የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ፕሮግራሞች ያስተማራቸውን ደቀመዛሙርት ቅዱስ ፓትርያርኩ በተገኙበት አስመረቀ።
ሰኔ 27/2018 ዓ/ምየቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛ እና በመጀመሪያ ድግሪ ፣ በዲፕሎማ እና በካህናት ሴሚናር መርሐ ግብር በዲፕሎማ ያስተማራቸውን ደቀ መዛሙርት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራአስኪያጅ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ፣
፣ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣የከፍተኛው ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝጀንት ክብርት አበባ አለበል እና ጥሪ የተደረገላቸው ዕንግዶች በተገኙበት አስመርቋል።
መርሐ ግብሩ በጸሎተ ወንጌል የተከፈተ ሲሆን ልብሰ ተክህኖ በለበሱ ዲያቆናት “ህየንተ አበውኪ ተወልዱ ለኪ ደቂቅ ወትሰይሚዮሙ መላእክተ ለኩሉ ምድር ወይዘክሩ ሰመኪ ለኩሉ ትውልደ ትውልድ ” የሚለው የዳዊት መዝሙር በያሬዳዊ ዜማ ተዜሟል። (መዝ 44 )
በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 10 ቁጥር 1 ላይ መከሩ ብዙ ነው ሠራተኛው ግን ጥቂት ነው። እንግዲህ የመከሩ ባለቤት ሠራተኛ እንዲጨምር ለምኑት ተብሎ የተመዘገበው ቃለ ወንጌል ተነቧል።
በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጸሎተ ኪዳንም ተደርሷል።
በዩኒቨርሲቲው ሊቀ ጳጳስ በብፁ አቡነ ፊልጶስ ዶክተር ሪፖርት የቀረበ ሲሆን ብፁዕነታቸው ባቀረቡት ሪፖርት ከእግዚአብሔር ቤት መረቅናችሁ የሚለውን የመጽሐፍ ቃል አብራርተዋል።
የደቀመዛሙርቱን ተልእኮ አስመልክተው በገለጹት ሐሳብ የክርስቶስ ወንጌል አምባሳደሮች ናችሁ ፣በጥበብ ተመሩ፣ተግታችሁ ሥሩ፣ግራ በገባው ዘመን ለሀገራችሁና ለሕዝባችሁ ቅድሚያ ስጡ፣ተስፋ ሳትቆርጡ ተግታችሁ ሥሩ፣ከመከራ በኋላ ደስታ እንዳለ አስቡ፣ የመከራን ዝናብ ታግሣችሁ ሰማያዊ ዘር ዝሩ በማለት ለተመራቂ ደቀመዛሙርቱ መመሪያ ሰጥተዋል፣
ብፁዕነታቸው አክለው እንደገለጹት የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃን ይታይባችሁ፣ በትምህርት ቆይታችሁ አውቀናል ስትሉ አለማወቅን እንደተማራችሁ እወቁ፣ በችግረኛው ዓለም ችግርን የምትፈቱ እንጂ ችግርን የምትፈጥሩ እንዳትሆኑ የሚል አደራ ብፁዕነታቸው ለተመራቂ ደቀመዛሙርት አስተላልፈዋል።
በዩኒቨርሲቲው ሥርዓተ አስተምህሮ መሠረት ትምህርታቸውን በማጠናቀቅ ለምረቃ የበቁ ደቀ መዛሙርት
በሁለተኛ ዲግሪ 70 በመጀመሪያ ድግሪ 80 በካህናትዲፕሎማ 39 የማታ የመጀመሪያ ድግሪ160 በርቀት የመጀመሪያ ድግሪ 206 በድምሩ 555 ደቀ መዛሙርትን ዩኒቨርሲቲው አስመርቋል።
በምረቃ መርሐ ግብሩ መሠረት በተመራቂ ደቀመዛሙርት
“እለ ቅኑታን ኃቔሆሙ በጽድቅ” የሚል ያሬዳዊ ወረብ የተወረበ ሲሆን በቅኔ ምሑራን ቅኔያትም ቀርበዋል።
ከተመራቂ ደቀ መዛሙርት ዝማሬ በማያያዝ ፕሮፌሰር አባ ኃለ ገብርኤል ግርማ የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ባቀረቡት ሪፖርት የመማር ማስተማሩ ሂደት ተጨማሪ ስኬት አስመዝግቧል።እርሱም የመማሪያ መጽሔት ኅትመት ነው ብለዋል። ዩኒቨርሲቲው እያደገ መምጣቱንም አብሥረዋል።
ለተገኘው ስኬት ፕሮፌሰር አባ ኃይለ ገብርኤል የዩኒቨርሲቲውን መምህራን አመስግነዋል።
ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ተበባባሪ ፕሮፌሰር የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ያጠናቀቁ መሆናቸውን በሪፖርታቸው በይፋ አብሥረዋል።
ለብፁዕነታቸውም ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ስጦታ ተበርክቶላቸዋል። በብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የብዙኃን መገናኛ ቴሌቭዥን ድርጅት ሊቀ ጳጳስ ለብፁዕ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር አቡነ ፊልጶስ ተጨማሪ ስጦታ አበርክተዋል ።
በመቀጠልም ከፍኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂ ደቀ መዛሙርት በሁየቱም ጾታ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በትምህርታቸው በጣም ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂዎች በቅዱስነታቸው የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
የዩኒቨርሲቲው መምህር የክቡር ረዳት ፕፕሮፌሰር መኮንን ወርቅነህ የትምህርት ዝግጅትና አገልግሎት ታሪክ በንባብ የቀረበ ሲሆን የዕውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ሌሎችም የዩኒቨርሲቲው የረጅም ጊዜ አገለሰግሎት የሰጡ ነባር ሠራተኞች የዕውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ተመራቂ ደቀመዛሙርት ቀጣዩ አገልግሎታቸውን በአንቀጸ ሃይማኖት የተደነገገውን ዶግማ፣ቀኖና እና ትውፊት ጠብቀው ለማገልገል ቃለ መሀላ ፈጽመዋል።
ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ ለተመራቂ ደቀመዛሙርትእና ለመርሐ ግብሩ ታደሚዎች ትምህርተ ወንጌል የሰጡ ሲሆን ብፁዕነታቸው ባስተላለፉት የወንጌል መልእክት ቤተ ክርስቲያን ዕድለኛ መሆንዋን፣በአባቶች ፈንታ ልጆች መወለዳቸውን፣ልጆች የአባቶችን ኃላፊነት መረከባቸውን፣ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ በአባቶቻቸው የሚተኩ ልጆች እየጠፉ መሆኑን፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ በሰጠው ትምህርት አባቶቻቸው ነቢያት መከራ መቀበላቸውን፣ሐዋርያትም በጨለማውና ባልጫው ዓለም ቀጣይ መከራ እየተቀበሉ ብርሃን መሆናቸውን፣
ተመራቂ ደቀመዛሙርትም ለጨለመውና ላልጫው ዓለም ብርሃን መሆን የሚገባቸው መሆኑን አብራርተው ገልጸዋል።
ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ በዶክትሬት ድግሪ በመመረቃቸው የእንኳን ደስ አለዎት የመልካም ምኞት መልእክት አስተላልፈዋል።
በመጨረሻም በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርኩ ቃለ ምዕዳንና አባታዊ ትምህርት የሰጡ ሲሆን ቅዱስነታቸው ባስተላለፉት አባታዊ ትምህርት ሑሩ ወመሐሩ ኩሎ አሕዛበ ወእንዘ ታጠምቅዎሙ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ወአነ እሄሉ እስከ ህልቀተ ዓለም ተብሎ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 28 ላይ የተጻፈውን በማብራራት ተመራቂ ደቀመዛሙርት በተማሩት ትምህርት ተግተው እንዲያስተምሩ አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል።
ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው አክለው እንደገለጹት ሰው አዋቂ ሆኖ መፈጠሩን፣ በልዩ አፈጣጠር የተፈጠረ ሰው ክብሩን ጥሎ እንደእንስሳ ማሰብ የማይገባው መሆኑን፣ሰው ክብሩን ካወቀ እንደእንስሳ የማያስብ መሆኑን፣ትናንት ተማሪ የነበራችሁ ዛሬ መምህራን በመሆን ሰው ፈጣሪውን እንዲአምንና ክብሩን እንዲጠብቅ ሓላፊነታችሁን ልትወጡ ይገባል በማለት የአደራ መልእክት በማስተላለፍ መርሐ ግብሩን በጸሎት አጠናቀዋል።
©eotc tv
