የምዕራብ ካናዳ ሀገረስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ በግንባታ ላይ የሚገኘው የሆሣዕና መንበረ ጵጵስና ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንን ጎበኙ። ሰኔ 25 ቀን 2018 ዓ.ም
ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ የምዕራብ ካናዳ ሀገረስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆሣዕና መንበረ ጵጵስና ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን የሕንጻ አሰሪ ኮሚቴ የበላይ ጠባቂ በግንባታ ላይ የሚገኘውን ዘመን ተሻጋሪዉን የሆሣዕና መንበረ ጵጵስና ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያንን ጎብኝተዋል።የቤተክርስቲያኑ የግንባታ ሂደት በብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ለተመራዉ ልዑካን ቡድን በደብሩ አስተዳዳሪ በክቡር መልአከ ኤዶም ቆሞስ አባ ወልደትንሳኤ ባህሩ እንዲሁም በኢንጅነር ዝናቡ ወልዱ በሕንጻ ቤተመቅደሱ ግንባታ ስራ ሰፊ ገለጻ ተደርጓል።
ክቡር መልአከ ኤዶም በገለጻዉ ወቅት እንደገለጹት ይህንን ታሪካዊና ዘመን ተሻጋሪ ሕንጻ ቤተመቅደስ አስፈጽመን ለትውልድ ታሪክ ሰርተን ማስረከብ እንዳለብን ገልጸዉ፣ በሚደረገዉ የአለም አቀፍ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐግብር ላይ በመላዉ አለም የምንገኝ ኦርቶዶክሳውያን በመሳተፍ አሻራችንን እንድናኖር ጥሪያቸዉን አቅርበዋል።
ክቡር መልአከ ገነት ሙሴ ዘነበ በአዲስ አበባ ሀገረስብከት የፕሮጀክት ክፍል ኃላፊ፣እንደገለጹት የእሳት ቃጠሎ አጋጥሟት የነበረችዉን የሆሣዕና መንበረ ጵጵስና ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያንን ለማጠናቀቅ ከሐምሌ 10 እስከ 12 ቀን 2018 ዓ.ም በሚደረገዉ የገንዘብ ማሰባሰቢያ መርሐግብር ላይ በመሳተፍ፣ ስትቃጠል የተቆጫችሁ ሁሉ አሁን አሻራችሁን የምታሳርፉበት ጊዜና ስዓት በመሆኑ፣ሁላችንም በተጠቀሰው ቀንና ስዓት በመገኘት የልጅነት አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅረበዋል ።
ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ይኽንን ሕንጻ እየገነባችሁ ያላችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ በዚህ አስቸጋሪና ፈታኝ ወቅት ታሪክ የማይረሳው ትውልድ የሚዘክረው ሕያው ቅርስ ሠርታችኋልና ዋጋ ሰማያዊና ዘለዓለማዊ ነው ብለዋል።
ብፁዕነታቸው ባስተላለፉት አባታዊ የአደራ መልእክት በመላው ዓለም የምትገኙ የድንግል ማርያም ወዳጆች፤ ውለታ ያለባችሁ ሁሉ፤ ድምፃችንን በመስማት፤ ከጎናችን በመቆም፤ የሆሣዕና መንበረ ጵጵስና ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም መቅደስን ለማጠናቀቅ ከሐምሌ 10_12/ 2018 ዓ.ም በሚደረገው ዓለም አቀፍ የገቢ ማሰባሰብ መርሐ ግብር ላይ በመሳተፍ በሚቻላችሁ ሁሉ እንድትረባረቡ በእግዚአብሔር ስም የአደራ መልእክታቸዉን አስተላልፈዉ፣ ይህንን ዘመን ተሻጋሪ የጀመራችሁትን መልካም ሕንጻ ለፍጻሜ ደርሶ የድካማችሁ ውጤት ለማየት ያብቃችሁ በማለት ቃለ በረከት ሰጥተው፣ ለሕንጻ አሰሪ ኮሚቴዉ የስራ መመሪያ በመስጠት ጸሎት አድርሰው ሐዋርያዊ ጉዟቸውን አጠናቀዋል።
በጉብኝቱ ላይ ክቡር መልአከ ሕይወት ቀሲስ ንጉሤ ባወቀ የሀዲያና ስልጤ ሀገረስብከት ዋና ስራአስኪያጅ ፣ክቡር መልአከ ገነት ሙሴ ዘነበ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፕሮጀክት መምሪያ ኃላፊ ፣መልአከ ሰላም ተሾመ ገብረ ስላሴ ፣ መጋቤ አእላፍ ዮናስ ኢሳይያስ ፣ መልአከ ምሕረት ዐሥራት ዘውዴ፣ክቡር መልአከ ኤዶም ቆሞስ አባ ወልደ ትንሳኤ ባሕሩ ፣የሕንጻ አሠሪ ኮሚቴዎች፣የሰበካ ጉባኤ አባለት በጉብኝት መርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተዉ መልእክታቸዉን አስተላልፈዋል።
እንደሚታወቀዉ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ የምዕራብ ካናዳ ሀገረስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆሣዕናን በሆሣዕና በዓል ላይ በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባ ሀዲያና ስልጤ አኅጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆሣዕና መንበረ ጵጵስና ደብረገነት ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን የሕንጻ አሠሪ ኮሚቴ የበላይ ጠባቂ ሆነዉ መሰየማቸው ይታወቃል።
©ብሕንሳ ሚዲያ
