በሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት የለገጣፎ ኆኅተ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ሕንጻ ቤተክርስቲያን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ በተገኙበት ቅዳሴ ቤት በዓል ተከበረ
ግንቦት 16 ቀን 2018 ዓ.ም
ቅዳሴ ቤቱ ሲከበር ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፤ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ፤ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፤ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፤ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መገናኛ ብዙኀን ድርጅት የበላይ ሓላፊ የሰሜንና ምሥራቅ አፍሪካ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስን ጨምሮ ሌሎችም ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ተገኝተዋል።
በተጨማሪ የሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት የሥራ ሓላፊዎች ፤ መልአከ ገነት መምህር ኤርምያስ ውብሸት የለገጣፎ ኆኅተ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ፤ አገልጋይ ካህናትና ፤ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ፣ ዘማሪያንና በርካታ ምእመናን ቅዳሴ ቤቱ ሲከበር የበረከቱ ተካፋይ ሁነዋል።
በዚሁ መርሐ ግብር ታቦተ ሕጉ ከመንበሩ ወጥቶ ምእመናንን የባረከ ሲሆን በሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እና በሰንበት ትምህርት ቤት ዘማርያን ሕንጻ ቤተክርስቲያኑ ቅዱስ ፓትርያርኩን ጨምሮ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ቡራኬ ለምርቃት መብቃቱንና የቅዳሴ ቤቱ መከበሩን የሚያዘክር ያሬዳዊ ጥዑመ ዜማ ቀርቧል።
ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መገናኛ ብዙኀን ድርጅት የበላይ ሓላፊ የሰሜንና ምሥራቅ አፍሪካ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሰጡት ትምህርት ደግሞ በአዲሱ ሕንጻ ቤተክርስቲያን “ቅዳሴው በሊቃነ ጳጳሳት ተቀድሶበታል ፣ሕፃናት አረጋዊያንም ቆርበውበታል ፣ከዚህ የበለጠ ደስታ ምንም ነገር የለም ፣ እንኳን ደስ ያላችሁ” ብለዋል።
ብፁዕነታቸው አክለውም ይህ ሕንጻ ቤተክርስቲያን እንዲጠናቀቅ መመሪያ ሰጥተው ግንቦት 16 ቀን 2018 ዓ.ም ቅዳሴ ቤቱ እንዲከበር ላደረጉት ለብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና ሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ምስጋና ይገባቸዋል ሲሉም ተደምጠዋል።
ከዚህ በመለስ የለገጣፎ ኆኅተ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ሕንጻ ቤተክርስቲያን ግንባታ ለፍፃሜው እንዲበቃ ገንዘባቸውን ፣ እውቀታቸውንና ጊዜያቸውን በበጎ ፈቃደኝነት የሰጡ እንዲሁም በአስተባባሪነት ፣ በልዩ ልዩ የሥራ ድርሻዎችና ሓላፊነቶች የጎላ ድርሻ የነበራቸው ሁሉ ከቅዱስ አባታችን ሽልማት ወስደዋል።
በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፤ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሰጡት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ “እግዚአብሔር አምላክ ይህንን ሕንጻ ቤተክርስቲያን ለማነፅ አነሳስቶ ስላስፈፀማችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ” ብለዋል።
ቅዱስ አባታችን ለለገጣፎ ኆኅተ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን ምእመናን “ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ ለብዙ ዘመናት መገልገያ የሚሆናችሁን እግዚአብሔርን የምታመሰግኑበት ፣ የምትቆርቡበትን ሕንፃ ቤተክርስቲያን ነው የገነባችሁትና እንኳን ደስ ያላችሁ” ሲሉም አክለዋል።
ቅዱስነታቸው “ከዛሬ ጀምሮ ይህንን አዲስ ሕንጻ ቤተክርስቲያን ካቴድራል ብለነዋል” ያሉ ሲሆን ቤተክርስቲያኑ በስያሜው ልክ መሆን ስለሚገባው ትምህርት ቤትና ሌሎችንም ከዚህ የበለጠ ልማት ሊሰራበት እንደሚገባ አመላክተዋል።
ከ፻ ሚሊየን ብር በላይ ፈሰስ ተደርጎበት ለምርቃት የበቃው የለገጣፎ ኆኅተ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ሕንጻ ቤተክርስቲያን ጥር 29 ቀን 2002 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፤ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚደንት፣ የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ለሰላም የክብር ፕሬዚደንት፣ የዓለም የሰላም አምባሳደር የመሰረት ድንጋይ ተቀምጦለት ግንባታው መጀመሩ ይታወቃል።
©Eotc tv
