የአዲስ አበባ ሀገረ_ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ሰሎሞን በቀለ የመስቀል ደመራ በዓልን አስመልክቶ የማኅበር ቀለም ጥናት ላይ የሚገኙት ሊቃውንት ጎበኙ።
መስከረም ፯/፳፻፲፱ ዓ/ም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ሰሎሞን በቀለ የመስቀል ደመራ በዓልን አስመልክቶ የማኅበር ቀለም ጥናት ላይ የሚገኙት ሊቃውንትን ጎበኙ።
በጉብኝት መርሐ ግብሩ ላይም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ሰሎሞን በቀለ፣ የሀገረ ስብከቱ ዋና ዋና ክፍል ኃላፊዎችና የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጆች በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ሊቃውንት አባቶች የመስቀል ደመራ በዓልን አስመልክቶ የማኅበር ቀለም ጥናት በማድረግላይ የሚገኙትን ሊቃውንት ጎብኝተዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት ቅዱስ መስቀል በእግዚአብሔር ፈቃድ የተቀበረበት ቦታ በደመራው ጢስ የታወቀበትና በንግሥት ዕሌኒ አማካኝነት በመስቀሉ የተገኘበትን ቀን በማስመልከት በዓሉ በድምቀት ይከበራል።
በዚህ በዓልም በአንድ በተዘጋጀ ቦታ የአድባራት የገዳማት ሊቃውንትና ምእመናን በመሰባሰብ የመስቀል ደመራን በዓል በልዩ ድምቀት ይከበራል::
በአዲስ አበባ መስቀል ዐደባባይ በሚከረው የመስቀል ደመራ በዓል በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ካህናት አስተዳደር መምሪያ መሪነት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አማካኝነት በሥሩ ከሚገኙ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ከሁሉም የተወሰኑ ሊቃውንትን በመምረጥ በበዓሉ የሚደርሰውን ስብሐተ እግዚአብሔር ቀለም በጋራ በማጥነት ያቀርባሉ።
በዚህም መሠረት በ2019 ዓ/ም ለሚከረበው የመስቀል ደመራ በዓልም ከነሐሴ 25/2018 ዓ/ም ጀምሮ የማኅበር ቀለሙን በጋራ እያጠኑ ሲሆን ጥናቱ በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መምህር ዕንቆባሕርይ ተከሥተ የካህናት አስተዳዳር መምሪያ ኃላፊ ገልጸዋል።
አክለውም ከቤተ መቅደስ እስከ አዳራሽ ድረስ ያለውን ቦታ ለአገልግሎት ክፍት በማድረግና ቅድሚያ በመስጠት፣ የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን ከታች እስከ ላይ ያሉ ሊቀ ሥልጣናትን ሁሉንም በተገቢው ሁኔታ ስላስተናገዱና ስለተቀበሏቸው ምስጋና አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ሥራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ሰሎሞን በሰጡት መልእክትም፣ የሀገረ ስብከቱ ዋና ዋና ክፍሎችና የክፍለ ከተማ ሥራ አስኪያጆች በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ቢሆኑም፣ ሊቃውንት አባቶች ይህንን ሥራ በሐላፊነት በመሥራታቸው ደስ እንዳሰኛቸው ገልጸዋል።
በተጨማሪም በ2019 ዓ.ም. ሊቃውንት አባቶች መብታቸውን ለማስጠበቅ በቁርጠኝነት እየሠሩ እንደሚገኙና ለዚህም ጸሎት፣ ጊዜና ትዕግስት እንደሚጠይቅ አሳስበዋል።
ሊቃውንቱም አንዱ ሌላውን አሳልፎ በመስጠት የሚገኝ የለምና አስታራቂ ሆናችሁ ለፍቅርና ለአንድነት ስትኖሩ፣ እኛም “ሊቃውንቱን ነፃ የምናወጣበት እንዴት ነው?” የሚለውን በማሰብ ትኩረት አድርገን እንድንሠራ ያግዘናል በማለት መልእክት አስተላልፈዋል።
በቀጣይም ሰፊ ጉባኤ በማዘጋጀት የሊቃውንቱን ሕይወት ለመለወጥ የውይይትና የሥልጠና መድረኮች ለማዘጋጀት እየተሠራ መሆኑን ክቡር ሥራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ሰሎሞን ገልጸዋል።
ዘጋቢ ጽናት አስቻለው
