የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ የመቄዶንያ አረጋውያንና አአምሮ ሕሙማን ማዕከልን ጎብኝቶ የ300,000 ብር ድጋፍ አደረገ!!
ጳጉሜን ፭ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም
በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ የሥራ ሐላፊዎች እና ሰባክያነ ወንጌል የ2019 ዓ.ም አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመምሪያው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ መሪነት በመቄዶንያ አረጋውያንና አአምሮ ሕሙማን ማዕከልን ጎብኝቷል።
በማዕከሉ ለሚገኙ ወገኖች የበዓል መዋያ ይሆናቸው ዘንድ በመምሪያው ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ማርቆስና በመምሪያው ሰባክያነ ወንጌልና ልዩ ልዩ ሠራተኞች ስም የ300,000/የሦስት መቶ ሺህ ብር/ ድጋፍ በማድረግ አጋርነቱን አረጋግጧል።
በዕለቱም የመምሪያው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ለ2019 ዓ.ም ዘመን መለወጫ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል፤ ትምህርተ ወንጌልም ሰጥተዋል ።
በሰጡት ትምህርተ ወንጌል “በዚህ ስፍራ የተሰባሰባችሁ ወገኖቻችን ትናንት ለሀገርና ለቤተክርስቲያን ከፍተኛ አበርክቶት ያበረከታችሁ ናችሁ፤ ልትኮሩ ይገባል የእኛ መምሪያም ከእንዲህ ዓይነቱ በጎ ተግባር ጋር መተባበር ይገባል ብለዋል።
ብፁዕነታቸው አክለውም የዛሬው ጉብኝታችን የ2018 በጀት ዓመት ስምሪት ማጠቃለያ ነው፤ በአዲሱ በጀት ዓመት በትልቅ ትኩረት መምሪያው ከማዕከሉ ጋር በመተባበር በማስተማርና በማጽናናት እንዲሁም በአስፈላጊው ሁሉ አብሮ ይሠራል ሲሉ አረጋግጠዋል።
የማዕከሉ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ቢኒያም በለጠ ባደረጉት ንግግር በዕለቱ በመምሪያ ለተደረገው ጉብኝትና ድጋፍ ከፍተኛ ምሥጋና አቅርበው በቀጣይም አብሮነቱ እንዲቀጥል አሳስበዋል።
በመጨረሻም በብፁዕነታቸው አባታዊ ቡራኬና ጸሎት መርሐ ግብሩ ፍጻሜ አግኝቶ ሕሙማኑና አረጋውያኑን የመጎብኘት ሥራ ተከናውኗል።
ዘገባው የመምሪያው ነው።
