ክርስቲያን ከአቃቂ ድልድይ በስተቀኝ በኩል ወደ አቃቂ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን የሚወስደውን መንገድ በመከተል ትንሽ እንደተጓዙ በስተቀኝ በኩል በታጠፍ የሚገኘውን መንገድ በመያዝ ቀጥታ በመሄድ መንደሩን እንዳለፉ ጫፍ ላይ የሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ነው።
