የደብረ ታቦር የዐራቱ ጉባኤ ቤትና ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የሁለትዮሽ ስምምነት ተፈራረሙ።
ግንቦት 15 ቀን 2018 ዓ.ም
የደብረ ታቦር ደብረ ልዑላን መድኃኔዓለም የአራቱ ጉባዔያት ምስክር ጉባኤ ቤት እና የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የሁለትዮሽ ስምምነት ተፈራረሙ።
ሀገር በቀል ዕውቀትን (Indigenous Knowledge) ከዘመናዊው ሳይንስ ጋር በማቀናጀት ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት መሠረት የሚጥል ታሪካዊ የሁለትዮሽ (Bilateral) ስምምነት ሰነድ ዛሬ ተፈርሟል።
የሁለትዮሽ ስምምነቱን የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሰሎሞን አበጋዝ እና የደብረ ታቦር ደብረ ልዑላን መድኃኔዓለም የአራቱ ጉባዔያት ምስክር ጉባኤ ቤት መምህር መምህረ መምህራን የኔታ በጽሐ ዓለሙ በጋራ ተፈራርመዋል ።
በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሰሎሞን አበጋዝ እንደገለፁት፦ ”ሀገር በቀል ዕውቀትን መሠረት ያደረጉ ስምምነቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት እየተሰጣቸው የመጡ፣ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የበለጸገ ባህል፣ ታሪክ እና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ዕውቀት ባላቸው ሀገራት ዘንድ ሕጋዊና ስልታዊ ማዕቀፍ የሚፈጥሩ ትልቅ ፋይዳ ያላቸው ናቸው። ዛሬ የተፈረመው ስምምነት ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመበት ዓላማና ከቁልፍ የሥራ አፈጻጸም አመላካቾች (KPIs) ጋር ቀጥታ የሚገጣጠም በመሆኑ፣ ዩኒቨርሲቲያችን ስምምነቱን በተግባር ለመተርጎም ሙሉ ቁርጠኛ ነው” ያሉ ሲሆን።
የጉባኤ ቤቱ መምህር መምህረ መምህራን የኔታ በጽሐ ዓለሙ በበኩላቸው፤ ጉባኤ ቤቱ ከዚህ ቀደምም ቢሆን ለሀገር ጠቃሚ በሆኑ የታሪክ፣ የሳይንስ እና የባህል ይዘት ባላቸው መጻሕፍት ላይ ዩኒቨርሲቲው በሚያዘጋጀው “ጉኔ” የመጽሐፍ ዳሰሳ መድረክ ላይ በንቃት ሲሳተፍ ቆይተናል ያሉ ሲሆን የአራቱ (፬ቱ) ጉባዔያት ቤታችን ጥበብና ዕውቀትን ከአባቶቻችን ለልጆቻችን ለማስተላለፍ ራዕይ አንግቦ እየሠራ በመሆኑ እና ይህንን ራዕያችንን ተግባራዊ ለማድረግ እና ዘመናዊውን ዕውቀት ከነባሩ ዕውቀት አስተባብሮ ሀገርን እና ትውልድን በዕውቀትና በሥነ-ምግባር ለማነጽ ከደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ጋር ስምምነት መደረጉን እና
ይህም ስምምነት የነበረውን ግንኙነት ይበልጥ ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው ገልጸዋል።
የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የአለቃ ገብረሃና የባህል ጥናትና ልማት ዳይሬክተር መምህር መሰረት ወርቁ እንደገለፁት፣ ሁለቱ ተቋማት በሚከተሉት ስልታዊ ዘርፎች ላይ :-በሀገር በቀል ዕውቀት፣ እሴትና ክህሎት ልማት ላይ መስራት እንዲሁም የሀገር በቀል እና ዘመናዊ ሥርዓተ ትምህርት (Curriculum) መቅረጽ፤ የግዕዝ እና የአማርኛ ቋንቋ ድርሳናትን ወደ ሌሎች ቋንቋዎች መተርጎም፤ በጥንታዊ የብራና ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙ የሕክምና፣ የአስትሮኖሚ፣ የትምህርትና መሰል ጥበቦችን ማውጣትና ጥቅም ላይ ማዋል፤ በመዛግብትና ሙዚየም ማደራጀት፣ በቅርስ ጥበቃ፣ በቱሪዝም፣ በሥነ-ምግባር፣ በታሪክ፣ በግብረ-ገብ እና በሰላም ግንባታ ዙሪያ በጋራ መስራት፤ የንባብ ባህልን ማዳበር፣ በቤተ-መጻሕፍት እና በተለያዩ አቅም ማጠናከሪያ ሥልጠናዎች ዙሪያ በጋራ መስራት እንደሆኑ ተገልጿል ።
© ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ
