ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ዘተናገረ በበዓለ ትንሣኤሁ ለእግዚእነ ወኣምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘዕሥራ ምእት ዓሠርቱ ወሰምንቱ ዓመተ ምሕረት

በስመ ኣብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ኣሐዱ ኣምላክ ኣሜን፡
በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣
ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፣
የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፣
በሕመም ምክንያት በየፀበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፣
እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ፣
በቤዛዊ መሥዋዕትነቱ ከሞተ ኃጢኣት ታድጎ የትንሣኤ ሙታንን በር የከፈተልን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም ኣደረሰን ኣደረሳችሁ!
‹ወኣነ እሜጡ ነፍስየ ቤዛ ኣባግዕየ ከመ ካዕበ ኣንሥኣ፤
ዳግመኛ ኣነሣት ዘንድ ነፍሴን የበጎቼ ቤዛ ኣድርጌ እሰጣለሁ (ዮሓ 10÷17)
ጌታችን ኣምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰብኣዊ ክዋኔው ሰው ቢሆንም በመለኮታዊ ክዋኔው የኣብና የመንፈስ ቅዱስ ቃል ወይም ወልደ እግዚአብሔር ነው፤
በመሆኑም በሰብኣዊ ክዋኔው መዋች ሲሆን በመለኮታዊ ክዋኔው ተነሽና ኣንሺ ነው፤ ከዚህ ኣንጻር ሥግው ቃል ሁለቱንም ተግባራት በኣንድ ኣካልና ክዋኔ የመፈጸም ሥልጣን ኣለው፤ ይህም በመሆኑ ራሴን የማኖርና የማንሣት ሥልጣን ኣለኝ በማለት እውነታውንና ምንነቱን ኣሳየ፤
ጌታችን ይህንን ኣስመልክቶ ከመሞቱና ከመነሣቱ በፊት ለቅዱሳን ሓዋርያት በተደጋጋሚ ኣስረድቶኣል፤ ስለሆነም የጌታችን ሞትና ትንሣኤ ድንገተኛና የግድ ሳይሆን ታውቆ ያደረና የውድ እንደሆነ ከዚህ እውነታ እንረዳለን፤
ጌታችን ይህንን ተግባር በውድ ፈቃዱ የፈጸመው በእግዚአብሔር ኣሰራር ከዚህ ውጭ የዓለም ድኅነት የሚከናወንበት ዕድል ስለሌለ ነው፤ በእግዚአብሔር ኣሰራር ኃጢኣትና በደል የሚሰረዘው በቤዛዊ መሥዋዕት ብቻ እንደሆነ ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ በነበረው የቤዛዊ መሥዋዕት ኣቀራረብ የታወቀ ነው፤
በመሆኑም የሰውን ምልኣተ ኃጢኣት ሙሉ በሙሉ ሰርዞ ሰውን ከሞት ቅጣት ነጻ ለማውጣት ብቃት ያለው ቤዛዊ መሥዋዕት ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ነበረበት፤ ይሁን እንጂ ለዚህ ዓይነቱ ቤዛዊ መሥዋዕት ብቁ የሆነ ከፍጡራን ወገን ስላልተገኘ ‹‹ለሊሁ መሥዋዕት፣ ወለሊሁ ሠዋዒ፣ ወለሊሁ ተወካፌ መሥዋዕት ማለትም›› ራሱ መሥዋዕት፣ ራሱ መሥዋዕት ኣቅራቢ ሊቀ ካህናት፣ ራሱ ተወካፌ መሥዋዕት ኣምላክ ሆኖ የቤዛነታችንን መሥዋዕት ራሱ በራሱ ለራሱ ኣቀረበ››፤
በዚህ ቤዛዊ መሥዋዕትም እኛን ከሞት ቅጣት ነጻ ኣደረገን፤ትንሣኤያችንንም በትንሣኤው ኣበሰረ፤ በክርስትና ሃይማኖት የሚገኝ ፍጹም ድኅነትና ነጻነት በዚህ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ የተመሠረተ ነው፤
የተወዳደችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!
ጌታችን በትንሣኤው ትንሣኤያችንን ሲያበስረን የትንሣኤ ሰዎች ሆነን በመንፈስና በሞራል በማደግ ብርሃናተ ዓለም ልንሆን እንጂ እንደገና የጨለማው ኃይል መሳሪያዎች ልንሆን ኣይደለም፤ የሞቱና የትንሣኤው ምስጢር በንጹሁ ኅሊናችን ካስተዋልነው ውስጣችን እሱን ለመቀበል የሚያዳግተው ኣይደለም፤
ከዚህ ኣንጻር በትንሣኤው ኣምነን ትንሣኤያችንን እየተጠባበቅን የምንገኝ ሕዝበ ክርስቲያን በቅን ኣስተሳሰብ፣በርቱዕ ኣእምሮና በኃይለ ሃይማኖት እየታገዝን ጨለማውን ዓለም ወደብርሃን ለመለወጥ መጣርና መትጋት ይጠበቅብናል፤
የጨለማው ዓለም መንፈስ ሊያጠፋን ካልሆነ በቀር እንደማይጠቅመን በተጨባጭ የምናውቀው ነው፤ወደድንም ጠላንም ያለን ብቸኛ ኣማራጭ ብርሃንን መከተል ነው፤ እሱም እግዚአብሔር ነው፤በብርሃን የሚመላለስ እንደማይጐዳ በእግዚአብሔር የሚኖርም ተጐድቶ ኣያውቅምና ነው፤
ዓለም እንደ ኣጠቃላይ በጨለማ ተውጦ ሲተረማመስ የሚታየው ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ምርጫው ስላደረገ ነው፤ ስለሆነም የኛ ምርጫ ብርሃን የሆነውን እግዚአብሔር እንዲሆን የቤተ ክርስቲያን የዘወትር ጥሪ ነው፤
በመጨረሻም፡-
የትንሣኤ በዓላችንን ስናከብር ዓለም በክፋቱ ያጨለመባቸውን ወገኖች ጦማችው እንዳይውሉ ካለን ከፍለን የተራቡትን በማብላት፣ የተጠሙትን በማጠጣት፣ የታረዙትን በማልበስና የዕለቱ ደስታ ተካፋይ እንዲሆኑ በማድረግ ቀኑ ለሁላችንም ፍጹም ብርሃን ሆኖ ይውል ዘንድ ክርስቲያናዊ ግዴታችንን እንድንወጣ ጥሪያችንን በእግዚአብሑር ስም እናስተላልፋለን፤
መልካም የትንሣኤ በዓል ያድርግልን!!
“እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ”
“ወስብሐት ለእግዚአብሔር”
ኣሜን!!!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ
ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣
ሚያዝያ 4 ቀን 2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ