ቅዱስነቱም ሊቅነቱም በክብር ይታሰብ!
ማኅቶተ ቤተ ክርስቲያን
ቅዱስ ያሬድ የቤተ ክርስቲያናችን ማኅቶት፣ የዓደባባይ መገለጫዋ፣ የውስጥ የአገልግሎቷ አብነት፣ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን ከኦሪት እስከ ራእየ ዮሐንስ ያዜመችበት ልሳኗ፣ የሊቃውንት አባት፣ ኢትዮጵያዊ ዕንቁ ነው።
ቅዱስ ያሬድ በ505 ዓ/ም የተወለደ ኢትዮጵያዊ አብሪ ኮከብ ሊቀ ነው። ግንቦት 11 በደብረ ሐዊ የተሠወረበትን ቀን ምክንያት በማድረግ በዓሉን በድምቀት ታከብረዋለች።
ዛሬ የሚከበረው የቅዱስ ያሬድ ዜማ ምንጩ ከእግዚአብሔር መሆኑ በክብር የተገለጠበትና በቤተ ክርስቲያን አገልግቶት መስጠት የጀመረበት ቀን እንደሆነ ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች።
የዜማው ሊቅ የምስጢሩ ባላባት የሆነው ቅዱስ ያሬድ ቅዱሱን ዜማ እግዚአብሔር ከገለጠለት በኋላ በአክሱም በተመስጦ ዜማውን ሲቃኝ በወቅቱ የነበሩት የዘመኑ ሰዎች እንዲሁ አልተቀበሉበት ነበር።
በዚህም ምክንያት የእግዚአብሔር እንደሆነ እንዲታወቅ ከታኅሣሥ 1-7 ድረስ ሱባኤ እንያዝ ተባባሉ ከዚያም በሰባተኛው ቀን ታኅሣሥ ፯ አርብ ቀን ቅዱስ ያሬድ በአክሱም ጽዮን ፊትለ ፊት ሆኖ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተሰቀለ ሆኖ ታይቶት እንዲህ ያለ ማዜም ጀምረ “ወልዶ መድኅን ንሰብክ ዘእምቅድመ ዓለም ሀሎ አክሊለ ሰማዕት ሠያሜ ካህናት ወተስፋ መነኮሳት ወልዶ መድኅንን ሰብክ ። (መዝሙር ዘስብከት)
ዘበመስቀሉ ተቀነወ ወበነቢያት ተሰብከ መላእክት ወሊቃነ መላእክት ሰብሕዎ ኪያሁ ንሰብክ መድኅነ” (ዕዝል) በማለት በክብር እያዜመ ተገለጠ። በዚህም ዜማው ከእግዚአብሔር ነው ብለው አመኑ ሁሉም ተቀበለ። ከዚያ ጀምሮ በቤተ ክርስቲያናችን የቅድስ ያሬድ ዜማ አገልግሎት ላይ መዋል እንደጀመረ ታሪክ ያስረዳል።
መክብበ ሊቃውንት ቅዱስ ያሬድ ከአክሱም ጀምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በተለይም በዙር አባ በጣና ሐይቅ በደብረ ሐዊ አስተምሯል።
ቅዱስ ያሬድ ከሰማይ ከተገለጠለት ዕውቀት በተጨማሪ የተመስጦ ሕይወት በሙሉ ሰውነት የማገልገል ጣዕም የተሰጠው በመሆኑ ዝማሜውን ሲዘም እግሩ በጦር ቢወጋም አልተሰማውም ነበር።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለበርካታ ዘመናት ሕያውን የምሥራች ቅዱሱን የመንግሥት ወንጌል የሰበከችበት ታሪኳ የያሬድ ዜማና ድርሰት ነው።
ቅዱስ ያሬድ ከመንፈሳዊ ብቃት በተጨማሪም ወድቆ የመነሳት ምልክት፣ የትዕግስት ክብር ማሳያ፣ የጥበብ አርአያ ነው።
በአሁኑ ሰዓት በሽዎች የሚቆጠሩት የድጓ ፣ የአቋቋም፣ የቅኔ፣ የዝማሬና መዋስዕት፣ የቅዳሴ እንዲሁም የትርጓሜ መጻሕፍት መምህራን ደቀ መዛሙርት አባታቸው ቅዱስ ያሬድ ነው።
በቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ያሬድ አሻራ ያልነካው አገልጋይ አይኖርም የቤተ ክርስቲያን ክብር ልብሷ የውስጥ ውበቷ ነውና።
በመሆኑም ቅዱስ ያሬድ የተሰወረበት ግንቦት 11 ቀን በዓል ቤተ ክርስቲያን ባለውለታዋን በልዩ ክብር ታከብረዋለች።
በአዲስ አበበ ሀገረ ስብከት ብቸኛ ለስሙ መታሰቢያ በታነጸው ቤተ ክርስቲያን በደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን በድመቀት በርካታ ሊቃውንት ቅዱሱን እና ባለውለታቸውን በማክበር እግዚአብሔርን ሲያመልኩ ቅዱሱንን ሲያከብሩ ያድራሉ።
የተሰወረበት በዓል በወርኃ ትንሣኤ በበዓለ ሃምሳ ቀናት በመሆኑ ” ያሬድ ካህን ሰበከ ትንሣኤሁ ለክርስቶስ” እያሉ የትንሣኤው ምስክር መሆኑንን እየገለጹ ያመሰግናሉ።
በዓሉንም በታላቅ ድምቀት ይከበራል።
ይሁን እንጂ ቅዱስ ያሬድ እንደሥራውና እንደቅድስናው ይከበራል ወይ? የሚለው ጥያቄ መልሱ አይደለም ነው።
ቅዱስ ያሬድ ደራሲ ብቻ አይደለም ቅዱስም በብቃት ደረጃ የደረሰ የእግዚአብሔር ቅዱሱ ነው።
በዚህም የማክበሩ ደረጃ ሲታይን ብዙ ሥራ የሚጠይቅ እንደሆነም ያመላክታል።
ሌላው ቅዱስ ያሬድ የቤተ ክርስቲያን ባለውለታ የዓደባባይ ውበቷና ክብሯ ጌጥ የሀገራችንንም የትም የሚማይገኝ ታላቅ ሀብት ሆኖ ሳለ ዜማው በክብር ተጠብቆ እንዲተላላፍና የዓለም በሕያውት ያለ ቅርስ ተብሎ በማስመዝገብ ደረጃ ውስንነቶችን ይስተዋላሉ።
በመሆኑም በተደራጀና በተጠና መልኩ ቅዱስ ያሬድን በቅድስናውንም በሊቅነቱም በበለጠ በኢትዮጵያ አልፎ በዓለም ደረጃ ሊታወስ የሚችልበትን ቁም ነገር መሥራት የዚህ ዘመን አደራ ነው።
