ወነበሩ በቤተ መቅደስ እንዘ ዘልፈ ይባርክዎ ለእግዚአብሔር ” (ዘወትር እግዚአብሔርን እያመሰገኑ በመቅደስ ኖሩ) ሉቃ 24:53
በመልአከ ምሕረት አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ (ቆሞስ)
የዐዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ
ይኽ ኃይለ ቃል ከጌታችን ዕርገት በኋላ ደቀ መዛሙርቱ የነበራቸውን መንፈሳዊ ሕይወት የሚገልጽ ነው።
✍️ አምልኮአቸው ቀጣይነት ያለው ነውና ደቀ መዛሙርቱ ጌታ በአካል ከተለያቸው በኋላ ተስፋ በመቁረጥ አልተበተኑም። በቤተ መቅደስ በመገኘት ምስጋናቸውን ቀጥለዋል። ክርስቲያን በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ሆኖ እግዚአብሔርን በማመስገን መጽናት እንዳለበት ያስገነዝበናል።
✍️ ቤተ መቅደስ መጠጊያ ነው። ቤተ መቅደስ ለደቀ መዛሙርቱ የጸሎትና የእግዚአብሔርን ረድኤት የሚቀበሉበት ሥፍራ ነው። ዛሬም ለእኛ ቤተ ክርስቲያን ከዓለም ጫጫታ ርቀን፣ ከፈጣሪ ጋር የምንገናኝባትና መንፈሳዊ ኃይል የምናገኝባት የነፍሳችን ወደብ ናት።
✍️ ክርስቲያን የምስጋና ሕይወት ሊኖረው ይገባል። “እንዘ ዘልፈ” (ዘወትር) መባሉ ምስጋናቸው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ አልነበረምና ነው። ክርስቲያን በደስታም ሆነ በከባድ ፈተና ውስጥ እግዚአብሔርን ማመስገን እንደሚገባው ያጠይቃል። ምስጋና ለጸሎት መልስ መቀበያ መንገድ ነው።
✍️ የበዓለ ሃምሳን ተስፋ የሚያገኙት በቤተመቅደስ ሲቆዩ ነው።
በመቅደስ መቆየታቸው ጌታ የሰጣቸውን የጰራቅሊጦስን (የመንፈስ ቅዱስን) ተስፋ በጸሎት እንዲጠባበቁ አድርጓቸዋል። እኛም በቤተ መቅደስ የምናሳልፈው ጊዜ የእግዚአብሔርን ጸጋ ለመቀበል ዝግጁ ያደርገናል።
ሕይወታችን ከምስጋናና ከቤተ እግዚአብሔር ጋር የተሳሰረ እንዲሆን ይመክረናል።
✍️ #ማብራሪያ:- ሉቃ 24:49-53 ድረስ ያለው ቃል ሲተነተን
ሉቃ 24:49 “ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ…” በሚለው ቃል ውስጥ መንፈስ ቅዱስን “ልብስ፣ኃይለ ማለቱ ስለምን ነው ቢሉ”
👉 “#ልብስ” ሰውን እንደሚሸፍን፣ መንፈስ ቅዱስም ሐዋርያትን ከፍርሃት፣ ከስህተትና ከድካም ይሸፍናቸዋል።
👉 “#ኃይል” መባሉ ወንጌልን ለማስተማር፣ ተአምራትን ለማድረግና ሞትን ለመጋፈጥ የሚያስችል ጽናት በመሆኑ ነው። በኢየሩሳሌም መቆየታቸውም ተስፋው ከአንድ ማእከል (ከጽዮን) እንዲወጣ ለማሳየት ነው።
የእስክንድርያው ሊቅ ቅዱስ ቄርሎስ ይኽንን ሲተረጉም:- ሐዋርያት ዓለምን ለመለወጥ የሰው ጥበብ ሳይሆን መለኮታዊ ኃይል ያስፈልጋቸዋል ። “ኃይልን እስክትለብሱ” ማለቱ፣ መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት እንደ ጦር ዕቃ ሆኖ ከጠላት ጥቃት ስለሚጠብቃቸውና በቃልም በተግባርም ብርቱዎች ስለሚያደርጋቸው ነው ብሎ ያስተምራል።
✍️ ሊቁ ቅ/ዮ/አፈወርቅ ደግሞ “ሐዋርያት በኢየሩሳሌም እንዲቆዩ የታዘዙት፣ መንፈስ ቅዱስ ሳይወርድላቸው በፊት ተበትነው ለጠላት እንዳይጋለጡና ልክ እንደ ሠራዊት በአንድነት ሆነው ኃይል እንዲቀበሉ ያዘዛቸው ስለሆነ በኢየሩሳሌም ቆዩ” ይላል።
፪. “አውጽኦሙ አፍአ እስከ ቢታንያ (ወደ ቢታንያ መውጣታቸው)” ሉቃ 24:50
👉 #ቢታንያ የኀዘን ቤት (House of Sorrow) ትባላለች። ጌታችን ደቀ መዛሙርቱን ወደዚያ ይዟቸው መውጣቱ፣ ክብር ከሕማም በኋላ እንደሚገኝ ለማሳየት ነው። አልዓዛርን ያስነሳበት፣ እርሱም ስለ እኛ መከራ የተቀበለበት አካባቢ በመሆኑ የትንሣኤያችንና የክብራችን ምልክት ነው።
#እጆቹን አንሥቶ ባረካቸው ሲል ይህ ቡራኬ የክህነት ሥልጣን ማጽኛና በዓለም ዙሪያ ለሚያስተምሩት ትምህርት የጸጋ መጀመሪያ መሆኑን ያብራራሉ። እስከ ፓትርያርክነት ድረስ ሹማቸው እንዲል
✍️ እየባረካቸው” ማረጉ፣ ቡራኬው ለቤተ ክርስቲያን ዘላለማዊ እንጂ የተቋረጠ አለመሆኑን ሲያጠይቅ ነው።
👉 ሊቁ ቅዱስ ቄርሎስ የበረከት ምንጭ መሆኑን፣ በረከት የባሕርይ ገንዘቡ መሆኑን ሲያሳይ እንደሆነ ይገልጻል። “ጌታ እጆቹን አንሥቶ መባረኩ፣ እርሱ ራሱ የበረከት ምንጭ መሆኑንና በብሉይ ኪዳን በነበሩ ካህናት ይደረግ የነበረው ቡራኬ በእርሱ የተፈጸመ መሆኑን ያጠይቃል። እንዲል
ሉቃ 24:51 “ወዓርገ ውስተ ሰማይ (ወደ ሰማይ ዓረገ)
👉 ጌታ ዕርገቱን የጀመረው ከምድር ዝቅ ብሎ ሳይሆን፣ በሥልጣኑ ወደ ላይ በመውጣት የሰውን ባሕርይ በክብር ከፍ ለማድረግ መሆኑን፤ ሰው ወደ ልዕልና መውጣቱን፣ ልዕልና ነፍስን ገንዘብ እንዲያደርግ ሲያመለክት ነው።
✍️ ቅዱስ ቄርሎስ “እርሱ በማረጉ የሰውን ባሕርይ በኪሩቤልና በሱራፌል ራስ ላይ አቆመው”። ቀድሞ በኃጢአት ምክንያት ተዘግቶ የነበረው የሰማይ ደጅ በክርስቶስ ዕርገት ተከፈተልን። እንዲል (Commentary on the Gospel of Saint Luke (Sermon CLX)
“እነርሱም ሰገዱለትና በብዙ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ ዘወትርም እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እየባረኩ በመቅደስ ኖሩ።” ሉቃ 24:52-53
✍️ ምስጢራዊ ትርጓሜው፦ ጌታ በአካል ሲለያቸው ማልቀስ ሲገባቸው “በብዙ ደስታ” መመለሳቸው፣ ሞት መሸነፉንና አምላካቸው በሰማይ እንዳለ ስላረጋገጡ ነው።
“በታላቅ ደስታ ተመልሰው በቤተ መቅደስ ኖሩ” የሚለው ደግሞ ሕይወታቸው ሁሉ የምስጋና ሕይወት እንደነበር ሲያመለክት ነው።
✍️ የጌታ ዕርገት ድል መሆኑን ሲያጠይቅ ነው፦ “በታላቅ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ” የሚለው ቃል ሐዋርያት የጌታን መለየት እንደ ኀዘን ሳይሆን እንደ ድል መቆጠራቸውን ያሳያል። ቤተ መቅደስ መቆየታቸውም፦
✍️ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በታላቅ ደስታ ተመለሱ የሚለውን ሲተረጉም፦ ጌታቸው በአካል ቢለያቸውም፣ ሞትን ድል አድርጎ በክብር ማረጉንና ዳግመኛ እንደሚመጣ ስላወቁ ኀዘናቸው ወደ ደስታ እንደተለወጠ ያስተምራል። ብሎታል (Homilies on the Acts of the Apostles (Homily I) & Commentary on the Gospel of Matthew )
✍️ታዛዥነትትን ያመለክታል፦ ጌታ በኢየሩሳሌም ቆዩ ስላላቸው ታዘው ቆይተዋል።
✍️ ለአምልኮ፦ አሮጌው ሥርዓት አልፎ አዲሱ የአምልኮ ሥርዓት (በመንፈስና በእውነት) መጀመሩን ለማብሰር ነው።
✍️ ሊቃውንት ይኽንን፦ በሐዲስ ኪዳን ትርጓሜ ጉባኤ ቤት “ዘልፈ ይብርክዎ” (ዘወትር ይባርኩት ነበር) የሚለው፣ ደቀ መዛሙርቱ በጸሎተ ጰራቅሊጦስ ተወስነው መንፈስ ቅዱስን ይጠባበቁ እንደነበር ያትታል። ይህም ለምእመናን “በረከት የሚገኘው በቤተ መቅደስ በመጽናት ነው” የሚል ትምህርት ይሰጣል።
✍️ መጠበቅና ትዕግሥት፦ ሐዋርያት ኃይል እስኪያገኙ ድረስ በመቅደስ እንደቆዩ፣ እኛም የእግዚአብሔርን እርዳታ በትዕግሥት መጠበቅ እንዳለብን እንማርበታለን።
✍️ ከመከራ በኋላ የሚገኝ ክብር አለ፦ ቢታንያ ወይም የኀዘን ስፍራ የነበረች ብትሆንም አሁን ግን የዕርገት (የክብር) መነሻ መሆኗ ከመከራ ኋላ ክብር፣ ከልቅሶ ኋላ ደስታ፣ ከሞት ኋላ ሕይወት፣ ከውድቀት ኋላ ትንሣኤ መኖሩን ያበሥረናል።
✍️ የማያቋርጥ ምስጋና፦ ደቀ መዛሙርቱ በቤተ መቅደስ የነበራቸው ቆይታ በምስጋና የተሞላ እንደነበር፣ የክርስቲያን ሕይወትም ሁልጊዜ አምላኩን በማመስገን መታጀብ እንዳለበት እንማራለን።
✍️ በቤተ መቅደስ መኖር እንደሚገባ ቅ/ዮ/አፈወርቅ፦ ሐዋርያት በቤተ መቅደስ መኖራቸው፣ ለጸሎት ያላቸውን ትጋትና ከመንፈስ ቅዱስ መውረድ በፊት ራሳቸውን በቅድስና እያዘጋጁ እንደነበር ያሳያል ይላል። በማለት ተርጉሞታል።
ማጠቃለያ “ወነበሩ በቤተ መቅደስ (በመቅደስ ኖሩ)” ማለቱ፣ ሐዋርያት ዓለምን ለመለወጥ ከመውጣታቸው በፊት ራሳቸውን በቅድስና ያዘጋጁበትን “የሱባኤ” ሕይወት ያሳያል። ክርስቲያን ከዓለም ጫጫታ ወጥቶ መረጋጋት ያለበት በመቅደሱ ነውና።
ሐዋርያቱ ሁልጊዜ እያመሰገኑ በቤተ መቅደስ ኑረዋልና የክርስቲያን ሕይወት መሠረትና ማረፊያውም ቤተ መቅደስ (ቤተ ክርስቲያን) መሆን እንዳለባት ያስተምራል። “ዘልፈ” (ዘወትር) መባሉ ደግሞ ጸሎትና ምስጋናችን በችግር ጊዜ ብቻ ሳይሆን በሁኔታዎች ሁሉ መሆን እንዳለበት ይመክረናል።
✍️ ሐዋርያት ከመንፈስ ቅዱስ መውረድ በፊት በመቅደስ እንደቆዩ፣ እኛም በሕይወታችን የሚገጥሙንን ፈተናዎች ለማለፍ፦
• በትዕግሥት መቆየት (ከእግዚአብሔር ፊት አለመኮብለልን)፣
• በአንድ ልብ መጸለይን (ከቅዱሳንና ከእመቤታችን ጋር መቆራኘትን)፣
• ሁልጊዜ ማመስገንን (በሰላሙም በፈተናውም ጊዜ) ምስጋናን ገንዘብ ማድረግ ይገባናል።
ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፦ “ሐዋርያት በመቅደስ መቆየታቸው፣ መንፈስ ቅዱስ የሚወርደው ሁልጊዜ በጸሎትና በአንድነት ባሉ ልቦች ላይ መሆኑን ሊያስተምሩን ነው” እንዳለው ሁሉ በመቅደሱ ቆይተን ጸጋ መንፈስ ቅዱስ እንዳይርቀን በጸሎት ተወስነን እንድንኖር አምላከ አበው ይርዳን።
#ቅድስት ሀገሬ ኢትዮጵያ!!!
#የወለድሻቸው ልጆችሽ ይውለዱሽ!!!
#ልጆችሽ ይሟገቱልሽ እንጂ አይሞግቱሽ!!!
#በስደት ያሉ ልጆችሽ በበረከት ይመለሱልሽ!!!
#ድንበርሽን እሳት መሀልሽን ገነት አድርጐ የዓለም ማረፍያ ያድርግሽ #አሜን!!!
መልአከ ምሕረት አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ (ቆሞስ)
የዐዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ
