በደብረ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስና መካነ ጎልጎታ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ አዘጋጅነት ለማኅበረ ካህናቱና ለወጣቶች ሲሰጥ የቆየው የሦስት ቀናት ሥልጠና በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ ቃለ በረከት ተጠናቀቀ።
ኢኦተቤ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያሰኔ ፳፯/፳፻፲፰ ዓ/ም
በደብረ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስና መካነ ጎልጎታ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ አዘጋጅነት ለማኅበረ ካህናቱና ለወጣቶች ሲሰጥ የቆየው የሦስት ቀናት ሥልጠና በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ ቃለ በረከት ተጠናቀቀ።
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከሚገኙ ጥንታዊያትና ባለታሪኮች አብያተ ክርስቲያናት መካከል የደብረ ነጎድጎድ ቅዱስ ዮሐንስና መካነ ጎልጎታ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አንዱ ነው።
በዚህም ታላላቅ ሊቃውንት ባለውለታ ምእመናን እንዲሀም ዘመኑን የወጁ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች የሚገኙበት ደብር ነው።
የደብሩ አስተዳዳር ሰበካ ጉባኤ የሊቃውንቱን አገልግሎት፣ የምእመናኑን ተሳትፎና የወጣቶችን የዓላማ ተከታይነት የበለጠ ዘመኑን በዋጀ መልኩ ለማጠናከር በማሰብ ከሰኔ 24-26/2018 ዓ/ም ለተከታታይ ሦስት ቀናት በተለያዩ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንት የሥልጠና መርሐ ግብር አከናውኗል።
በሥልጠና መርሐ ግብር ማጠናቀቂያ ቀን ላይ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባና ሀዲያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ረዳት ፕሮፌሰር ቀሲስ ግርማ ባቱ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የማኅበራዊና ኢኮኖሚ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ፣ መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ መልአከ አሚን ለይኩን አበጀ የደብሩ አስተዳዳሪ ተገኝተዋል።
ሥልጠናው ለካህናቱና ለሊቃውንቱ ብቻ ሳይሆን ከሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች፣ ከአካባቢው ወጣቶች እንዲሁም ከምእመናን ለተወጣጡ አካላት መሆኑን ተገልጿል።
የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ አሚን ለይኩን አበጀ ሥልጠናው የካህናትን እረኝነትን፣ በዋጋ የተገዙ ምእመናን እንደ ቃሉ መጠበቅ እንደሚገባ ሥልጠናው በሰፊ መሰጠቱን አብራርተዋል።
ዘመኑ ብዙ ተግዳሮት ያለው መሆኑን ያስታወሱት አስተዳዳሪው ለዚህ የበቃና የነቃ ካህን ሊቅ እንዲሁም እንደቃሉ ለካህን መታዘዝና ለመጠበቅም ዝግጁ የሆነ ምእመን እንዲኖር ሥልጠናው ድርሻ እንዳለው ጠቁመዋል።
አስተዳዳሪው ሥልጠናው የተሳከና በታቀደው መልክ የተከናወነ መሆኑም የጠቀሱ ሲሆን ከዚህ በላይ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ ከዋና ሥራ አስኪያጅ ጋር መገኘታቸውን ለትናንትናው ድካምና በጎ ሥራ ዕውቅና እንዲሁም ለቀጣይም ጉልበት ብርታት ይሆነናል ብለዋል።
የሥልጠናው ተሳታፊዎች በበኩላቸው በሦስት ቀናቱ ሥልጠና ባገኙት ጭብጥ መሠረት ወደፊት ስለሚሠሩትና ለሚያደርጉት በአቋም መገልጫ መልክ ያቀረቡ ሲሆን በሥልጠናው ትልቅ ቁም ነገር እንዳገኙ ፣ በተሰጠው ሥልጠናም ለተግባራዊነቱ እንደሚተጉ፣ ሥልጠናው ቀጣይነት እንዲኖረውና በዚህ ሥልጠና ማዘጋጀትም ለደከሙ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበው በቀጣይ ምእመናንን በማስተባበር የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ቃል ገብተዋል።
በመርሐ ግብሩ ከደብሩ ሰበካ ጉባኤ አባላት ጀምሮ ሁሉም ተሳታፊዎች ምስክር ወረቀት ከብፁዕነታቸውን እጅ ተቀብለዋል።
የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ምሕረት አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ በበኩላቸው የሥልጠና ውጤት በጎችን በተኩላ ከመበላት መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ከዚህ የከፋውን በጎችን ለማይረባ እእምሮ ተላልፈው እንዳይሰጡ እንዲሁም የሚበሉ ከመሆን አልፎ የሚባሉ በጎች እንዳይሆኑ እንዲሁም አስብቶ ከመብላት በመቆጠብ መንጋውን በቅዱሳት መጻሕፍት ቃል መሠረት በማድረግ ዕለት ዕለት መጠበቅ ይገባል ብለዋል።
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ በበኩላቸው ባዩት ነገርና በሆነው ጉዳይ መደሰታቸውን ገልጸው ከተመሪው መሪው ከድግሱ አስተባባሪው ነውና በቀናው መንገድ ለመሩት ለደብሩ አስተዳዳሪ ምስጋና አቅርበዋል።
ሥልጠና በትናንትናና በነገ መካከል ያለ ድልድይ መሆኑን ያስታወሱት ብፁዕነታቸው ለላቀው የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ራስን የማዘጋጃ መንገድ መሆኑን ገልጸዋል።
ብፁዕነታቸው ዕውቀትና ልምድ ዕለት ዕለት አብሮ ካልሆኑት ዘላቂ ዘመድ እንዳልሆነ የተጠቆሙ ሲሆን ለዚህ ሁነኛ ማሻሻያውና ማሰንበቻው በየጊዜው የሚሰጡ ሥልጠናዎች ናቸው ብለዋል።
በመጨረሻም ብፁዕነታቸው ሀገረ ስብከቱ በሰጠው ሁሉን አቀፍ መመሪያ መሠረት ላከናወናችሁት ሥልጠና እናመሰግናለን በቀጣይ በተጠናከረና ውጤቱ በሚለካ መንገድ እንዲቀጥል እናሳስባለን ብለዋል።
