ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ግቢ ውስጥ እየተገነባ ያለውን ዓለም አቀፍ የስብሰባ አዳራሽ ጎበኙ
ግንቦት ፮ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተቋማዊ ክብሯንና ዓለም አቀፋዊ ተጽዕኖዋን የሚያሳድጉ የልማት ሥራዎችን አጠናክራ የቀጠለች ሲሆን፣ በዛሬው ዕለት ግንቦት 6 ቀን 2018 ዓ.ም ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በግቢው ውስጥ የሚገኘውንና ዘመኑን የዋጁ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ያካተተውን ዓለም አቀፍ የስብሰባ አዳራሽ ግንባታ በቦታው ተገኝተው ጎበኙ።
በዚህ ከፍተኛ የሥራ ጉብኝት ላይ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የድርጅት ሥራ አስኪያጆች እና የመምሪያ ኃላፊዎች መገኘታቸው የፕሮጀክቱን ታላቅነት ያመለክታል።
ስለ ግንባታው ሂደት ዝርዝር መረጃ የሰጡት የ AV Consultant አማካሪ አርክቴክት ሳሙኤል አፈወርቅ እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ በ2,500 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ግዙፍ ሕንጻ ሲሆን በአንድ ጊዜ 2,500 ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል ዋና አዳራሽን ጨምሮ የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ አዳራሽ፣ የሰንዳኬት (Syndicate) መሰብሰቢያ፣ የቪ.አይ.ፒ (VIP) አዳራሽና ሬስቶራንት እንዲሁም ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ቢሮዎችን በውስጡ ይዟል።
ሕንጻው ከመደበኛ የግንባታ ጥበቡ ባሻገር እስከ 30 ቋንቋዎችን በቅጽበት መተርጎም የሚችል የትርጉም ክፍል፣ ዘመናዊ ዲጂታል ቤተ መጻሕፍት፣ የጋዜጣዊ መግለጫ መስጫ (Press Conference) ክፍል፣ የድምፅ መከላከያ (Soundproof) ሥርዓት እና ዘመናዊ የቅዝቃዜ መቆጣጠሪያ (AC) ግብዓቶች የተሟሉለት በመሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ያደርገዋል።
ከቴክኖሎጂው ባሻገር ለተገልጋዮች ምቾትና ለደኅንነት ልዩ ትኩረት የተሰጠው ሲሆን፣ በአንዴ 16 ሰዎችን መጫን የሚችሉ ሁለት ሊፍቶች፣ ለ90 ሰዎች የሚሆኑ ዘመናዊ መጸዳጃ ቤቶች እና ቀድሞ እስቶር በነበረው ሰፊ ቦታ ላይ ከ300 በላይ መኪናዎችን ማቆም የሚችል ዘመናዊ ፓርኪንግ ተዘጋጅቶለታል። የሕንጻው የውስጥ (Interior) ዲዛይን የቤተ ክርስቲያኒቱን ረጅም ታሪክ፣ ጥበብና መንፈሳዊ ማንነት በሚሰብክ መልኩ የተቀረጸ ከመሆኑም በላይ አጠቃላይ ግንባታው የአረንጓዴ ልማትን (Green Infrastructure) መሠረት ያደረገ ሆኖ ለውበት የሚተከሉ ዕፅዋት በሙሉ ሀገር በቀል እንዲሆኑ ታቅዷል። በተጨማሪም የግቢውን የውሃ ችግር ለመፍታት የከርሰ ምድር ውሃ ወጥቶለታል። በ Atom Construction አማካኝነት እየተገነባ የሚገኘው ይህ ታሪካዊ ፕሮጀክት ተጠናቆ ለአገልግሎት ሲበቃ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለምታካሂዳቸው ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ኩነቶች ታላቅ አቅምና ገጽታ የሚፈጥር መሆኑ በጉብኝቱ ወቅት ተመላክቷል።
©ኢኦተቤ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ
