በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት የአብነት መምህራን በስብከተ ወንጌል አገልግሎት ላይ ድርሻቸውን እንዲወጡ የሚያስችልና በር የሚከፍት የሥልጠና መርሐ ግብር ተካሄደ። ኢኦተቤ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ
ሰኔ ፳፭/፳፻፲፰ ዓ/ምበኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል ክፍል አዘጋጅነት፣ በክፍለ ከተማው ለሚገኙ የአብነት መምህራን፣ የሊቃውንት ጉባኤ አባላትና ሰባክያነ ወንጌል የተዘጋጀ መንፈሳዊ ሥልጠና ተሰጠ።
የመርሐ ግብሩ ዋና ዓላማ የአብነት መምህራንና ሊቃውንት ያላቸውን ጥልቅ እውቀት በመጠቀም፣ በስብከተ ወንጌል ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ የበለጠ ውጤታማ፣ የበቃና የላቀ እንዲያደርጉ ማስቻል መሆኑ ተገልጿል።
ረዳት ፕሮፌሰር መምህር ግርማ ባቱ «የአብነት ትምህርትና ስብከተ ወንጌል» በሚል ርእስ ሥልጠና ሰጥተዋል። በገለጻቸውም የአብነት ትምህርት ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት መሠረታዊ እውቀትን፣ ጠንካራ ስብእናንና አገልጋይነትን የሚያጎለብት መሆኑን ገልጸዋል። እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትና የአብነት መምህራን በስብከተ ወንጌል ዘርፍ ተሳትፏቸውን በማሳደግ የቤተ ክርስቲያኒቱን ተልዕኮ ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።
በትምህርታቸው ወቅት የአብነት ትምህርት ቤቶች እውቀትንና ማንነትን በመቅረጽ ረገድ ያላቸውን ታሪካዊ ልዕልና፣ እንዲሁም ከስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጋር ያላቸውን የማይነጣጠል ትስስር በስፋት አብራርተዋል። የአብነት ትምህርት ከእውቀት ባለፈ ማንነትን፣ ሥነ ምግባርንና የአገልግሎት ብቃትን የሚገነባ ጥንታዊ የትምህርት ሥርዓት መሆኑን ጠቅሰው፣ ከዘመናዊ የስብከት ዘዴዎች ጋር በተጣጥሞ ለቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ የበለጠ አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚችልም አመልክተዋል።
መጋቤ ብሉይ መምህር አእመረ አሸብር «ወንጌል በተለያዩ ዘመናት የገጠሙት ተግዳሮቶች» በሚል ርእስ ሥልጠና ሰጥተዋል። በሥልጠናቸውም ወንጌል በታሪክ ውስጥ ያጋጠሙትን የአስተሳሰብ ፈተናዎች በመዳሰስ፣ ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ እስከ ዘመናዊነትና ድኅረ ዘመናዊነት ድረስ የተፈጠሩ ለውጦች ከወንጌል ጋር ያላቸውን ግንኙነት በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት አብራርተዋል።
በመርሐ ግብሩ የተገኙት ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ በሰጡት አባታዊ ምክር ፣ የወንጌል አገልግሎት ከሁሉም በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ገልጸው፣ ስብከት የሚሰጥበት አቀራረብ፣ የጊዜ አጠቃቀም፣ በአገልጋዮች መካከል ያለው ቅንጅትና ለምዕመናን የሚቀርበው መልእክት በጥበብ ሊቀርብ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባና የሀዲያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ መልአከ ምሕረት አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ፣ ረዳት ፕሮፌሰር መምህር ግርማ ባቱ የመንፈሳዊና ኢኮኖሚያዊ ምክትል ሥራ አስኪያጅ፣ መጋቤ ብሉይ መምህር አይመረ አሸብር በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የትምህርትና ማሰልጠኛ መምሪያ ጸሐፊ፣ መልአክ ገነት መምህር ልሳነ ወርቅ ተስፋ የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ፣ የክፍለ ከተማው የሥራ ኃላፊዎች፣ መምህራን፣ የሊቃውንት ጉባኤ አባላትና ሰባክያነ ወንጌል ተሳትፈዋል።
ዲ/ን ቅዱስ ጥበቡ
ነቢዩ ሚክያስ
