የምሥራቅ ካቶሊኮስ እና የማላንካራ ሜትሮፖሊታን የሆኑት ቅዱስነታቸው ሞራን ማር ባስልዮስ ማርቶማ ማቴዎስ ሣልሳዊ፣በመንበረ ፓትርያርክ የቅርሳ ቅርስ ጥበቃ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር ገበኙ ።
መስከረም 15 ቀን 2019 ዓ.ም
የሕንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ እና ልዑካኑን በመንበረ ፓትርያርክ የቅርሳ ቅርስ ጥበቃ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር ጉብኝት አድርገዋል።
በመዘክሩ ገለጻ ያደረጉት ረዳት ፕሮፌሰር ዳንኤል ሠይፈሚካኤል የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የጥናት እና ምርምር መምሪያ ኃላፊ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ በዘመናት ውስጥ ያለፈችበትን ውጣ ውረድ፣ የፓትርያርኮቿን ታሪክ፣ እንዲሁም በተለይም ከሕንድ ጋር ያላትን ደም የተገበረበት የረጅም ዘመን የአንድነት ታሪክ ለልዑካኑ በስፋት አብራርተዋል።
ረዳት ፕሮፌሰር ዳንኤል ለልዑካኑ በሰጡት ማብራሪያ፣ የሁለቱ ሀገራትና አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት የረጅም ዘመናት ታሪክ ያለው መሆኑን አንስተዋል። በተለይም በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኦቶማን እና የማምሉክ ኃይሎች በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ ከባድ የወረራ አደጋ በደቀኑበት ወቅት፣ ከፖርቹጋል ጦር መሪ ክርስቶፈር ዳጋማ ጋር አብረው የመጡ የሕንድ ወታደሮች ከኢትዮጵያውያን ወንድሞቻቸው ጎን ተሰልፈው ሀገሪቱንና ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመታደግ ከፍተኛ መስዋዕትነት መክፈላቸውን አውስተዋል።
ሌላው የሁለቱን አብያተ ክርስቲያናት የጠበቀ መንፈሳዊ ትስስር አጉልቶ የሚያሳየው፣ በ1965 (እ.ኤ.አ) በንጉሠ ነገሥት አጼ ኃይለ ሥላሴ እና በበብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ የተካሄደው ታሪካዊው የኦሪየንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ ላይ የሕንድ ቤተክርስቲያን አባቶችን ተሳትፎ በማስታወስ፤ የሕንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን
ካቶሊኮስ በነበሩት በብፁዕ ወቅዱስ አባ ኦገን ባቫ (Baselios Augen I) አማካኝነት ለኢትዮጵያው ፓትርያርክ በስጦታ የተበረከተውንና አሁንም በሙዚየሙ በክብር ተቀምጦ የሚገኘውን እጅግ ማራኪ፤ ከዝሆን ጥርስ የተሠራ መስቀል ለልዑካኑ አሳይተዋል። ይህ ስጦታ የሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት ፍቅር እና መንፈሳዊ አንድነት ሕያው ምስክር መሆኑንም አክለዋል።
የምሥራቅ ካቶሊኮስ እና የማላንካራ ሜትሮፖሊታን የሆኑት ቅዱስነታቸው ሞራን ማር ባስሊዮስ ማርቶማ ማቴዎስ ሣልሳዊ ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ባደረጉት ጉብኝት ጥልቅ የሆነ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
“የማላንካራ ኦርቶዶክስ ልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ባደረገው አጭር ጉብኝት እጅግ ተደሰተናል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ማግኘት ፣ ታላላቅ ገዳማትን እና አብያተ ክርስቲያናትን መጎብኘት ችለናል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን በእምነታቸው እና በሃይማኖታዊ ሥርዓታቸው ጠንካራ እና ንቁ መሆናቸውን በማየታችን በጣም ደስተኞች ነን። ወደፊት፤ የገጠሟቸው ፈተናዎች እና መከራዎች አብቅተው፣ በዓለም ላይ ካሉ ቀዳሚ አብያተ ክርስቲያናት አንዷ ሆና እንደምትወጣ ተስፋ እናደርጋለን። ቤተ ክርስቲያኒቱ በታሪኳ እና በሕይወት ጉዞዋ ብዙ ሰማዕታት ስላሏት፣ ይህ ትልቅ በረከት አለው። የእነዚያ ሰማዕታት ደም ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ጸጋ (በረከት) እንዳመጡ እናውቃለን። አሁን ቤተ ክርስቲያኒቱ በፍጥነት እያደገች ሲሆን፣ በዓለም አብያተ ክርስቲያናት መካከልም ራሷን እንደ መሪ (ታላቅ) እያስቀመጠች ትገኛለች።
ለቤተ ክርስቲያኒቱ፣ ለጳጳሳቱ፣ ለካህናቱ፣ እንዲሁም በእምነታቸው እና በሥርዓታቸው ጸንተው ለሚገኙ ምዕመናን ሁሉ ፤ ሰላም እንደሚመጣ ተስፋ እናደርጋለን፣ እንጸልያለንም በማለት
ገልጸዋል ።
በጉብኝት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና ሸገር አህጉረ ስብከተ ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ መልከጼደቅ የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ የጠቅላይ ቤተክህነት የየመምሪያ ኃላፊዎች፣ ተገኝተዋል ።
© EOTCTV
